Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለሚሄዱ 36 ሺሕ ሥራ ፈላጊዎች ሥልጠና መጀመሩ ተነገረ

ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለሚሄዱ 36 ሺሕ ሥራ ፈላጊዎች ሥልጠና መጀመሩ ተነገረ

ቀን:

ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚላኩ 36 ሺሕ የመጀመርያ ዙር ሥራ ፈላጊዎች ካለፉት ሦስት ሳምንታት ጀምሮ ሥልጠና መጀመሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በመጀመርያው ዙር የሚላኩት በቤት ሠራተኝነት ሙያ የሚሰማሩ ሥራ ፈላጊዎች ናቸው ብሏል፡፡ ሠራተኞቹ በሁለቱ አገሮች የጋራ ስምምነት መሠረት በ1000 የሳዑዲ ሪያል (በወቅቱ ምንዛሪ 14,531 የኢትዮጵያ ብር) የመነሻ ደመወዝ እንደሚቀጠሩ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

ወደ ሳዑዲ የሚሄዱት ሥራ ፈላጊዎች ለኤጀንሲም ሆነ ለደላላ ምንም ዓይነት ክፍያ መፈጸም የለባቸውም ተብሏል፡፡ በሕገወጥ ደላሎችና አግባብ በሌላቸው ኤጀንሲዎች መበዝበዝ እንደሌለባቸው ሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸው፣ ሥራ ፈላጊዎቹ እ.ኤ.አ. በ2019 በሳዑዲ ዓረቢያና በኢትዮጵያ መካከል በተደረገ የጋራ ስምምነት መሠረት እንደሚላኩ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹የመጀመርያ ዙር 36 ሺሕ ሥራ ፈላጊዎች በአገሪቱ ባሉ የቴክኒክና የሙያ ሥልጠና ተቋማት ገብተው ቋንቋ፣ አፕቲቲዩድ (ጠቅላላ ዕውቀት) እና የሙያ ሥልጠና እየተሰጣቸው ነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ ሁለተኛና ሦስተኛ ዙር ሠልጣኞች ይገባሉ፤›› ብለዋል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ 500 ሺሕ ሥራ ፈላጊዎችን ከኢትዮጵያ ለመውሰድ ፍላጎት አላት ተብሎ በመዘገብ ላይ ስላለው ጉዳይ የተጠየቁት አቶ አሰግድ፣ ‹‹እሱ የእነሱ ሠራተኛ ፍላጎት ሊሆን ይችላል፡፡ በእኛ በኩል ግን ይህን ያህል ማለት ይከብደናል፡፡ ቁጥሩ የሚወሰነው በተመዘገበውና ሠልጥኖ በተዘጋጀው ሰው ነው፡፡ ለማንኛውም ቁጥሩ ከፍ ያለ ሥራ ፈላጊ ለመላክ እየሠራን ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሳዑዲዎች በኩል ከቤት ሠራተኞች በተጨማሪ በሹፍርና፣ በኮንስትራክሽንና በሌሎችም የሙያ ዘርፎች ኢትዮጵያን ጨምሮ ከብዙ የዓለም አገሮች ሠራተኛ ለመውሰድ እንቅስቃሴ መኖሩ ታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 የሳዑዲ ሠራተኛና ማኅበራዊ ልማት ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው (www.musaned.com.sa) በተባለው ከዓለም ዙሪያ ሠራተኛ የመመልመያ ድረ ገጹ ላይ ሥራ ፈላጊዎች የጉዞና የቅጥር አገልግሎቶችን በመረጃ ድረ ገጽ መጨረስ እንደሚችሉ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ይህን በተመለከተ ከሳዑዲው የኦንላይን ሠራተኛ መመልመያ ገጽ ጋር የሚናበብ ድረ ገጽ በኢትዮጵያ እየበለፀገ መሆኑን ነው አቶ አሰግድ የተናገሩት፡፡ ሥራ ፈላጊዎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የመመልመያ ሥርዓት ከመዘርጋት ባለፈም፣ የአሠልጣኞች ሥልጠና መካሄዱን ሚኒስትር ደኤታው ገልጸዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በአሁኑ ጊዜ ሳዑዲ ዓረቢያ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2019 በተፈረመው ስምምነት መሠረት የኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች መነሻ ደመወዝ ከ1000 የሳዑዲ ሪያል ጀምሮ እንዲሆን የተደረገው ስምምነት፣ አሁን ባለው የወቅቱ የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ በቂ እንዳልሆነ ለሳዑዲ ባለሥልጣናት እንደተነገራቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያውያን ደመወዝ መጠን የጋራ ስምምነቱ በሚሻሻልበት ወቅት አብሮ እንደሚሻሻል የተናገሩት አቶ አሰግድ፣ የሠራተኞች አያያዝ ሁኔታ ላይም መሻሻል መኖሩን አስረድተዋል፡፡

ሥራ ፈላጊዎች ፈቃድ በተሰጣቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሚያውቃቸው ኤጀንሲዎች በኩል እንዲሄዱ ያሳሰቡት አቶ አሰግድ፣ ከዚህ ውጪ ግን የሚከፈል ገንዘብ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዜጎች ጥሪት አራግፈውና በሕገወጥ ሠራተኛ ላኪዎች ተበዝብዘው ወደ ውጭ ለመሄድ መሞከር የለባቸውም፤›› ሲሉ ያሳሰቡት ሚኒስትር ደኤታው፣ የፓስፖርትና የጤና ምርመራ ወጪ ካልሆነ በስተቀር ዜጎች የሚጠየቁት ክፍያ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ከ1000 የሳዑዲ ሪያል በታች በሆነ ደመወዝ ላስቀጥር የሚሉ ኤጀንሲዎች ሕገወጥ መሆናቸውን ያስታወቁት ባለሥልጣኑ፣ የሠራተኛን ደመወዝ ልቀናንስ የሚሉ በመረጃ ቋቱ ስለሚታወቁ ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...