Friday, June 14, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹ያልተኖረ ወጣትነት በዓለም ከሚያጋጥሙ ኪሳራዎች ሁሉ ቁንጮው!

በያሬድ  ነጋሽ

“ኤሊ ጉረኛው አፈረ፣ ጥንቸል ትጉ ተከበረ፣ . . .” በአጸደ ሕፃናት ጊቢ ውስጥ ድምፁ ያስተጋባል። መምህራኑ በወዲህ የተጋ፣ ላቡን ያፈሰሰ፣ ተስፋ ያልቆረጠ፣ ቀና የሆነ ከግቡ እንደሚደርስ በወዲያ፣ በዋዛ ፈዛዛ ጊዜውን የሚያሳልፍ፣ በንቀትና በክፋት የቆመ ደግሞ በአጭር እንደሚቆም፣ ህልሙን እንደማያሳካ በጨዋታ መልክ ለሕፃናቱ ያስገነዝባሉ። ይህንን እየዘመረ ያደገው ተማሪ፣ በሃይማኖት ሥፍራዎች ይህንኑ የሚያጠነክሩ ወይም ሃቀኝነት፣ ብርታት፣ ሰው አክባሪነት፣ የመሳሰሉ ቀና መንገዶች ያለማወላወል ሊጓዝባቸው የሚገባው እንደሆኑ ይሰበካል። ቤተሰብም፣ ማኅበረሰብም፣ ይህንን መንገድ ተከትሎ እንዲጓዝ የታዳጊውን ሞራል ይገነባል።

ሆኖም በዚህ መልኩ ያደገው ወጣት በጉብዝና ወራቱ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ፣ እሩቅ ሳይጓዝ በአጭር ይቀራል ያሉት ፌዘኛ ቀድሞ፣ እሩቅ ይጓዛል ያሉት ትጉህ በአጭር ቀርቶ ቢመለከት እንዲህ ሲል አንጎራጎረ ‹‹ባለሱቁ በሁለት በኩል ከፍና ዝቅ እያለ የእኩልነትን፣ የመብለጥንና የማነስን ማረጋገጫ በሆነው ሚዛን ላይ ዕቃውን እየሰፈረ ለደንበኞቹ ይሸጣል፡፡ ሚዛኑ እንዲለካ የተሰጠውን ነገር ሻጩንም ገዥውንም በማይጎዳው የእኩልነት ደረጃ ላይ ከማመላከቱ በፊት ከበድ ያለ ነገር የበዛበት የአንደኛው የሚዛኑ ክፍል ዝቅ ብሎ አነስተኛ ክብደት የተሸከመው ሌላኛው የሚዛኑ ክፍል ደግሞ ከፍ ማለቱ የተፈጥሮም ሕግ በመሆኑ ባያስገርመኝም፣ ዓለም ሕዝቦቿን የምታስተዳድርበት መንገድ ማሳያ መስሎ ይታየኛል፡፡

በዓለም ሚዛን ላይ የተቀመጡ የሰው ልጆች ሁሉ ልክ እንደባለ ሱቁ ሚዛን ሁሉ ከባዱ ዝቅ ሲል ቀለል ቀለል ያለው ደግሞ ከፍ ይላል፡፡ ‘ለሃቅ ኖሬ ለሃቅ እሞታለሁ፣ ለእውነት እሰዋለሁ’ በሚል ከባድ ድርጊት ውስጥ በርካቶች ሕይወታቸውን ያሳልፋሉ፡፡ ዓለም በሚዛኗ እነዚህ ሰዎች በችግር አረንቋ ውስጥ በዝቅታ ሰፍራ ታኖራለች፡፡ በውሸት፣ በተንኮል ዝቅጠት ውስጥ የቀለለን ሰው ደግሞ በከፍታ ሥፍራዋ ላይ ሕንፃዋን ትገነባለታለች፡፡ በዓለም ሚዛን አዳፋ፣ ሰንካላው፣ ሰላቶው፣ ሌባው፣ ቀማኛው፣ ባለጌው፣ ናቂው፣ አቅላዩ ቀላል ቢሆኑም፣ ከፍ ብለው እንዲበሩ ምርጫዋ ነው፡፡  ታታሪው፣ ቅን፣ ሃቀኛው፣ ሰው አክባሪው፣ ጨዋው ደግሞ ከባድ ቢሆንም በዝቅታ ሥፍራዋ ማሰንበቷ ሃቅ ነው፡፡ ይገርማል በዓለም ሚዛን ላይ ከባዱ ዝቅ ብሎ ቀላሉ ከፍ ይላል፡፡

