Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየለመዱትን ያስጣለ የኑሮ ውድነት

የለመዱትን ያስጣለ የኑሮ ውድነት

ቀን:

በአበበ ፍቅር

‹‹አንተ ደህና እንድትውል ቤተሰብህ ደህና ይዋል›› የሚባለው አባባል የአንዱ ሰላም መሆን ለሌላው ሰላም ውሎ ማደር ወጥቶ መግባት ወሳኝ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ለብዙዎች አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው አስቸጋሪና ፈታኝ መሆን አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ጓዳ ነክቷል፡፡

የአንደኛው አበሳ ጠባሳው ሳይሽር ሌላው እየተተካ በአንዱ ሲሉት በሌላው እያመረቀዘ መምጣት በኢትዮጵያ ሰላም እንዲናፈቅ አድርጓል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታየ ያለው የሰላም መደፍረስና ግርግር ተስፋቸውን ያጨለመባቸው ነዋሪዎች ደግሞ እንደባህል፣ እምነታቸውና ወጋቸው የሚያከብሩትን በዓል እንኳን በደስታ እንዳያከብሩ እንቅፋት ሆኗል፡፡ አቅሙ እንኳን ቢኖር ሥነ ልቦናዊ ጫናው ደስታቸውን ስለመንጠቁ አስተያየት የሰጡን ነግረውናል፡፡

‹‹በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንደሚባለው በየቀኑ በፍጥነት እየጨመረና እያደገ ያለው የኑሮ ውድነትም በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ከመብላት ወዳለመብላት፣ ከዘመድ አዝማድ ከመጠያየቅ ወዳለመጠያየቅ፣ በዓላትን እንደልማዳቸው ከማክበር ወዳለማክበር፣ ከየጎረቤት ከመቋደስ ወዳለመቋደስ እያሸጋገራቸውም ነው፡፡ ኑሮው ከሚችሉት በላይ እየሆነባቸው እንደመጣና በዚሁ ከቀጠለ ለመኖርና በልቶ ለማደር በእጅጉ እንደሚቸገሩ ስጋታቸውን ያጋሩንም አሉ፡፡

ከዕለት ኑሮ በተለየ መልኩ በጉጉት የሚጠብቁት፣ ከመቼውም በተለየ በጋራ የሚበሉበት፣ የሚጠጡበትና አዳዲስ የሚለብሱበት በዓል ሲመጣ አብሮት የሚመጣው ወጪ ፍርኃትና ጭንቀት እንደሆነባቸው የሚገልጹም አሉ፡፡

ወ/ሮ መሠረት ብርቁ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ መንገድ ዳር ሸራ ወጥረው ሻይና ቡና በመሸጥ ሁለት ልጆቻቸውን ያሳድጋሉ፡፡ ለልጆቻቸው አቅማቸው የፈቀደውን እያደረ ቢሆንም፣ የኑሮ ውድነቱ እንደፈተናቸው ይናገራሉ፡፡ በተለይ በዓላት ሲመጡ ለልጆቻቸው ያስለመዱት እንዳይቀር ላይ ታች ብለው ቤታቸውን ይሞሉ የነበረ ቢሆንም፣ ለዘንድሮ ግን አቅማቸው ተፈትኗል፡፡

‹‹በማንኛውም ነገር ላይ በየዕለቱ ዋጋ ጨምሯል፣ ውኃ መብራት ጨምሯል›› በማለት ኑሮው ጣሪያ ነክቶ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነባቸው የሚናገሩት መሠረት፣ ከዚህ በፊት የፋሲካንም ሆነ ሌሎች ትልልቅ ሃይማኖታዊ በዓላትን ለማክበር ከተቻለ በግ ካልሆነ ደግሞ የቅርጫ ሥጋ በማምጣት፣ ጠላና ዳቦውን፣ እንጀራውን በቤት ውስጥ በማዘጋጀት በቄጠማና በጭሳጭስ ሞቅ በማድረግ ያከብሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በዓልን በሰላምና በፍቅር ከልጆቻቸው ጋር ተሳስቀው ከጎረቤት ጋር በመጠራራት ቤት ያፈራውን ሁሉ በልተው ጠጥተው ያሳልፉ እንደነበር በመጥቀስም፣ ዘንድሮ ግን ሐሳባቸው ሁሉ መበተኑን፣ ጭንቀት ውስጥ መግባታቸው ይናገራሉ፡፡

