ኢትዮጵያ የምትገመገምበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ፣ በማሰቃየት (Torture) ላይ ያተኮረ ስብሰባ በጄኔቫ ተጀመረ፡፡ የምክር ቤቱ የፀረ ማሰቃየት ኮሚቴ 76ኛ መድረክ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ካዛኪስታን፣ ሉክሰንበርግና ስሎቫኪያ በፀረ ማሰቃየት (Torture) ላይ የሠሩትን ሥራ ያስገመግማሉ ተብሏል፡፡
ማክሰኞ ሚያዚያ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በተጀመረው የኮሚቴው 1978ኛ ስብሰባ ላይ፣ የኮሎምቢያ የሰብዓዊ መብቶች ባለሥልጣናት በአገሪቱ ያለውን ሰብዓዊ የሰዎች አያያዝ በሰፊው ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መረጃ እንዳመለከተው ስድስቱ አገሮች በተከታታይ ቀናት ለኮሚቴው ሪፖርታቸውን በማቅረብ ይገመገማሉ፡፡ ስብሰባው አስከ እ.ኤ.አ. ግንቦት 12 ቀን 2023 ይቀጥላል ብሏል፡፡
ከተገምጋሚዎቹ አገሮች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ግንቦት 2 ቀን 2023 ሪፖርቷን እንደምታቀርብ ከወጣው መርሐ ግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡
የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የፀረ ማሰቃየት (Torture) ኮሚቴ የሚገመግመው የአገሮች ሪፖርት በዋናነት፣ የሰዎችን የሕግና ሰብዓዊ አያያዝ የተመለከተ መሆኑንና ሰዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ፣ ከተያዙ በኋላና ወይም ተፈርዶባቸው በእስር ላይ ሳሉ የሚያጋጥማቸው ሰብዓዊ አያያዝ ለኮሚቴው ሪፖርት ይደረጋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ የምክር ቤቱ አባል አገሮች ለዜጎቻቸው የሚያደርጉት የሕግ አያያዝ ሰብዓዊነት የተሞላው መሆን አለመሆኑን፣ በዚህ መድረክ በሚቀርብ ሪፖርት እንደሚለይ የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡
የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ዳይሬክተር ማሀማኔ ሲሴ ጉሩ፣ በሰዎች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ዓይነት የማሰቃየት አያያዝን ለማስቀረት የዓለም አገሮች መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህም በተመድ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግ ላይ የተደነገገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የምክር ቤቱ መረጃ እንዳመለከተው በበርካታ አገሮች ይህንን ዓለም አቀፍ ድንጋጌ በመተላለፍ የማሰቃየት ወንጀል ይፈጸማል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የበለጠ ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