በአገር አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጎጂዎች የካሳ ፈንድ እንዲቋቋምና ተቋማዊ ቅርፅ የሚይዝበት አሠራር እንዲጀመር፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ትናንት ሚያዚያ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በድረገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጎጂዎች ስለሚሰጥ ድጋፍ፣ ማካካሻና የመፍትሔ አማራጮች ላይ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚፈጽሙ ሰዎችን የሕግ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ከዚህ ጎን ለጎን ተጎጂዎች በቂ ካሳና ማካካሻ እንዲያገኙ ማድረግና የመብት ጥሰቱ እንደማይደገም ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
ዳንኤል (ዶ/ር) አክለውም፣ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ለሰብዓዊ መብቶች ተጎጂዎች የገንዘብ ካሳ የመክፈል በጎ ጅምሮች የታዩ ቢሆንም፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጎጂዎች የካሳ ፈንድ ማቋቋምና ተቋማዊ ቅርፅ የሚይዝበትን አሠራር ከወዲሁ መጀመር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂዎች ስለሚሰጡ ድጋፎች ዓለም አቀፍና አገራዊ የሕግ ማዕቀፎች፣ እንዲሁም የሌሎች አገሮች ተሞክሮን የሚዳስሱ ጽሑፎች መቅረባቸውን ኢሰመኮ ገልጿል፡፡ የውይይቱ ዋና ዓላማም በኢትዮጵያ ወደፊት ተግባራዊ ለሚደረገው የሽግግር ፍትሕ ሒደት ግብዓት መስጠት ነው ብሏል፡፡
ኢሰመኮ የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር ባካሄዳቸው ምክክሮች የተሰበሰቡ ዋና ዋና ግኝቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ በጽሑፉም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጎጂዎች መፍትሔ የማግኘት መብትን በተመለከተ፣ በኢትዮጵያ በንብረት መብትና በሠራተኛ መብቶች ላይ ለደረሱ ጥሰቶች ካሳ ለማግኘት የተሻለ የሕግ ማዕቀፍና አፈጻጸም መኖሩ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በወጣው አዋጅና በፀረ ሽብር አዋጁ፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና በሽብር ተግባራት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸው ተጎጂዎች ካሳ የማግኘት መብት እንዳላቸው የተደነገገ ቢሆንም፣ ተፈጻሚነታቸው ክፍተት እንዳለበት መገለጹን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም የሕገወጥና የዘፈቀደ እስራት፣ እንዲሁም የማሰቃየትና የጭካኔ ተግባራት ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎችን፣ የካሳ መብት ለማረጋገጥ ሁሉን አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩንና ያሉትም ጥቂት የሕግ አንቀጾች ተፈጻሚነታቸው ውስን እንደሆነ፣ በውይይት መድረኩ ላይ በቀረበው መነሻ ጽሑፍ መመላከቱ ተጠቁሟል፡፡
ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (OHCHR) ጋር በመተባበር በአፋር፣ በሶማሌ፣ በሐረሪ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ ምክክር አካሂዶ፣ መሪ ሰነድ ይፋ ማድረጉ እንደሚታወስ፣ የማኅበረሰብ ተወካዮቹ በአጽንኦት ካነሷቸው ሐሳቦች መካከል በሽግግር ፍትሕ ሒደቱ የማኅበረሰብ ተሳትፎ ሊረጋገጥ እንደሚገባ፣ ተጎጂዎች ካሳ ማግኘትና ወደ ቀደመ ሕይወታቸው መመለስ እንዳለባቸው የሚጠቀሱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ ክፍል 19፣ የሽግግር ፍትሕ አንድ ማኅበረሰብ ለደረሰበት መጠነ ሰፊ ጉዳቶች፣ ወይም ለደረሱ ቆየት ያሉ ታሪካዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ጥልቅ ክፍፍሎችና መራራቅ ኢእኩልነትን ለማረቅና መፍትሔ ለመስጠት የሚካሄዱ መደበኛ ወይም መደበኛ ያልሆኑ ሒደቶችና መዋቅሮች ናቸው በሚል ጠቅለል አድርጎ ይገልጸዋል።
ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትሕ እርስ በርሳቸው የሚደጋገፉና የሚዛመዱ አራት ዋና ዋና ሒደቶችን የያዘ እንደሆነ የሚያትተው የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ፣ እነዚህም እውነትን ማረጋገጥና ይፋ ማድረግ፣ ተጠያቂነት፣ ለተጎጂዎች ምሉዕ ካሳና መቋቋም ማስገኘት፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዳግም እንደማይፈጸሙ ተጨባጭ ማረጋገጫ ማቅረብ ናቸው ይላል።