Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበፋሲካው ምድር

በፋሲካው ምድር

ቀን:

ዛሬ በዕለተ ሰንበት ሚያዝያ ስምንት ቀን ሁለት ሺሕ አሥራ አምስት ዓመተ ምሕረት፣ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖችና የጁሊያን ካሌንደርን የሚከተሉ የምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን፣ ፋሲካ የሚባለውን የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓልን እያከበሩ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት የሆሳዕና (የዘንባባ እሑድን) ኦርቶዶክሳውያን ሲያከብሩ የግሪጎሪያን ካሌንደርን የሚከተሉት የምዕራቡ ዓለም ክርስቲያኖችና የተወሰኑ ኦርቶዶክሳውያን ፋሲካቸውን ማክበራቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ የምትገኝበት የኦሬንታል ኦርቶዶክስ ተከታዮችና እነ ሩሲያ የሚገኙበት የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ተከታዮች እንደየ ሥርዓታቸው ፋሲካውን እያከበሩ ነው፡፡ ሳምንቱንም በልዩ ልዩ መንፈሳዊ መሰናዶዎች እያከበሩ ይዘልቁታል፡፡

“ፋሲካ” የሚባለው ትንሣኤ፣ በፀደይ ወቅት (በኢትዮጵያ መጋቢት 26 ቀን የገባው) ከምትታየው የመጀመርያዋ ሙሉ ጨረቃ (ሚያዝያ 1 ቀን ታይታለች) በኋላ የሚከበር ነው፡፡ ትንሣኤ እግዚእ ኢየሱስ ተሰቅሎና ሙቶ፣ ከሙታንም ተለይቶ የተነሳበትን ዕለት ያመለክታል፡፡ የተሰቀለውና የሞተውም በአይሁድ ፋሲካ (ፍሥሕ) ጊዜ ሲሆን፣ የተነሳውም ከአይሁድ ፍሥሕ በኋላ በመጀመሪያው እሑድ ነው፡፡

የአይሁድ ፋሲካ ሁልጊዜ የሚወለው በፀደይ ወቅት የመጀመርያ ሙሉ ጨረቃ በሚታይበት ዕለት ነው፡፡ የዚህም ማስረጃው በኦሪት እንደሚከተለው ተጽፏል፡- “በመጀመርያው ወር ሲመሽ በአሥራ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው፡፡” በዚህ መሠረት የአይሁድ መጀመርያ ወር የተባለው ‹ኒሳን› ሲሆን ይህም የጨረቃ ሚያዝያ ማለት ነው፡፡

በፋሲካው ምድር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የፋሲካ ቀመር ለምን ተለያየ?

የፋሲካ (ትንሣኤ) በዓል አከባበር በአቆጣጠር ልዩነት የተነሣ ከ16ኛው ምእት በኋላ ምሥራቆችና ምዕራቦች ከመለያየታቸው በፊት ከ326 እስከ 1582 ድረስ በ325 በተካሄደው ኒቅያ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ክብረ በዓሉ በተመሳሳይ ቀን ይውል ነበር፡፡ 

በዓሉ ምንግዜም ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12፣ 12 ሰዓት ከሚሆንበት መጋቢት 25 (በጁሊያን ማርች 21) በኋላ፣ ከአይሁድ ፍሥሕ (ፋሲካ) በኋላ፣ ባለው እሑድ ሁልጊዜ እንዲውል ይደነግጋል፡፡ ከጥቅምት 1575 ዓ.ም. (1582) በኋላ የጁሊያን አቆጣጠርን ያሻሻለው የጎርጎርዮስ ቀመር በአብዛኛው የአውሮፓ ካቶሊኮች ተቀባይነት በማግኘቱና በተፈጠረው የቀናት መሳሳብ ሌላ የትንሣኤ በዓል ሊፈጠር ችሏል፡፡ 

