ወጣቶች ከአደንዛዥ ዕፅና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ለማድረግ አገር አቀፍ አደንዛዥ ዕፆች ንቅናቄ ማስጀመሩን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
‹‹ወጣቶችን ከአደንዛዥ ዕፆችና መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች እንታደግ›› በሚል መሪ ቃል የሚተገበረው ይህ ንቅናቄ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ የሚረዳ መሆኑን ንቅናቄው ይፋ በተደረገበት ረቡዕ ሚያዝያ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ተገልጿል፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ንቅናቄው መጀመሩን አስመልክተው እንደገለጹት፣ የሚታለመውን ዘላቂ ልማት ለማምጣት ለወጣቶችና ታዳጊዎች በቂ ትኩረት በመስጠት ሰብዕናቸውን መገንባት ያስፈልጋል፡፡
በከተሜነት መስፋፋትና ሉላዊነት ምክንያት የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እየተስፋፋ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ግንዛቤ እየተፈጠረላቸው አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወጣቱ አደንዛዥ ዕፅና መጤ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመሞከር ለከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውሶች እየተዳረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በራሳቸው ባህል የሚኖሩና አገራቸውን የሚወዱ ወጣቶችን ለመፍጠር ከቤተሰብ ጀምሮ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባም መክረዋል፡፡
ከመንግሥት በተጨማሪ በርካታ የሲቪል ማኅበራት በጉዳዩ ላይ እየሠሩ እንደሚገኙ ያስታወሱት ሚኒስትሯ፣ የሱስ ማገገሚያ ማዕከላት ባለመገንባታቸው ወጣቶች በተለያዩ ሱሶች እየተዋጡ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የወጣቱን ሰብዕና ለመገንባት ቀደም ሲል የተቋቋሙትን ማዕከላት በማጠናከር ወጣቶች መሠረታዊ የባህሪና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ የተጀመረው ንቅናቄ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የሚሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