Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከሕግ አግባብ ውጪ የሚፈጸሙ ድርጊቶች እንዳሳሰቡት የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ገለጸ

ከሕግ አግባብ ውጪ የሚፈጸሙ ድርጊቶች እንዳሳሰቡት የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ገለጸ

ቀን:

ባለፉት አራት ዓመታት የፍትሕ ሥርዓቱ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረገበት ቢሆንም፣ ጋዜጠኞችን በተመለከተ ከሕጉ አግባብ ውጪ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ለማስቀረት አለመቻሉ በእጅጉ እንዳሰሰበው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

ምክር ቤቱ ማክሰኞ ሚያዝያ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ውስጥ የሚሠሩ ጋዜጠኞች ከሕግ አግባብ ውጪ መያዛቸውን፣ መታፈናቸውንና የሚዲያ ተቋማትም ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ብርበራ የማካሄድ ድርጊቶች በተደጋጋሚ እንደተፈጸመባቸው ተገንዝቤያለሁ ብሏል፡፡

በሚዲያ አማካይነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ጋዜጠኞች በፖሊስ ሲያዙ ብቻ ሳይሆን፣ ፍርድ ቤት ሲቀርቡም በአዋጁ መሠረት አለመሆኑ፣  ባለሙያዎች ሥራቸውን በነፃነት እንዳይሠሩ፣ እንዲሸማቀቁና የፕሬስ ምኅዳሩ የበለጠ እንዲጠብ እያደረገው ነው ሲል ምክር ቤቱ አክሏል፡፡

በኢትዮጵያ የሚዲያ ፖሊሲም ሆነ በመገናኛ ብዙኃን፣ አዋጁ ዕውቅና ተሰጥቶት እንደተቋቋመ ያስታወሰው ምክር ቤቱ፣ ጋዜጠኞችን የሚያስጠይቅ ክስ በሚኖርበት ወቅት የእርስ በርስ ቁጥጥር ሥልት  ዘርግቶ ተግባራዊ እየተደረገ በመሆኑ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም፣  በሕግ መንግሥቱ የተረጋገጠውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሊያስከብር ይገባል ብሏል፡፡

‹‹ጋዜጠኞች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ አይጠየቁ የሚል እምነት የለኝም፤›› ያለው የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት፣ ነገር ግን ሕግ ተርጓሚው አካል (ፍርድ ቤት) ጋዜጠኞች ተከሰው ሲቀርቡ፣ በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ መሠረት መከሰሳቸው ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ በሥራ ገበታቸው ላይ ሆነው  ጉዳያቸውን መከታተል እንዳይችሉ እንደ ማንኛውም ተከሳሽ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ በመፍቀድ፣  እንዲታሰሩ ማድረግ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡

ምክር ቤቱ እንዳለው፣ መንግሥት የወንጀል ተግባራት የመከላከል፣ የመመርመርና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም፣ ተግባራቱ ሁሉ ግን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን  በማያጠብና የዜጎችን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተሳትፎ በማያቀጭጭ መንገድ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክር ቤቱ አክሎም ማናቸውም ሕግን የማስከበር ተግባራትም በሕግ አግባብ ብቻ መመራት ስላለባቸው  ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት መሠረት እንዲኖረው፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በመገናኛ ብዙኃን  አዋጁ ድንጋጌ ብቻ በመመራት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን የፍትሕ ሥርዓቱ በሕግ በተደነገገው አሠራር ብቻ የሚመሩ ስለመሆኑ፣ ለኅብረተሰቡ ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራቸውን አበክረው እንዲያከናውኑ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ጥበቃ ተሟጋች ኮሚቴ (ሲፒጄ) ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የፖለቲካ ውጥረት በነበረበት ወቅት በዘፈቀደ የታሰሩ ጋዜጠኞችን እንዲለቅቁ ጠይቋል፡፡ የፀጥታ ኃይሎች በጋዜጠኞች ላይ ባደረሱት ጥቃት ላይ ተገቢው ምርመራ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡

እ.ኤ.አ. ከሚያዝያ 3 ቀን 2023 ጀምሮ ቢያንስ ስምንት ጋዜጠኞች እንደታሰሩ በማስታወስ፣ ይህ ድርጊት በአገሪቱ የሚዲያ ነፃነት ምሥል ላይ ጥላሸት የሚቀባ መሆኑን ገልጿል፡፡ ባለሥልጣናት የታሰሩ ጋዜጠኞችን እንዲፈቱ፣ በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅት ወከባና ጥቃት በደረሰባቸው የሚዲያ ባለሙያዎች ጉዳይ ላይ ምርመራ እንዲያደርጉ ሲፒጄ አሳስቧል፡፡ ጋዜጠኞች በፍርኃት እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ ከመንግሥት ባለሥልጣናት የሚጠበቅ አይደለም ብሏል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽል በተመሳሳይ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል በእስር ላይ የሚገኙ ሰባት ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቋል፡፡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ጋዜጠኞች መካከል በአንደኛው ላይ የተሰነዘረው አካላዊ ጥቃት ምርመራ እንዲደረግበት አምነስቲ በመግለጫው አሳስቧል፡፡

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ዳይሬክተር ፍላቪያ ምዋንጎቪያ፣ ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን ሳይሸበሩ፣ ሳይዋረዱና ሙያዊ ግዴታቸውን ባከበረ መንገድ ለኅብረተሰቡ መረጃ የማቅረብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡና ባለሥልጣናትን ተጠያቂ እንዲያደርጉ ማመቻቸት ይገባል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ሦስት ወራት የሞሉትንና በመንግሥት አማካይነት በአንዳንድ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የተጣለው ክልከላ በመጥቀስ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ክልከላውን እንዲያነሱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...