Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ንፁህና ሰላማዊ ህሊና!

ሰላም! ሰላም! ውድ ወገኖቼ በሙሉ፡፡ እንዲሁም ለመላ የክርስትና እምነቶች ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሳዔው አደረሳችሁ፡፡ አገር ሰላም ሆና ሕዝባችን ተደስቶ የሚኖርበት ጊዜ እንዲመጣ ለሁላችሁም እመኛለሁ፡፡ እኔም ብሆን የድለላ ሕይወቴ ነፍስ የሚዘራው ሰላም ኖሮ ሰዎች በነፃነት ወዲህና ወዲያ እያሉ ሲሠሩና ገንዘብ ሲንቀሳቀስ ነው፡፡ አንዱ ደላላ ወዳጄ በቀደም ዕለት ዕድላችንን የሚያመጣልንን ሥራ ስንጠባበቅ፣ ‹‹አቶ አንበርብር ደሃ አገር ውስጥ በዓላት በዝተው የሥራ ቀናት መሆን የሚገባቸው ሲባክኑ በጣም ያሳዝነኛል…›› ሲለኝ ሌላው ደላላ ወዳጃችን፣ ‹‹ወዳጄ በዚህ ዘመን ምን ቀኑ በበዓል ዝግ ቢሆንም፣ የሥራ ሰዎች ግን ሁሌም ሥራ ላይ ናቸው፣ ገንዘባቸውም በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ይንቀሳቀሳል…›› ብሎ ገላገለኝ እንጂ እኔማ መልስም አልነበረኝም፡፡ አንዳንዱ በርቀትም ሆነ በምሽት ክፍለ ጊዜ ወጥሮ እየተማረ ራሱን ከጊዜው ጋር እኩል የሚያራምድበት ጥንካሬው ድንቅ ሲለኝ፣ የእኔ ቢጤዎች ደግሞ ከቡና ረከቦት ዙሪያ እስከ ግሮሰሪ ባንኮኒ ድረስ የምናጠፋው ጊዜና ገንዘብ ግርም ይለኛል፡፡ በዚህ ላይ መያዣ መጨበጫ የሌለው ወሬ፣ ሐሜት፣ አሉባልታ፣ ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ ሲታከልበትማ ድንቁርናችን ለከት እያጣ ያበሳጨኛል፡፡ ወይ ነዶ!

በበዓል ሰሞን ገበያ ብቅ ማለት አይቀሬ ነው፡፡ ታዲያ በቀደም ዕለት አንዲት እናት በስስት እቅፋቸው ውስጥ የያዟትን ዶሮ ከሾላ ገበያ ገዝተው ሲመለሱ፣ ‹‹ማዘር ይህችን ዶሮ ስንት ገዟት?›› ብሎ አንዱ ሞቅ ያለው ጎረምሳ ይጠይቃቸዋል፡፡ ‹‹ልጄ እንዲህ ሆነህ የገዛሁበትን ዋጋ ብነግርህ አይጠቅምህም…›› ብለውት ሲያልፉት፣ ‹‹እውነትዎን ነው እማማ ባልሰማ ይሻላል፡፡ ዋጋውን ቢነግሩኝ የበለጠ ራሴን ያዞረዋል…›› ሲላቸው ቆም ብለው፣ ‹‹አንተንስ መጠጡ ሳይሆን ኑሮው ነው መሰል በልጅነትህ ያንጀባረረህ እንጂ፣ የችግሩ ፅናት ገብቶሃል…›› እያሉ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ከብዙ ዓመታት በፊት ተመሳሳይ ቀልድ መስማቴን አስታውሳለሁ፡፡ ለትንሳዔ በዓል በግ ለመግዛት ሾላ በግ ተራ የደረሱ እናት ዓይናቸው ውስጥ የገባ መለስተኛ ሙክት ዋጋ ሲጠይቁ፣ ‹‹350 ብር ወዲህ ይበሉ…›› ብሎ ሻጩ ዋጋውን ይነግራቸዋል፡፡ እሳቸው 350 ብር ያወጣል የተባለውን መለስተኛ ሙክትና ሻጭ በትዝብት እያዩ፣ ‹‹ምነው አሁንስ አልበዛም እንዴ? መንግሥት በአገሩ የለም እንዴ?›› እያሉ በንዴት ሲንገፈገፉ፣ ‹‹እማማ ይግዙት በጣም ርካሽ ነው…›› እያለ አንድ ወፈፌ ጣልቃ ሲገባ፣ ‹‹አይ ልጄ እኔን… እኔን… ዘንድሮስ ከእኛ አንተ ሳትሻል አትቀርም…›› ያሉት ትዝ ብሎኝ ከት ብዬ ሳቅሁ፡፡ ውስጤ እያረረ ልሳቀው እንጂ!