በሥራው ልቡ እስኪወልቅ ታታሪና ሃቀኛ የሆነ ሠራተኛ ከበድ ያለ ልባም ሰው ቢሆንም ዓለም በሚዛኗ ሰፍራ ዓመታቱን ሁሉ በአንድ ሸሚዝ፣ ዘመናቱን ሁሉ በደሳሳ ጎጆ ሆኖ እንዲያሳልፍ ትፈርድበትና ከሥራው ይልቅ በወሬ አለቅላቂነቱ፣ የባለ ጉዳይ ኪስ አውላቂነቱና የሕዝብ ሀብት መዝባሪነቱ ገኖ ቅልል ያለውን ሰው ደግሞ ከፍ አድርጋ፣ በሹመት አንበሽብሻ በዘመናዊ ቪላው መንደላቀቅን ቸራዋለች፡፡ በንቀትና በመጸየፍ ለሰላምታ እንኳን እጁን የማይዘረጋን ቀላላ፣ ክብርና መፈራትን ቸራ በአንድ ደሴት ላይ የብቻውን የውኃ ላይ ቤት ሠርታ ታስረክባለች።›› (የካድሬው ንሰሐ፣ በያሬድ ነጋሽ 2010 ዓ.ም.፣ ገጽ 139-140)

 

እንደወጣቱ ሁሉ በርካቶች ይህንን መሰል ቃላት አንጎራጉረዋል። ለአብነት ያህል በ1980 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴዓትር ጥበባት የመጀመርያዋን ዲግሪ ካገኘች በኋላ በኢትዮጵያ የቴዓትር ዘርፍ ውስጥ ጉልህ ሚና ያበረከተችው ተዋናይት ጀማነሽ ሰለሞን፣ በተለይም የእውነታው ዓለም ውክልና ተሰጥቶት ከሚስተዋልበት የድርሰት ሥራዎች ጋር አዛምዳ ይህንን ትላለች፣ ‹‹እኔ አብዘርድ (ወለፈንዲ) ድራማ ከእውነታው ድራማ ይበልጥ ይህንን ሕይወት ይገልጻል ብዬ አምናለሁ። ሕይወት በብዛት እውነታዊው ድራማ እንደሚለው አይደለችም። ለምሳሌ በእውነታው ድራማ ላይ ጸሐፍያን ተውኔቶቹ በብዛት የሚጠቀሙት ‘Poetic Justice (በሰፈሩት ቁና)’ የሚባል ነው።

ድራማው መጀመርያ ላይ መጥፎ የነበረው ሰው በመጨረሻ ሲሸነፍ፣ ሲቀጣ፣ ሲወድቅ፣ በአንፃሩ ደግሞ መልካምነት፣ ጥሩነት፣ ሰላም ሲያሸንፍ ይታያል። ይህንን ነው ወይ በዓለም ላይ የምንመለከተው? ነው ጥያቄው፣ አይደለም። በዓለም ላይ ብርቱው ደካማውን ጨፍልቆ ሲኖር፣ ቀጣፊውና ውሸታሙ ውጤታማ ሲሆን፣ ሲሾምና ሲሸለም አጭበርባሪው እየበለፀገ፣ እውነት ተናጋሪው ደግሞ እየቆረቆዘ ነው ያለው። አብዘርድ ነው ይሄ እራሱ። እውነተኛውና ሃቀኛው ሊሸለም ሲገባው ዓለም ግን ሸልማዋለች ወይ? ነው ጥያቄው። እኔ በዚህ መልኩ ሳየው ከእውነታዊው ይልቅ አብዘርድ ድራማ ሕይወትን በትክክል ይገልጻል ብዬ ነው የማምነው።›› (ፍልስፍና ክፍል ፩፣፪፣፫፣ በቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ 2014 ዓ.ም.፣ ገጽ 9-10)