 ሚያዝያ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚከበረውን የፋሲካ በዓል ለማክበር ከመዘጋጀት ይልቅ ክፍል ሀገር ስላሉት ዘመድ ቤተሰቦቻቸው ደኅንነት በእጅጉ መጨነቃቸውን ይገልጻሉ፡፡

ሰሞኑን በአማራ ክልል ያለው ግርግር ስለቤተሰቦቻቸው ቢያሳስባቸውም፣ ‹‹ከአጠገቤ ያሉት ልጆቼ በዓሉን በሰላም እንዲያሳልፉ ማድረግ ስላለብኝ እንደ አቅሜ ተዘጋጅቻለሁ፤›› ይላሉ፡፡

የልጆቹ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከዕድሜያቸው ጋር እየጨመረ ቢመጣም፣ በአንፃሩ የኑሮ ውድነቱም አብሮ እያደገ በመምጣቱ በግ ገዝቶ መብላት ይቅርና ዶሮ ሽንኩርትና ዘይትን አሟልቶ በመግዛት በዓልን ለማሳለፍ በጣም እንደከበዳቸው የሚናገሩት መሠረት፣ መንግሥት በሚዲያ በጉና በሬው ዶሮውና ዕንቁላሉ በገፍ ወደ ገበያ እንደሚቀርብ ቢናገርም፣ ሁሉ ነገር ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ከመስማት በዘለለ ፋይዳ እንዳልሰጣቸው ይናገራሉ፡፡

እንደ ከዚህ ቀደሙ በግ ወይም የቅርጫ ሥጋን መግዛት የማይቻል በመሆኑም ልጆቻቸውን በመምከርና በማሳመን ዶሮ በመግዛት የዘንድሮውን የፋሲካ በዓል በዶሮ በጠላና በዳቦ ለማሳለፍ መወሰናቸውን ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ ይልቅ በእጅጉ የሚያሳስባቸው በበዓል ገበያ ወቅት ገበያው ተዘጋግቶባቸው፣ ለበዓል መዋያ የሚሆን አንዳችም ነገር ሳይገዙ በጉጉት የሚጠብቁትን በዓል በባዶ እንደሚያሳልፉ የነገሯቸው ቤተሰቦቻቸው እንደሆኑም ያክላሉ፡፡

የኑሮ ውድነቱ በተለይ በዓላት በመጣ ቁጥር የሚፈትነው በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ያሉትን ብቻ ሳይሆን መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ጭምር ነው፡፡ እሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው ተቀጣሪ መሆናውን የነገሩን ሌላ አባት፣ የዘንድሮ ፋሲካን እንደከዚህ ቀደሙ እንደማያከብሩ በሐዘኔታ ነግረውናል፡፡

በሁሉም በዓላት ቤታቸው ሞልቶ ማየት እንደሚወዱ፣ ከ25 ዓመታት በላይ በዘለቀው የትዳር ሕይወታቸውም በሁሉም በዓላት ዶሮ፣ በግ፣ ቅርጫ፣ ከመጠጡም ጠላና ጠጅ ቀርቶባቸው እንደማያውቅ የነገሩን እኚህ ሰው፣ ዘንድሮ ይህ እንደማይሆን ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ መፈሰኪያ ሦስት ዶሮ ይታረድ የነበረ ሲሆን፣ ዘንድሮ ይህንን ወደ ሁለት ለማውረድ ተገደዋል፡፡

ለእሑድ ቅርጫ ሥጋና በግ ቀርቶባቸው የማያውቅ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ከሁለት አንዱን መርጠው፣ በግ ለማረድ ቢወስኑም ይህንን እንዴት እንደሚገዙትም ጨንቋቸዋል፡፡

በተለያዩ ገበያዎች ዞረው እንዳዩት የበግ ዋጋ የሚቀመስ አልሆነም፡፡ እሳቸው በሰባት ሺሕ ብር በግ ለመግዛት ቢያስቡም፣ እስከ ረቡዕ ሚያዝያ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በነበረው ገበያ በወፍ በረር ባደረጉት ቅኝት ዘጠኝ ሺሕ ብር መሆኑ በጉንም ሊያስጥላቸው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...