የኦርቶዶክስ ፋሲካ የጁሊያንን ቀመር፣ ኢትዮጵያና ኮፕት ደግሞ በራሳቸው ቀመር የኒቅያውን ድንጋጌ ይዘው በመዝለቃቸው ክብረ በዓሉን በአንድ ቀን ያከብራሉ፡፡ በኢትዮጵያና በኮፕት ባሕረ ሐሳብ መሠረት የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ዓርብ መጋቢት 27 ቀን፣ ትንሣኤው እሑድ መጋቢት 29 ቀን 34 ዓ.ም. የዋለ ሲሆን፣ በየዓመቱ እነዚህ ዕለታት  የስቅለት መነሻ፣ የትንሣኤ መነሻ ተብለው ይታሰባሉ፡፡

ትንሣኤን ተከትለው ቀናቸው በየዓመቱ የሚዘዋወሩት ጾሞችና በዓሎች የአወጣጥ ሥርዓት መደበኛውን ፀሐያዊ አቆጣጠር ሳይሆን የፀሐይና ጨረቃን ጥምር አቆጣጠር (ሉኒ-ሶላር) ይከተላል፡፡ ይህም በመሆኑ ትንሣኤ በመጋቢት 26 እና በሚያዝያ 30 መካከል ባሉት 35 ቀናት ውስጥ ይመላለሳል፡፡ 

ጥንታዊ መጽሐፍ ፍትሐ ነገሥት በፍትሕ መንፈሳዊ ክፍሉ ስለ ትንሣኤ በዓል አከባበር እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹… የትንሣኤውን በዓል በዕለተ እሑድ እንጂ በሌላ ቀን አታድርጉ፤ በመንፈቀ ሌሊት ብሉ፤ ያም ባይሆን በነግህ ብሉ. . . ከዚህም በኋላ ፈጽሞ ደስ እያላቸሁ ጾማችሁን በመብል በመጠጥ አሰናብቱ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና፡፡››

በዓሉና ባህሉ

በዓሉ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች መሠረተ እምነቱን ይዘው እንደየባህላቸው ያከብሩታል፡፡ የቅርስ ባለሥልጣን የፎክሎርና የሥነ ሰብእ (አንትሮፖሎጂ) ባለሙያዎች ባዘጋጁት የማይዳሰሱ የባህላዊ ቅርሶች መድበል ውስጥ እንደተጠቀሰው፣ በደቡብ ክልል ሸካ ዞን የሚገኙት ሸከቾዎች ፋሲካን በራሳቸው ባህላዊ መለያ ያከብሩታል፡፡ በዓሉ ሐሙስ የሚጀምር  ሲሆን ዕለቱ ‹‹ዳጲ ማዮ ማዮ›› ይባላል፡፡ ይህም የንፍሮ ቀን ማለት ሲሆን፣ ቀኑን በጾም በማሳለፍ ወደማታ የሚበላው ምግብ ንፍሮ ብቻ ነው፡፡

የስቅለት ቀን የሚባለው ዓርብ ‹‹አኪላቶስ›› ሲባል በዚህ ቀን በተለይ እናቶች ቀኑን በልዩ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡ እናቶች ጠንካራ የፈትል ገመድ አዘጋጅተው የሁለቱን እጃቸውን ክንድ ባንድ ላይ የኋሊት በማሰር ይውላሉ፡፡ ወደማታ ሲሆን እጃቸውን ከፈቱ በኋላ በሠፈሩ ያሉ ሴቶች በኅብረት ‹‹ዮዲ›› በሚባል በደንና በዕፀዋት በተከበበና በተከበረ ቦታ በመሰባሰብ ቅጠል አንጥፈው ድምፃቸውን ከፍ  አድርገው ዘለግ ባለ ድምፀትና ተመስጦ ‹‹እቶማራማራ እቶስ›› ‹‹ዮሻ ዮሻ ኢቶስ›› እያሉ ለረዥም ሰዓታት ይሰግዳሉ፡፡ ‹‹መሐሪ የሆነው ክርስቶስ ተይዞ ለሞት ተሰጠ›› የሚል ትርጉም ያለው ነው፡፡