በወቅታዊ የአገራችን የፖለቲካ ጉዳይ ዙሪያ ከላይ ያነሳነውን ሐሳብ በጉልህ እየተመለከትን ነው። ፖርላማ ገብተን ሐሳባችንን ባንሰጥም፣ በተሰበሰብንበት ሥፍራ የጎንዮሽ ማንጎራጎራችን አልቀረም። እስር ቤት ያሉትን በነፃነት ከሚጓዙት ጋር፣ ሕክምና የሚከለከሉትን ከተፈደላቸው ጋር፣ የተሾሙትን ከተሻሩት ጋር፣ ቤት የተለገሳቸውን ከፈረሰባቸው ጋር ስናነፃፅር ከርመናል። “Poetic Justice ወይም በሠሩት ቁና መሰፈር በድራማ እንጂ በዕውኑ ዓለም የማይሠራ ተረት ነው፤›› የሚለውን የአርቲስት ጀማነሽ ንግግርን አጠነከርን። ግጥሙ ተለውጦ፣ ‹‹ጥንቸል ጉረኛው ተከበረ፣ ኤሊ ትጉ አፈረ›› ሆኗልና ‹‹አባት ለልጁ፣ ደጉን ከክፉ ለይቶ፣ ጥቅሙን ጉዳቱን አብራርቶ ለመምከር እንዴት አንደበቱ ይከፈትለታል፤›› ስንል ሥጋት አጭሮብናል።

ባለፉት ጊዜያት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት የሰው ነፍስ እንደ ቄጤማ ሲቀጠፍ፣ ደም እንደ ውኃ ሲፈስ፣ አካል እንደ ዋዛ ሲገደፍ ከደረሰብን ሕመም በላይ የዚህ ሁሉ መዘዝ መንስዔ የሆነው ሰው በሲመት ወደ ሥልጣን ሲመለስ ማየታችን ሐኪም የማይሽረው፣ ወጌሻ የማይጠግነው ሕመም ተጣባን። ‹‹የተከዳው መከላከያም ወይም የተቋማት አወቃቀር ከፖለቲካው ይልቅ ለሕዝብ በቆመበት፣ የገዥው ፖርቲ አባላት ከገዥው ይልቅ ለሕዝብ በወገኑበት አገሮች ውስጥ ነገሩ የተፈጸመ ቢሆን፣ የአገሪቱ መንግሥት ለአንድ ሰዓት እንኳን በቤተ መንግሥት አይቆይም፤›› ስንል በእርግጠኝነት ተናገርን። ሆኖም የፖለቲካው መልክ ይህንን ቢመስልም ወጣቱ ሊገነዘበው የሚገባ ዋነኛ ጉዳይና ሊጠይቀው የሚገባው አንኳር ጥያቄ ከፊቱ ተጋርጧል።

ሊገነዘበው የሚገባውን ጉዳይ እናስቀድም። ቤተሰብ በሆኑ፣ ከልብ በሚፈላለጉ፣ በሚደናነቁ፣ በሚከባበሩ ግለሰቦችም ይሁን ማኅበረሰቦች መሀከል አጥር ሆነው የቆሙ አካላት በሚፈጥሩት ጋሬጣ የሚዋደዱት፣ የሚፈላለጉትና የሚደናነቁት ግለሰቦች ይሁን የማኅበረሰብ አባላት ደም የተቃቡ፣ የተራራቁ፣ የተለያዩ ሆነው ለመኖር ይገደዳሉ። ወዳነሳነው ሐሳብ የሚያደርሰን አንድ ተመሳሳይ ጉዳይ እናንሳ።

በአንድ አገርና በተመሳሳይ ጊዜ በሩሲያ ውስጥ የተወለዱት ሁለቱ ታላላቅ የልብወለድ ደራሲያን፣ ቶልስቶይና ዶልስቶቪስኪ (ሰባት ዓመት ታላቅ ነው) በሥራቸው የሚከባበሩ፣ የሚደናነቁና መገናኘት የሚፈልጉ የነበሩ፣ ነገር ግን መገናኘት ሳይችሉ ሕይወታቸው ያለፈ የሥነ ጽሑፍ ፈርጦች ነበሩ። አንደኛው ለአንደኛው ሲሞካሹም ተስተውሏል። ‹‹በሩሲያ ሕዝብ መካከል ዘመን አይሽሬ ተወዳጅ የሥነ ጽሑፍ ቁንጮ፣ ከፑሽኪንም በላይ!›› ዶልስቶቪስኪ ስለቶልስቶይ የተናገረው። በ1881 የዶልስቶቪስኪ መሞትን የሰማው ቶልስቶይ፣ ‹‹ደግሜ የማላገኘውን ጓደኛዬን እንዳጣሁ ይሰማኛል። ለእኔ በጣም የቅርብ ዘመድ፣ ውድና አስፈላጊ ሰው እንደሆነ ተረዳሁ። እኔም ጸሐፊ  ነበርኩ። ነገር ግን ራሴን ከእሱ ጋር ለማወዳደር በጭራሽ አልሞክርም። መሞቱን ሳውቅ፣ ከውስጤ የሆነ ዓይነት ነገር እንደተለየኝ ተሰማኝ። እሱ ስለእኔ ያለውን ጥሩ ስሜት ስረዳ ደግሞ አምርሬ አለቀስኩ።›› ሲል ማስታወሻውን አሥፍሯል።