አንድ ደንበኛዬ ለበዓል ከውጭ የሚመጡ ዘመዶቹንና ወዳጆቹን ለማስተናገድ ጠብ እርግፍ ሲል ነው የከረመው፡፡ የተለያዩ ቦታዎች ሲሄድ እንዳግዘው ብሎ ይዞኝ ሲዞር ነው የሰነበተው፡፡ ከአንዱ ሞል ወደ ሌላው እየዞርን ውድ የሳሎን ጌጦችና ቁሳቁሶችን፣ አሉ ከሚባሉ አስመጪዎች ውድ የአልኮል መጠጦችን (ብሉ፣ ግሪንና ጎልድ ሌብል ውስኪዎች፣ ሲንግል ማልት ውስኪዎች፣ የተለያዩ ቮድካዎች፣ ምርጥ ኮኛኮች፣ የኤክሶ ዘር መበተኛዎች፣ የአውሮፓ ወይኖች፣ ወዘተ) እና ለበዓል ማዳመቂያዎችን ሲሸምት ዋጋዎቹን በአዕምሮዬ ለማስላት ከፍተኛ ትግል ነበር የገጠመኝ፡፡ እኔና ማንጠግቦሽ በቀን ሦስቴ ጠግበን እያገሳን ለአምስት ዓመት ያህል የምንበላው ምርጥ ምግብ ብናገኝ፣ ደንበኛዬ ከላይ ለዘረዘርኳቸው ነገሮች ያወጣውን ወጪ ሩቡን የምንፈጅ አልመስልህ ሲለኝ ነበር፡፡ ‹‹ዕድሌ ጠማማው…›› የሚለውን ዘፈን በለሆሳስ ባልበላ አንጀቴ እያንጎራጎርኩ የዘመናዮችን መንደር ሳስስ አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ልጅ አንበርብር እያንዳንዳችን ከእናታችን ማህፀን ስንወጣ ጀምሮ ነው የዕድላችን ሰሌዳም አብሮ የተጻፈው…›› ያሉኝን ሳስታውስ አቃረኝ፡፡ ምሁሩ ልጃቸው ደግሞ በአንድ ወቅት፣ ‹‹በፊት ዕድል እንዳለ አላምንም ነበር፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ 95 ፐርሰንት ዕድል፣ አምስት ፐርሰንት ብቻ ጥረት በቂ መሆኑን ተረድቻለሁ…›› ያለኝ ትዝ ሲለኝ ደግሞ ከመተከዝ ውጪ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ እንዲያ መሰለኝ ነገሩ!

እኔን ሁሌም ግርም የሚለኝ ምን መሰላችሁ? የዚህ ዘመን አነቃቂዎቻችን በጣም ብዙ የጥረት መንገዶችን ሲነግሩን ለምን ይሆን የዕድልን ነገር እንደ ዋዛ የሚያልፉት? ለምሳሌ አንድ ሥራ ለመጀመር ሥልጠና፣ ከዚያም ዕቅድ፣ ትጋት፣ የገበያ ጥናት፣ ፋይናንስ፣ ቀጥሎም ኔትወርክ ማስፋት፣ ወዘተ፣ ወዘተ እያሉ በርካታ ነገሮችን ይዘረዝራሉ፡፡ ጥርሱን ነክሶ ለመሥራት ታጥቆ ለተነሳ መልካም ሊሆን እንደሚችል ይገባኛል፡፡ ግን፣ ነገር ግን እኔን የማይገባኝ ይህን ሁሉ ገንዘብ ሰብስቦ ሕንፃ እንደ ችግኝ የሚተክለው፣ ውድና ቅንጡ መኪኖችን እንደ ሸሚዝ እየቀያየረ የሚነዳው፣ በር ዘግቶ በአንድ ምሽት በመቶ ሺዎች  ሲበትን የሚያድር ሁሉ የጥረት ወይም የላብ ውጤት ነው ቢሉኝ ለመቀበል ያዳግተኛል፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ሳይቀባበሉ ወይም ሳያቀባብሉ ሚሊየነር መሆን የማይቻልባት አገር ውስጥ በልፋት ሀብት ይገኛል ቢሉኝ፣ አስማት ካልሆነ በስተቀር ፈፅሞ የማይሞከር ብቻ ሳይሆን የማይታሰብ ጭምር ነው…›› የሚል አቋሙን የማውቅ ከመሆኔም በላይ፣ እኔም በድለላዬ ሕይወቴ የተገነዘብኩት ስለሆነ አቋሙን እጋራለሁ፡፡ አንዱ ጎረምሳ በአንድ ጊዜ አምስት ሲኖትራኮች መግዛት ፈልጎ በጥቆማ እኔ ዘንድ ይመጣል፡፡ በጨዋታ መሀል በወጣትነቱ ይህንን ሁሉ ሀብት ከየት እንዳመጣ ስጠይቀው፣ ‹ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም› የሚለውን ምሳሌ አስቀድሞ የሳቀብኝን አልረሳውም፡፡ እንዴት ይረሳል!