ስለ ሸካቾ ብሔረሰብም እንደሚከተለው ያትታል፡- ‹‹በስቅለት ዕለት (ዓርብ) ምዕመናኑ ሙሉ ቀን ጹመው ‹የሺ-ቅቶሶች›ን ይለምናሉ፡፡ ‹የሺ-ቅቶሶች› ማለት ከሥረ መሠረቱ ከእኛ ጋር ያለን ጌታ፤ ተይዞ ለእኛ የተሰቀለው፤ ለእኛ ብሎ የሞተ፤…›› የሚለውን ቃል ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም የጸሎት አዝማቹ ‹‹እቶ ማራማራ እቶስ!›› የሚለውም የክርስቶስ ተከታዮችን ያመለክታል፡፡  

እሑድ ፋሲካ ወይም የዋናው ማዲካም ዕለት በመሆኑ ከብት ይታረዳል፤ እናቶች ገሪግዮ በሚባል ጎምዛዛ ቅጠል አፋቸውን አራት ጊዜ ‹‹ጮሚበቾ›› በማለት ካበሱ በኋላ መመገብ ይጀምራሉ፡፡

ሸከቾች በዓመት ውስጥ ካሉት ወራት የሦስቱን ስያሜ በተለይ ከሁዳዴና ፋሲካ ጋር ያያይዙታል፡፡ የካቲት፡- ‹‹መዴጉፓ›› የሁዳዴ ጾም በየካቲት ወር ስለሚጀምር፣ እስካሁን በቅበላ ቆይተሃልና ገበታህን አጥበህ ድፋው ወይም ጾም ጀምር የሚል አንድምታ ያለው ነው፡፡ መጋቢት፡- ‹‹ገኤውቆ›› የጾም እኩሌታ የሚደርስበት ወር በመሆኑ በርታ እንደማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የደብረ ዘይት በዓል የሚከበርበት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሚያዝያ፡- ‹‹መካሞ›› ጾም ልትፈታ ነው፡፡ ስለዚህ ተደፍቶ (ተቀምጦ) የከረመውን ገጽታህን ቀና አድርገህ ጾምህን ፍታ፣ የፋሲካ በዓልን አክብር ማለት ነው፡፡ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም አከባበሩ ጉልህ ይሆናል፡፡

ከትንሣኤ በፊት ያሉት ሰሙነ ሕማማትና ዓርብ ስቅለት በተለይ በጾምና በስግደት የሚከበሩ ናቸው፡፡ በወይራ ቅጠል ጥብጠባ በማሳረጊያው ይደረጋል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ሥርዓት መሠረት ከሆሳዕና ሰኞ (እሑድ ሌሊት) እስከ ጸሎተ ሐሙስ ያሉት ቀናት ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበሩትን 5500 ዓመታት (አምስት ተኩል ቀናት) “የዓመተ ፍዳ” መታሰቢያ ሆነው ተሠርተዋል፡፡ 

መምህር ካሕሣይ ገብረእግዚአብሔር ‹ኅብረ ብዕር› በተሰኘው መጽሐፋቸው የፋሲካ በዓልን ከሰሙነ ሕማማት ጋር አያይዘው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ድርጊቶችን እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡ 

‹‹በወሎና በጎንደር ከጉልባን በተጨማሪ በተለይ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ብቻ የሚጋገር የተለየው ዳቦ በወሎ ‹ትኩሴ›፣ በጎንደር ደግሞ ‹ሙገራ› ይባላል፡፡ ይህ ዳቦ ጌታ ለሐዋርያት የሰጣቸውን ኅብስት አምሳያ ነው ተብሎ ስለሚታመንበት ከዚህ ቀን ውጭ በሌላ ጊዜ አይጋገርም፣ በመሆኑም ሰው ሁሉ ዳቦውን ለመብላት የሚጠባበቀው በታላቅ ጉጉት ነው፡፡

‹‹በቅዱስ ላሊበላ አጠገብ በሚገኘው የይምርሐነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ጣርያ ካህኑ ‹የትኩሴ ዳቦ› ሲባርክ የሚያሳይ ሥዕል (ቅርፅ) አለ፡፡ ይህ ምን ያህል ክቡርና ቅዱስ መሆኑን አመልካች ነው፡፡