እኚህ ታላላቅ ሁለት ደራሲያን በሕይወት ሳሉ፣ እንደፍላጎታቸው በአካል የሚያገናኛቸው አድናቆታቸውን፣ መውደዳቸውን ሊለዋወጡበት የሚያስችላቸው አንድ ምክንያት ተፈጠረ። እ.ኤ.አ. 1878 በሴንት ፒተስበርግ፣ “ቭላድሚር ሶልቬቭ” የተባለ ፈላስፋ በተለያየ ጉዳይ ላይ ገለጻ ለማድረግ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ ሁለቱም ደራሲያን ታደሙ። ነገር ግን ሁለቱም በቦታው መገኘታቸውን ደራሲያኑ አያውቁም ነበር። በዚሁ ዝግጅት ላይ ሁለቱም እንደታደሙ፣ ምን ያህል ለመገናኘት የቃተቱ እንደሆኑና አንዳቸው ለአንዳቸው ያላቸውን ክብር ጠንቅቆ የሚያውቅ “ስትራኮቭ” የተባለ ግለሰብ ተገኝቷል። ሆኖም፣ ሁለቱ ደራሲያን ሳይገናኙ ፕሮግራሙ አልቆ ተበተኑ።

‹‹ይኼ ስትራኮቭ የተባለ የሁለቱም ወዳጅ እንዴት ሊያገናኛቸው አልፈቀደም?›› ያልን እንደሆን፣ ሰውየው የሚሰጠው ምላሽ ‹‹ቶልስቶይ ከማንም ጋር መገናኘትም፣ መተዋወቅም አልፈልግም ብሎኛል፤›› የሚል ነበር። የቶልስቶይን ገለልተኛ የኑሮ ዘይቤ የሚያውቁ ሰዎች “ብሎ ይሆናል” ብለው ቢያምኑም፣ “አና ግሪጎሪቭና” የተባለች የዶልስቶቪስኪ ወዳጅ በማስታወሻዋ እንዳሰፈረችው፣ “ስትራኮቭ” የተሰኘው ሰው የመገናኛ መስመሩን የቆረጠው ሆን ብሎ ደራሲያኑ እንዳይገናኙ ከመፈለግ የመነጨ የክፋት መንፈስ መሆኑን ገልጻለች።

ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የጀርመን ባህል ማዕከል (ጎተ ኢንስቲትዩት) በተዘጋጀ የአጭር ልቦለድ ወርክ ሾፕ ላይ ደራሲና ሃያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ አና ግራጎሪቭና የገለጸችው ጉዳይ እውነት እንደሆነ ሲያስረግጥ ለማዳመጥ ችለናል።

እንዲህ በተጠማ ሰውና በውኃው ጉድጓድ መሀል፣ በተራበ ሰውና በእህሉ መሀከል የሚገኝ የመገናኛውን መንገድ ለተራ ጥቅማቸው ሲሉ የዘጉ አያሌ ናቸው። በቤተሰብ፣ በአንድ ሕዝብ፣ በአንድ ሃይማኖት፣ በአንድ አገር መሀከል የሚገኝ የመሻገሪያውን ድልድይ ለተራ ትርፋቸው ሲሉ ያፈረሱ ብዙዎች ናቸው።