ከአታካቹ ኑሮአችን ወጣ ብዬ የፖለቲካውን መንደር ጠጋ ለማለት ስሞክር ወላፈኑ አላስጠጋ አለኝ፡፡ የእኛ ሰው ዳርና ዳር ሆኖ በነገር ፍላፃ እየተቀጣቀጠ ነው፡፡ እኔማ የዛሬ አምስት አመት የነበረውን ያን የማያልፍ የሚመስል ‹‹የጫጉላ ጊዜ›› እያሰብኩ በሐሳብ ወደኋላ ነጎድኩ፡፡ ከመሪ እስከ ተመሪ ተቃቅፈው የዘመሩባቸው እነዚያ ወርቃማ ጊዜያት ትዝ እያሉኝ፣ ‹‹ያሳለፍነው ጊዜ ደስታን ያየንበት፣ አሁን ተመልሶ ቢገኝ ምናለበት…›› የሚለው የሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ዘፈን በምናቤ መጣ፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ልጅ አንበርብር ሰለሞን በመጽሐፈ መክብብ፣ ‹…የሆነው ነገር እርሱ የሆነ ነው፣ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፣ ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም…› ያለው እኮ እኛ በሁኔታዎች መለዋወጥ እንዳንገረም ወይም እንዳንደናገጥ ነው፡፡ ስለዚህ ‹…ሁሉም ነገር ንፋስን እንደ መከተል ነው…› እንዳለው ያን ያህል አንደነቅ…›› የሚሉኝ እየታወሰኝ ሥጋዬና ነፍሴ ሲሟገቱ ከረሙ፡፡ ለማንኛውም የገፋ ዕውቀት ባይኖረኝም ዕድሜ አስተምሮኛልና ለስክነትና ለትዕግሥት ከፍ ያለ ቦታ እሰጣለሁ፡፡ የምበሳጨው ግን አውቀናል በቅተናል የሚሉት ምን እየሆኑ ነው በዚህ በሠለጠነ ዘመን ካራ የሚስሉት እያልኩ ነው፡፡ ግራ የገባ ነገር!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አገራችን እየገባችበት ያለው ከድጡ ወደ ማጡ ሁኔታ በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ በቀደም ዕለት ከስግደት መልስ የውዴ ማንጠግቦሽን ጉልባን እየበላን ቡና ስንጠጣ፣ ‹‹የአገራችን ልሂቃን ትልቁ ችግር ምን እንደሆነ ታውቃለሁ?›› ሲለኝ፣ ‹‹ወንድሜ አንተው ምሁሩ ንገረኝ እንጂ እኔማ ምኑን አውቄ?›› በማለት የሚለኝን በአንክሮ ለመስማት ተመቻቸሁ፡፡ ትኩሱን ቡና በሚጥሚጣ ከተለወሰው ጉልባን ጋር አብሮ ማስኬድ አቅቶት ትንሽ ከታገለ በኋላ፣ ‹‹…ብዙዎችን ልብ ብለህ አስተውለሃቸው እንደሆነ አንደኛ ስክነት የላቸውም፣ ሁለተኛ ምን እንደሚፈልጉ ግልጽ አይደለም፣ ሦስተኛ ዕውቀታቸው ለብ ለብ ስለሆነ ራሳቸውን ለመግለጽ ያዳግታቸዋል፣ አራተኛ የሚለቀቅላቸውን አጀንዳ እያላመጡ መወራጨት እንጂ የደረጀ ሐሳብ ይዘው አይሞግቱም፣ አምስተኛውና የመጨረሻው በጭፍን መቃወም ወይም መደገፍ እንጂ ከምክንያታዊነትና ከሒሳዊ ትንተና ጋር አይተዋወቁም…›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ የድንጋጤዬ መነሻ ግን እኔ ይህንን ያህል ጊዜ በምድር ስኖር አንዲት መናኛ ዲግሪ ሳትኖረኝ፣ በዲግሪ ላይ ዲግሪ እየደራረቡ አንቱ የተባሉት ጭምር እዚህ ጎራ ውስጥ ሲደመሩ መስማቴ ነው፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲግሪ ማምረቻ እንጂ የዕውቀት ማዕድ አለመሆናቸውን የተናገሩትን ሳስታውስ ደግሞ አፌን መረረው፡፡ ምሬት በዛ እኮ ጎበዝ!