‹‹በትግራይ በዕለተ ስቅለት ከተለመደው የጾምና የስግደት ሥነ ሥርዓት በተጨማሪ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ የዕለቱ ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት መታሰቢያ ሲባል ወንዶች ልጆች በሙሉ ፀጉራቸውን እንዲላጩ ይደረጋል፡፡ ልጃገረዶች በበኩላቸው በዛፍ ላይ ገመድ በማሰር ዥዋዥዌ ይጫወታሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት የጌታን መስቀል ለማዘከር ነው ይባላል፡፡ ጎረምሶች ደግሞ ስቅለትን ጨምሮ በሰሙነ ሕማማት ቃርሳ (ገና) ይጫወታሉ፡፡ ይህም ምሳሌነቱ የጌታን መንገላታት፣ ወድቆ መነሳትን ለማሰብ ተብሎ የሚፈጸም ድርጊት  ይላሉ መምህር ካሕሣይ፡፡

የፋሲካው ምግብ

በእሑድ ፋሲካ ዋዜማ ቀዳም ሥዑር (ቅዳሜ ሹር) ቄጠማ እየታደለ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ወአግሀደ ትንሣኤሁ” (በመስቀሉ ሰላምን አደረገ፣ ትንሣኤውም ግልጽ ሆነ) ተብሎ ይከበራል፡፡ ምሽት ላይ ምዕመናን ወደየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው ጧፍና ሻማ በመያዝ በምሥራቹና በሥርዓተ ቅዳሴው ለመካፈል የሚጓዙበት ነው፡፡ እስከ መንፈቀ ሌሊት ይቆያሉ፣ በፋሲካ ሌሊት የምሥራቹን ጧፍና ሻማ በመለኮስ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የሚደረገው ዑደት “ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ” (ትንሣኤህን ላመንን ለእኛ ብርሃንህን ላክልን)  ‹‹ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ክርስቶስ›› (ምድር ፀዳች ሐሴት አደረገች፤ በክርስቶስ ደም በእውነት ታጠበች) በሚለው ዝማሬ የታጀበ ነው፡፡

 ሁሉም ዶሮ ሲጮህ ይፈስካሉ፡፡  ለምዕመናኑ በመንፈሳዊ እርሻ የተመሰለው ሁዳዴው ሲጀመር፡-

“ጀግናው ዓቢይ ጾም ቢታይ ብቅ ብሎ፣

ቅቤ ፈረጠጠ አገር ርስቱን ጥሎ” ተብሎ በቃል ግጥም የታጀበው ጾም ሲፈታ፣ በተለይ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ከቅባት የተለየው አካል እንዳይጎዳ ልዩ ምግብ ይዘጋጅለታል፡፡ ማለስለሻ እንዲሆን ተልባ ይቀርባል፡፡ በጸሎተ ሐሙስም ለየት ያለ የምግብ ባህል አለ፡፡ ጸዋሚዎቹ ጉልባንና ንፍሮ ቀምሰው እስከ ትንሣኤ ሌሊት ሳይመገቡ ያከፍላሉ፡፡ ጉልባን ባቄላ፣ ስንዴና ጥራጥሬ ተቀላቅሎበት የሚዘጋጅ የምግብ አይነት ነው፡፡ ዓርብ ስቅለት ከስግደት መልስም ጉልባን ይበላል፡፡ የሐዘን መግለጫ ሆኖ ተወክሏል፡፡

እንደየኅብረተሰቡ ባህል የፋሲካ ድፎ ዳቦ፣ ዶሮ ዳቦ፣ ኅብስት፣ የዶሮ ወጥ እንቁላል፣ የዕርድ ከብቶችን ማዘጋጀት ጠጅና ጠላ መጠጥ ማዘጋጀት የክብረ በዓሉ አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ከመልካም ምኞቱ ‹እንኳን አደረሳችሁ›፣ ‹ጾመ ልጓሙን እንኳን ፈታልዎ› በአነጋገር ደረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከርቀትም ሆነ ከቅርበት ያሉ ቤተሰቦች የሚሰባሰቡበት ስጦታ ሙክት፣ ድፎ ዳቦና መጠጦችም የሚለዋወጡበት ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...