በሕዝብ መሀከል የተገነቡ የልዩነት አጥሮች፣ ጥቅመኞች ለተራ ጥቅማቸው ሲሉ በክፋት ያቆሟቸው እንጂ የሕዝብ ፍላጎት እንዳልሆነ በዓለም ታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚና በጉልህ ታይቷል። የበርሊን ግንብን በማቆም ሕዝቡን ከወዲያና ወዲህ ለመለየት የተሞከረው ሙከራ ፍላጎቱ የጥቅመኞች እንጂ የሕዝቡ እንዳልሆነ፣ ግንቡን በማፍረስ ሒደት ወቅት ፈረሳው ሳይጠናቀቅ የወዲኛው ሕዝብ አንዱ በአንዱ ላይ ተነባብሮ የወዲያኛውን ለማቀፍ ባደረጉት አስደናቂ የናፍቆት ትግል በግልጽ ተረድተናል። ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ በሁለት የርዕዮተ ዓለም ተነጣጥለው ከቆዩ በኋላ፣ ውጥረቱን አርግበው ወንድማማች የነበረው ሕዝብ እንዲገናኝ በፈቀዱበት ወቅት፣ ተለያይቶ የነበረው አንድ ሕዝብ ተቃቅፎ ሲያለቅስ የታየበት ትዕይንት፣ በሁለት አገር ተቋርጠው የመኖሩ ፍላጎት የፖለቲከኞች እንጂ የዜጋው እንዳልሆነ ለዓለም አሳይተዋል።

በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝብ መሀል ከተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ፣ በቅርብ ጊዜ በሁለቱ መንግሥታት መሀከል በተደረገው መስማማትና አንደኛቸው ወደሌላው አገር ባደረጉት የጉብኝት ጉዞ ወቅት በሁለቱ ሕዝብ ዘንድ የነበረውን ደስታ የሞላበትን አቀባበል ለተመለከትነው ሰዎች፣ ግለሰቦች በካቡት የፖለቲካ ካብ አንድ የሆነና የሚዋደድ ሕዝብ አላስፈላጊ ደም መቃባት ውስጥ ሰጥመው እንደነበር መረዳት ችለናል።

አሁንም በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካም፣ አንድ በሆነ ሕዝብ፣ ኑሮው ማኅበረሰባዊ በሆነበት፣ ጉርብትናው ባየለበት በትዳር፣ በክርስትናና በዓይን አባት ዝምድና በሚፈለግበት በፅዋ፣ በዕድር፣ በዕቁብ፣ አብሮነትን በሚያደረጅ ሕዝብ መሀከል የፀብ ግንብ ተገንብቷል። ከየአቅጣጫው አገሪቷን የገጠሟትን የውጭ ወረራ ወቅት፣ አንደኛው ከቀዬው ርቆ በመሄድ በሌላኛው መሬት ላይ የሕይወትና የደም ዋጋ ከፍሎ የአብሮነት ማኅተቡን በመስዋዕትነት ባሰረ ሕዝብ መሀከል የመለያየት ድንበር ተረስሷል። ኢትዮጵያውያን አብሮነትንና ቤተሰባዊነትን መመሥረት ከመፈለጋቸው የተነሳ፣ አንደኛው ለሌላኛው “የወንዜ ልጅ ነው” ወይም “አንድ ወንዝ ነን” ይላል። ይህንን ሲል ግን አንደኛው የማጀቴው “ጃራ” ወንዝ መነሻ፣ ሌላኛው መድረሻ ላይ ሆነው ይሆናል።

ይህንን የልዩነት አጥር ለማፍረስና ድንበሩን ለመጣስ፣ በተለይ ላልተገባ ግጭት ተዳርገው በከንቱ ደማቸውን ያፈሰሱ በትግራይና አማራ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች እንዲጋሩን የምንፈልገው ነገር ቢኖር፣ ማኅበረሰባዊ ግንኙነቱ በጠነከረበት እንደ እኛ ባሉ አገሮች ውስጥ “ጉርብትና” በተለምዶ የግጭት መንስዔ የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። በአርብቶ አደሩ አካባቢ ሱማሌና አፋር፣ ቦረናና ጉጂ በግጦሽ ይጋጫሉ። በአርሶ አደሩ አካባቢ ሃድያና ከንባታ፣ ስልጤና ጉራጌ እንዲሁ በድንበር ይጋጫል። ሌላውም እንደዚያው። ሆኖም የግጭቱን መንስዔ በማረቁ፣ ተበዳይን በመካሱ፣ በዳይን በመቅጣቱ ረገድ የአገር ሽመግሌ ጣልቃ ገብቶ ሚናውን የሚወጣበት እንጂ ጉዳዩ ከዚህ ተርፎ ወደፍርድ ቤት የሚሄድበት፣ ጦሩን የሚያዘምትበት አጋጣሚ አናሳ ነው። በሰሜኑ አካባቢ የዚህ ዓይነት ልማዱ እንደነበር አንጠራጠርም። ሆኖም አግብተው ወልደው ወግ ማዕረግ ባዩ፣ ዘመናቸውን ባጣጣሙ፣ ነገር ግን በወጣቱ ዘመን (የልጆቻቸውን ጨምሮ) የሚቀልዱ ፖለቲከኞች በገነቡት የመለያየት ካብ ወይም ፖለቲከኞቹ አሁን ላይ ሊስማሙበት በቻሉት መልኩ እልባት ሊሰጡት የሚቻላቸውን ጉዳይ በማጦዝ የበርካቶችን ሕይወት ጭዳ አድርገዋል። የአገር ሀብት አውድመዋል። አንድ የሆኑ ሕዝቦች በዓይነ ቁራኛ እንዲተያዩ አድርገዋል። ታሪክ አዋቂ ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪ መንፈሳውያን ነገሩን ከማብረድ ይልቅ አጡዘውታል። እነዚህም ቢሆኑ በወጣቱ ዘመን ላይ እየተወራረዱ ያሉ ናቸው።