ባለፈው ሰሞን የሚከራይ ባለሦስት ደርብ ዘመናዊ ቪላ አለኝ ያሉ ሴት ወይዘሮ ደውለውልኝ እሳቸው ዘንድ ሄጄ ነበር፡፡ ለመጦሪያቸው ብለው ያስገነቡትን ዘመናዊ ቪላ ከተቻለ ለፈረንጅ ኤምባሲ፣ ካልተቻለ እኔ ነኝ ላለ ዓለም አቀፍ ኤንጂኦ ብቻ ማከራየት እንደሚፈልጉ ነገሩኝ፡፡ ምነው አቅሙ ላለው ማንም ተከራይ የማያከራዩት በማለት ትዝብት ያጠላበት ጥያቄ ቢጤ ጣል ሳደርግላቸው፣ ‹‹አቶ አንበርብር እኔ ከማንም ጋር መነካካት አልፈልግም፡፡ ለቢሮ እፈልገዋለሁ ብሎ የተከራየ ነገ የፖለቲካ ፓርቲ መሰብሰቢያ ወይም መዶለቻ ቢያደርገው አለቀልኝ ማለትም አይደል፡፡ እኔ የምፈልገው የዲፕሎማቲክ መብቱ የተጠበቀ አስተማማኝ የምዕራብ አገር ኤምባሲ ወይም የዩኤን ኤጀንሲ ወይም የዕርዳታ ተቋም ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ወንድሜ የእኛ ሰው እንደሆነ አካሄዱ አይታወቅም፡፡ አሁንማ የግራ ፍሬቻ እያበራ ወደ ቀኝ የሚታጠፈው እየበዛ ስለሆነ እዚያው በፀበሉ፡፡ ደግሞ በገዛ ንብረቴ ለማንም የማከራየት መብት እንዳለኝ አትዘንጋ…›› ብለው ገርመም አደረጉኝ፡፡ እኔም በኃፍረት ፈገግ እያልኩ አንገቴን በአዎንታ እየነቀነቅኩ በሐሳባቸው መስማማቴን አሳየሁ፡፡ በማይረባ ንትርክ ለምን የእንጀራ ገመዴን ልበጥስ? ወቸ ጉድ!

አንድ ጊዜ ላፍቶ ለአንድ ሰው የሚከራይ ቤት አፈላልጌ አግኝቼ ከባለቤቱ ጋር ሲነጋገሩ፣ የቤቱ ባለቤት ቆምጨጭ ያሉ የድሮ ሃምሳ አለቃ ኖረው መመርያውን ያዥጎደጉዱ ጀመር፡፡ ‹‹ከሦስት ሰዓት በኋላ አምሽቶ መምጣት አይቻልም፣ ከዕጮኛህ ወይም ከከንፈር ወዳጅህ ውጪ ማንም ሰው እዚህ ግቢ መግባት አይችልም፣ ለጤናህ ጎጂ የሆኑ እንደ ጫት፣ ትምባሆና የአልኮል መጠጥ ከቢራ በስተቀር ማምጣት አይፈቀድልህም፣ በአጠቃላይ ከሌሎች ተከራዮች ጋር ቢቻል ተግባብተህ ለመኖር ካልሆነ ደግሞ ላለመነታረክ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል…›› አሉት፡፡ ለነገሩ ተከራዩ መልካም ሰው ስለነበረ በአከራዩ መመርያ አልተከፋም፡፡ ‹‹እኔ ያሉኝን ነገር በሙሉ ተግባራዊ አደርጋለሁ፣ እርስዎም በቃልዎ መሠረት ይሁኑ…›› ብሎ ለአሥር ዓመታት ያህል አባትና ልጅ ሆነው መዝለቃቸውንና እሱ የራሱን ቤት ሲሠራ አጋዡ እንደነበሩ ምስክር ነኝ፡፡ ተድሮ የወጣውም ከእሳቸው ቤት እንደ አባቱ ሆነው ደግሰው ነበር፡፡ ይህንን መሳይ የበርካታ ሰዎች ተመሳሳይ ታሪክ እንደ ዋዛ ታልፎ እዚህ ደረጃ መድረሳችንን ሳስበው ሆዴን ባር ባር ይለዋል፡፡ እ…ህ…ህ…ህ…!

