የፋሲካ በዓልን የሚያከብሩ የዓለም ሕዝቦች በዓሉን ከሚያደምቁበት የቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥነ ሥርዓት በተጨማሪ ለበዓሉ የሚያዘጋጁት የተለያዩ ምግቦችም ይገኙበታል፡፡
ዱቄት፣ ስኳርና እንቁላልን ጨምሮ ከተለያዩ ጣፋጭና ለዓይን ማራኪ ከሆኑ ግብዓቶች የሚዘጋጁ ኬኮችና ዳቦዎች፣ ከዶሮና በግ የሚዘጋጁ ምግቦችም በተለያዩ አገሮች እንደ ባህልና ልምዳቸው ለበዓሉ የሚቀርቡ ናቸው፡፡
እንቁላልና ዶሮ በአብዛኛው የበዓሉ አክባሪ ማኅበረሰቦች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ በተለይ እንቁላልን ቀይ ቀለም በመቀባት የሚታወቁት የምዕራቡ ዓለም ክርስቲያኖች፣ ይህን የሰውን ልጆች ያድን ዘንድ በመስቀል ላይ የተቸነከረውንና ደሙን ያፈሰሰውን ኢየሱስ ክርስቶስ ለማስታወስ ይጠቀሙበታል፡፡ እንቁላልን የፋሲካና የአዲስ ሕይወት ምልክት አድርገውም ይወክሉታል፡፡
በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታዮች ባብዛኛው ፆሙን የሚፈስኩት በዶሮ ወጥ ነው፡፡ አክፋዮች ደግሞ፣ በተልባ ወጥ ወይም ለሆድ በማይከብዱ ምግቦች ፆማቸውን ይገድፋሉ፡፡
እንደየ ባህልና ልማዱ ቅርጫ ተቀራጭቶ፣ በግ አርዶ የተለያዩ ምግቦችን ማዘጋጀትና ድፎ ዳቦ መጋገር የበዓሉ ማዕድ ማድመቂያ ናቸው፡፡ በዕለቱ ጠላ፣ ጠጅ እንዲሁም አልኮል ለማይጠጡ ከገብስ የሚዘጋጅ ኪኒቶ (መውደድ) ለማወራረጃ ይቀርባሉ፡፡
በግሪክ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ዘንድ የተጠበሰ የበግ ሥጋና ጣፋጭ የትንሳዔ ዳቦ በፋሲካ የሚቀርብ ምግብ ነው፡፡ ባህላዊ ሾርባ ደግሞ የፆም መፍቻቸው ነው፡፡
በሰርቢያ የበግ ሥጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ዓይብ፣ በቤት ውስጥ የተዘጋጀ ዳቦና የተለያዩ ጣፋጭ ኬኮች ለፋሲካ ይዘጋጃሉ፡፡
በኦስትሪያ ለፋሲካ በገበታ ከሚቀርቡ ምግቦች መካከል ከዘቢብ፣ ለውዝና ቀረፋ የተዘጋጀ ኬክ ይገኝበታል፡፡ በፖርቱጋል ደግሞ በእንቁላል ያጌጠ ጣፋጭ ኬክ ይቀርባል፡፡
በጣሊያን ፋሲካ ከሁሉ በዓላማት በድምቀት የሚከበርበትና የጣሊያን ባህላዊ ምግቦች የሚታዩበት ነው፡፡ ሕይወትን ይወክላል የሚሉት የጠቦት በግ ሥጋ፣ መልሶ መወለድን የሚወክለው እንቁላል ሁልጊዜም ከፋሲካ ማዕድ አይለዩም፡፡
በሩሲያ በጥንት ጊዜ 48 የጾም ቀናትን ለመወከል 48 አይነት ምግቦች ለፋሲካ ማዕድ ይቀርቡ እንደነበር የሩሲያን ኪችን ድረገጽ ያሳያል፡፡ በቀለም የተዋቡ የተቀቀሉ እንቁላሎችና የእየሱስ ክርስቶስን መሰቀል የሚያስታውሱ ኬኮች ሩሲያውያን ለፋሲካ ማዕድ ከሚያቀርቡዋቸው ይገኙበታል፡፡