በትግራይና አማራ አካባቢ ያለው ወጣት መካከል ትልቅ ንቅናቄን ይሻል። ከግጭት ጊዜው ይልቅ፣ ሙስሊም አባቶቻቸው ከትግራይ ወደ ወሎ “ለዳአዋ” ይሄዱበት የነበረው ጊዜ እጅጉን እንደሚበዛ፣ ክርስቲያን አባቶቻቸው ከወሎ፣ ከጎጃም፣ ከጎንደር ለዜማ ዕውቀት ወደ ትግራይ፣ ለቅኔ ዕውቀት ከትግራይ ወደ ጎጃም ይጓዙ የነበረበትና የሚያሳልፉበት የአብሮነት ወቅት እጅጉን እንደሚበረክት አብልጠው ሊመለከቱት የሚገባ አንኳር ጉዳይ ነው። በተጨማሪም አሁን ላይ በአካባቢው የገጠመን ጉዳይ ከሕዝብ ይልቅ የፖለቲከኞች ፍላጎት መሆኑን መገንዘብ ይሻል።

ወጣቱ አሁን ላይ ማንንም ተስፋ ሳያደርግ፣ ሁለቱ ማኅበረሰቦች ሊነጣጠል በማይችል አብሮነትና ወንድማማችነት በርካታ የታሪክ ምዕራፎችን አብረው እንደዘለቁ በማመን (ኢትዮጵያ የሚለውን ስም መጥራት የተጠየፉ አካላት፣ ሰሜናዊውን አካባቢ ለመግለጽ “ጥንታዊ አቢሲኒያ” በማለት የሁለቱን አካባቢ ሕዝብ በአንድ ላይ ለማንሳት ሲሞክሩ ይስተዋላል። ይህም በተዘዋዋሪ የሁለቱን አካባቢ ሕዝብ ጥንታዊ አንድነት የሚያስረዳና ሁለቱ ማኅበረሰቦች በመጥፎም ይሁን በጥሩ፣ እህል ውኃቸው በአንድ የሚሰፈር መሆኑን ያስታውሰዋል)፣ በመሀከላቸው የተገነባውን የጥላቻ ካብ በመናድ ወይም ካቡ ጥቅመኞች የገነቡት እንጂ ሕዝባዊ መሻት እንደሌለው በመገንዘብ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በተለያየ መንገድ ማቀላጠፍ አለበት።

በትግራይና በአማራ አካባቢ ያሉ የኦርቶዶክስ ወጣት መንፈሳዊ ማኅበራት፣ የሙስሊም ጀማና የፌሎሺፕ አወቃቀሮች ግንኙነታቸውን በማጠንከርና ፖለቲካውን በመብለጥ አንድነትን ሊያስመልሱ፣ የወጣቱ ዘመን ከመጠልሸቱና ከመቀማቱ፣ አንድነታቸውን የማይመጥን ተጨማሪ መቋሰል ውስጥ ከመግባታቸው በፊት በቃ ሊሉ ይገባቸዋል።