ይህንን ጉድ ያጫወትኩት ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አንድ ቀልድ ነገረኝ፡፡ ያኔ በዘመነ ኢሕአዴግ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ሰዎች አንድ አካባቢ ጥሩ ቪላ በደላላ አማካይነት ያገኙና ሊከራዩ ይሄዳሉ፡፡ ከአከራይዋ ጋራ ተገናኝተው በወርኃዊ ኪራይ ዋጋ ተስማምተው የተወሰነ ቅድሚያ ክፍያ ፈጽመው ይመለሳሉ፡፡ ሌላ እሳት የላሰ ደላላ አከራይዋ ዘንድ ይሄድና በተመሳሳይ ዋጋ ተከራይ እንዳገኘላቸው፣ የበፊቶቹ ግን ኢሕአዴጎች ስለሆኑ ጥሩ እንዳልሆነ ይነግራቸዋል፡፡ አከራይዋም ደላላውን ቶሎ ብለህ ተከራዩን አምጣና ዕቃውን ያስገባ ይሉታል፡፡ በነጋታው አዲሱ ተከራይ ሙሉ የቢሮ ዕቃውን አስገብቶ እያስተካከለ ሳለ ኢሕአዴጎቹ ይመጣሉ፡፡ በሚመለከቱት ነገር ተገርመው አከራይዋን ያስጠሩና ለምን እንዲህ እንደሆነ ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹እኔ ኢሕአዴጎች መሆናችሁን አላወቅኩም ነበር፡፡ ሳውቅ ግን ለእናንተ ቤቴን ከማከራይ ሰይጣን ቢከራየው ይሻላል ብዬ ነው እናንተን ያላስገባሁት…›› ይላሉ፡፡  አንደኛው በጣም ተገርሞ፣ ‹‹ከኢሕአዴግ ለምን ሰይጣንን ይመርጣሉ?›› ብሎ ሲጠይቃቸው፣ ‹‹ሰይጣንን በፀበል አባርረዋለሁ፣ እናንተን በምን አቅሜ ነው ከቤቴ ላስወጣችሁ የምችለው…›› ብለው ነበር የመለሱት አለኝ፡፡ የባሰው መጣ አትሉም!

ከመሰነባበታችን በፊት አንድ ነገር ጨምሬ ላሳርግ፡፡ በበዓላት ሰሞን ወገኑን ወዳዱና አክባሪው ሕዝባችን በጦርነቱ፣ በድርቁ፣ በተለያዩ ጥቃቶችና ግጭቶች ሳቢያ ተፈናቅለው ሜዳ ላይ የወደቁ ወገኖችን እንደሚያስብ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ታሞ የተኛን መጠየቅ፣ የተራበን ማጉረስ፣ የተጠማን ማጠጣት፣ የታረዘን ማልበስ፣ የተከፋን ማፅናናትና የመሳሰሉ ፈጣሪ የሚወዳቸው ተግባራት ሥጋን ብቻ ሳይሆን ነፍስን ያረሰርሳሉ፡፡ ፈጣሪ ይህንን ከእያንዳንዳችን የሚጠብቀው መልካምነት ነው፡፡ በከንቱ ዝናና በዓለማዊ ተራ ነገሮች ከመታሰር ይልቅ፣ ለህሊና ጭምር የሚመቹ መልካም ተግባራት ላይ ማተኮር ይመረጣል፡፡ ደግነታችን ታይታ ያጠላበት እንዳይሆን እንጠንቀቅ፡፡ ‹ቀኝ ሲሰጥ ግራ እንዳያይ› እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ‹‹ፈጣሪ ልግስናችንን ብቻ ሳይሆን የሚያየው በልባችን ውስጥ ያለውን ቅንነትና የዋህነት ጭምር ስለሆነ፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ የዲያቢሎስ ማደሪያ እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን…›› የሚሉት አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው፡፡ ምሁሩ ልጃቸው ደግሞ፣ ‹‹አፈ ቅቤ ልበ ጩቤ በመሆን ማንንም ማታለል ስለማይቻል፣ ቢያንስ ለህሊናችን ሰላም ስንል ደግ መሆን ይጠበቅበናል…›› ይለኛል፡፡ ውድ ባለቤቴ ማንጠግቦሽም፣ ‹‹ህሊናችን ሰላም የሚያጣው ፈጣሪ በሚፈልገን ቦታ ሳንገኝ ስንቀር ነው…›› ብላ ታስደምመኛለች፡፡ እኔ እነዚህን ሁሉ ማሳሰቢያዎች ቃርሜ ህሊናችን ንፁህና ሰላማዊ ይሁን እላለሁ፡፡ መልካም በዓል! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት