ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸውና በጤና ላይ ከባድ ችግር የሚያስከትሉ የፀረ ወባ በሽታ ኬሚካሎች፣ በሕገወጥ መንገድ እየተዘዋወሩ መሆኑን እንደደረሰበት፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ለሪፖርተር ገለጸ፡፡
የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው የፀረ ወባ በሽታ ኬሚካሎችን የክልሉ የዞንና የወረዳ ጤና ተቋማት እንዲያሰባስቡ፣ ከተሰበሰቡ በኋላም እንዲወገዱ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደነበር፣ ሐሰተኛ ደብዳቤ የያዙ አካላት ግን በየወረዳው እየገቡ ኬሚካሎቹን እየወሰዱ እንደሆነ መረጋገጡን፣ የክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና ጤና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ማሌ መቴ ተናግረዋል፡፡
‹‹ከአዳሚ ቱሉ፣ ከጤና ሚኒስቴር ‹መጣን› የሚሉ ሰዎች በየዞኑ ወረዳ እየገቡ ኬሚካል እየሰበሰብን ነው ይላሉ፡፡ ሰዎቹ ግን ፎርጅድ የሆነ ደብዳቤ የያዙ ናቸው፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ኬሚካሎቹን ከሰበሰቡ በኋላ ጠፍተው፣ በደቡብ ኦሞ፣ በጎፋ፣ በወላይታ በፖሊስ ከእነ ተሸከርካሪያቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች አሉ፤›› ብለዋል፡፡
የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የወባ ማስወገድ ፕሮግራም አማካሪ አቶ ሔኖክ በቀለ በበኩላቸው፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸውና መወገድ ያለባቸው የፀረ ወባ በሽታ ኬሚካሎች፣ በክልሉ በሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች በሕገወጥ መንገድ እየተዘዋወሩ መሆኑን በተደረገ ክትትል ማረጋገጥ እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡
ለወባ በሽታ ርጭት ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ ፕሮፎክሰርና ኦንዶካርፕ የተሰኙ 21 ሺሕ ኪሎ ግራም ኬሚካሎች፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው በማለፉ በክልሉ ከሚገኙ የጤና ተቋማት እየተሰበሰቡ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሔኖክ፣ በኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞን ኬሚካሎችን በመሰብሰብ ወደ ክልሉ ጤና ቢሮ ሳያስገቡ በሕገወጥ መንገድ ለማዘዋወር የሞከሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
በተደረገው ክትትል በደቡብ ኦሞ ኬሚካል ለመጫን ሁለት አይሱዙ ተሽከርካሪዎች ይዘው የገቡ ሁለት ሰዎች እንደተያዙ፣ ከተያዙ በኋላ በአካባቢው በፖሊስ ዋስትና ተለቀው ንብረታቸው እንደተያዘ፣ በኮንሶ ዞንም በተመሳሳይ ድርጊት የተሰማሩ ሰዎች ስለመኖራቸው ነዋሪዎቹ በሰጡት ጥቆማ መሠረት ወደ ጤና ቢሮው በመሄድ ጊዜው ያለፈ ኬሚካል አስወጋጅ እንደሆኑ የሚያስመስል ሐሰተኛ ደብዳቤ ይዘው የቀረቡ ሰዎች እንደተገኙ፣ በዚህ ሁኔታ ሕገወጥ ሥራ ሲሠሩ እንደነበሩ ማወቅ መቻሉን የጠቀሱት አቶ ሔኖክ፣ የፈጸሙትን ጥፋት በሚመለከትም ለጤና ሚኒስቴር ጭምር እንዳሳወቁ ገልጸዋል፡፡
ኬሚካሎቹን ሲያዘዋውሩ ተገኙ የተባሉት ድርጅቶችና ግለሰቦች እንደሆኑ ስለመታወቁ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሔኖክ፣ ‹‹አዎ አውቀናቸዋል፡፡ እነሱ ኬሚካሎቹን ያሰባሰቡት ‹የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎችን የሚያስወግድ የአዳሚ ቱሉ ማኅበር ነው ያሰማራን በሚል ነው፤›› ብለው፣ ኬሚካሎችን ለመውሰድ ያስገቡት ደብዳቤ ግን ሐሰተኛ መሆኑን ማረጋገጥ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
‹‹ሰዎቹ ፎርጂድ ማኅተም ይዘዋል፡፡ ያቀረቡት ደብዳቤም በዚሁ ማኅተም በድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተፈርሞበታል፡፡ ‹በማኅበሩ የተደራጀን ወጣቶች ነን› ነው የሚሉት፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
በሕገወጥ መንገድ የመዘዋወር ሙከራ እየተደረገባቸው እንደሆነ የተነገረላቸው ኬሚካሎቹ፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ካለፈ በኋላ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ቢደረግ ሊያስከትሉት የሚችለውን ጉዳት በተመለከተ ምላሽ ሲሰጡም፣ ‹‹ጥናት መደረግ አለበት፡፡ ኬሚካል ያው ኬሚካል ነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የመጠቀሚያ ጊዜው ካለፈ የሚያደርሰው ጉዳት ከባድ ነው፡፡ ይህን ያህል ጉዳት ያደርሳል ብሎ በእርግጠኝነት ለመግለጽ ግን ጥናት ያስፈልጋል፡፡ ግን ከባድ ጉዳት የሚያደርስ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የአዳሚ ቱሉ ፀረ ተባይ ማምረቻ ፋብሪካ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የፀረ ወባ ኬሚካሎችን ለማሰባሰብ የተለያዩ ማኅበራትን በማደራጀትና ከኢትዮጵያ የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ኮርፖሬሽን ከአዳሚ ቱሉ ፀረ ተባይ ማምረቻ ፋብሪካ እንደተደራጁ በመግለጽ፣ ‹‹ፅናት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ዕቃዎች አስወጋጅ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› የተደራጁ ወጣቶች ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ በደብዳቤ ገልጸው እንደነበርም ሪፖርተር የተመለከተው ደብዳቤ ያሳያል፡፡ የክልሉ ጤና ቢሮ ደብዳቤው ሐሰተኛ መሆኑን እንደደረሰበት ነው የገለጸው፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ለሪፖርተር የላከው ሌላው ደብዳቤም፣ ባለፉት አሥር ዓመታት የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካሎች ለቤት ውስጥ ርጭት ጥቅም ሲውሉ ቢቆዩም፣ በ2012 ዓ.ም. የአገልግሎት ጊዜያቸው ስላለፈ ጥቅም ላይ እናዳይውሉ መታገዳቸውን፣ በዚህም ሳቢያ በወረዳ ማዕከላት እንዲሰበሰቡ መደረጋቸውን፣ ነገር ግን ከጤና ሚኒስቴርና ከክልሉ ጤና ቢሮ ዕውቅና ሳይሰጣቸው ‹‹ሕገወጥ በሆነ መንገድ›› ‹ፈቃድ ተሰጥቶናል› በማለት፣ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ኬሚካሎችን እያዘዋወሩ የተለያዩ አካላት እየወሰዱ መሆኑን እንደተደረሰበት ያስረዳል፡፡