በርካታ ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት የቆዳ ምርቶች ትርዒት ሊካሄድ ነው
በኢትዮጵያ የእንስሳት ዕርድ ዘመናዊ አለመሆንና የተደራጁ የዕርድ ቦታዎች በበቂ መጠን አለመኖራቸው፣ ለቆዳ አምራች ኢንዱስትሪዎች ፈተና እንደሆነባቸው የኢንዱስትሪዎች ማኅበር አስታወቀ፡፡
የዘመናዊ ዕርድ አለመኖር በሚያመርቷቸው ቆዳዎች ላይ ከጥራት ጋር በተያያዘ ተግዳሮት መፍጠሩ፣ እንዲሁም ደግሞ የአቅርቦት ሰንሰለቱ መፍረሱና ቆዳ ሰብስበው ለኢንዱስትሪዎች የሚያቀርቡ አካላት ባለመኖራቸው፣ በዘርፉ ኮሚታዩት ችግሮች ዋነኞቹ መሆናቸውን፣ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር አመራር አባላት ገልጸዋል፡፡
ማኅበሩ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ከሚያዚያ 12 እስከ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን የሚያዘጋጀውን 13ኛው የመላው አፍሪካ የቆዳ ትርዒት በማስመልከት፣ ትናንት ማክሰኞ ሚያዚያ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የማኅበሩ አመራር አባላትና የሚመለከታቸው አካላት ተወካዮች፣ በትርዒቱ ስለሚጠብቁት ውጤትና በዘርፉ ውስጥ ስላሉት ተግዳሮቶች ለሚዲያ አካላት ገለጻ አድርገዋል፡፡
የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ሰለሞን ጌቱ፣ በአገሪቱ ዘመናዊ ዕርድ በስፋት አለመለመድ፣ በተደራጀና ዘመናዊ በሆነ መንገድ ዕርድ የሚፈጸምባቸው ቦታዎች ትንሽ በመሆናቸው ችግሩ ሊከሰት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
‹‹በከተማዎች ውስጥ ካሉ ውስን ቄራዎች ውጪ 90 በመቶ የሚሆነው ማኅበረሰብ ባህሉንና ሃይማኖቱን መሠረት አድርጎ በቤቱ ነው የሚያርደው፤›› ያሉት አቶ ሰለሞን፣ ኢንዱስትሪዎቹም ግንዛቤ ባለማስጨበጣቸው በዕርድ ወቅት በቢላ የተቀዳደዱ ቆዳዎች እየቀረቡላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢንዱስትሪዎች ከማኅበረሰቡ ቆዳ እንዳይሰበስቡ በሕግ በመከልከላቸውና ሰብስበው ለእነሱ የሚያቀርቡ አካላት ደግሞ ከገበያ በመውጣታቸው፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ተቋርጦ እንደነበር አቶ ሰለሞን ጠቁመው፣ በዚህም ምክንያት አምራቾች በውድ ይገዙ እንደነበርና አሁን ግን በዓሉን በማስመልከት ለሦስት ወራት ተፈቅዶላቸው ከማኅበረሰቡ እየሰበሰቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹እኛ ገብተን ስናየው ሰሞኑን ከሰበሰብናቸው ቆዳዎች በቢላ የመቀደድና ቅርፅ የማጣት ትልቅ ችግር ነው የገጠመን ግንዛቤ ባለመፈጠሩ ምክንያት ትልቅ ሀብት ስናባክን ያሳዝናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎች ራሳቸው ቆዳዎችን በመሰብሰባቸው፣ አቅርቦቱ በርካታ እንደሆነ መታወቁን፣ ከዚህ በመነሳት በበዓላት ወቅት ብቻ የዓመቱን እስከ 30 በመቶ ፍላጎት እንደሚያሟሉ የማኅበሩ አመራሮች ገልጸዋል፡፡
ቆዳን በጥራት ከማቅረብ ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን የሰጡት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሬድዋን በዳዳ፣ ችግሩ በውጪ ንግድ ላይ ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱን አክለው ገልጸዋል፡፡ የአገሪቱ ቆዳ ተመራጭነት ከዓመት ዓመት ሊወርድ እንደሚችል አቶ ሬድዋን ተናግረዋል፡፡
‹‹የማኅበረሰቡ ግንዛቤ ማደግ አለበት፣ ከብት ወዲያው ታርዶ ወዲያውኑ ወደ መጋዘን መጫንና ጨው ማግኘት አለበት፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹እኛ ብቻችንን ልንሠራው ስለማንችል የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
የጫማ አምራቾችን፣ የተለያዩ የቆዳ ውጤት አምራቾችንና ቆዳ ማልፋትና ማለስለስ ላይ የሚሠሩ 189 ኢንዱስትሪዎች በአባልነት የያዘው የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር፣ ከተለያዩ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን የመላው አፍሪካ የቆዳ ትርዒትን በሚሌኒየም አዳራሽ እንደሚያካሂድ ተገልጿል፡፡
በትርዒቱ ላይ ለመሳተፍ ከ33 የአፍሪካ አገሮች ትርዒት አቅራቢ አምራቾች መምጣታቸውን የገለጹት የማኅበሩ አመራሮች፣ ከ200 በላይ አምራቾች እንደሚካፈሉበትም ገልጸዋል፡፡
ትርዒቱ እ.ኤ.አ. በ2008 ከተጀመረ ወዲህ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ 12 ጊዜ ማካሄዱን፣ በዚህ ዓመት 13ኛውን ትርዒት በማካሄድ ከ15 ሺሕ በላይ ጎብኚዎች እንደሚገኙ አቅዶ ማኅበሩ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አስረድቷል፡፡