ተከታይ ጉዳያችን መላው የኢትዮጵያ ወጣት ሊጠይቀው የሚገባውን ጥያቄ ማንሳት ይሆናል። በዘመን ቅብብል ከትናንት ሰው ጀምሮ እየተንከባለሉ እስከ መጪው ትውልድ ደርሰው የሚነሱ ተመሳሳይነት ያላቸው ጥያቄዎች እንዳሉ የፍልስፍናው መስክ ይነግረናል። እነዚህም ‹‹እኔ ማነኝ? ማን ፈጠረኝ? የተፈጠርኩት በአጋጣሚ ወይስ በአምላክ ፈቃድ? አምላክ ማነው? የተፈጠርኩበት ዓላማ ምንድነው? ቆይታዬ ምን መምሰል አለበት?›› የሚሉና የመሳሰሉት ሲሆኑ መጠሪያቸውም “Perennial” ይሰኛሉ። ከዚህ ውስጥ የዛሬ ጊዜ ባለቤቶች ወይም በጉብዝና ወራት የምንገኝ ወጣቶች፣ ‹‹የተፈጠርኩበት ዓላማ ምንድነው? ቆይታዬ ምን መምሰል አለበት?›› የሚለው ከፊታችን የተጋረጠ ጠቅለል ያለ ጥያቄ ነው። ይህ ላይ ያተኮረ ወጣት ደግሞ በኢትዮጵያ  አሁናዊ ሁኔታ ላይ  ተከታዮቹን ጥያቄ ለመመለስ ግዴታ አለበት።

ሰላማችን ወዴት አለ? በእነማን ዘመን ይህ ሆነ? ከአገር ይልቅ ለፖለቲከኛው ፍላጎት ሲባል በማን ዘመን ደም ፈሰሰ? ሕይወት አለፈ? በማን ዘመን ሰው ተዘቅዝቆ ተሰቀለ? ማን በድንጋይ ተወገረ? የዚህ ዘመን ታሪክ በማን ስም የሚመዘገብ ይመስለናል? በአገርህ መቼ ትምህርትህን አጠናቀክባት? መቼ ሠርግህ ተደገሰባት? መቼ ልጅህን አስተምረህ ዳርክባት? መቼ የልጅ ልጅህን አየህባት? አንድ አገር ላይ ተፈጥሮ ወግ ማዕረግ ሳያዩ ማለፍ መቀሰፍ እንደሆነ አልተረዳኸም? ጠምዶ የሚያርስብህ ፖለቲከኛው ለወግ ማዕረግ የደረሰ መሆኑን ዘነጋኸው? (አብዛኛው ፖለቲከኛ መማር፣ ማግባት፣ መውለድ፣ መክበድ፣ የሚባሉ ነገሮችን ጨርሶ በቀጣይ የሞቱን ዘመን ብቻ የሚጠብቅ ነው)፣ ሰላም መስፈኑ ለሌሎች ሳይሆን የተፈጠርክለት ዓላማ አሳክቶ ለማለፍ ለራስህ ስትል የምትጠብቀው መሆኑን ረሳኸው? በዘመንህ እየተቀለደ መሆኑን ዘነጋኸው? ቁማሩ ያንተን ዘመን ማሳዥያ አድርጎ እንደሚቆመር አልተረዳህም? ማን በማን ዘመን ላይ ይቀልዳል? በእውነቱ በአሁኑ ወቅት ወጣቱ የሕይወት መስዕዋትነት  ሊከፍልለት የሚገባው ዓላማ አለ? የዘመኑ ታሪክ በዘመንህና በስምህ የሚመዘገብ መሆኑን ዘነጋኸው? ጥያቄው ከዚህ በላይ መጓዝ ይችላል።

የዚህ አንቀጽ ዓላማ አመፅ አንሳ የሚል ጥሪ ሳይሆን ሰላማዊ በሆነ ኑባሬን በመምረጥ፣ ጥያቄዎችን በመጠየቅ፣ መሣሪያ አድርገው ለሚጠቀሙት፣ ዘመኑን የቁማር መጫወቻ ጠረጴዛ ያደረጉትን አካላት ፊት በመንሳት የገዛ ዘመኑን ማስጣልና በዘመኑ እየተፈጸመ ያለውን ታሪክ ማደስ አሁን ላይ ከወጣቱ የሚጠበቅ ሥራ መሆኑን ማስገንዘብ ነው። በማጠቃለያችን መውጪያ የሚሆነን ሐሳብ አንስተን እናብቃ።

‹‹ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዎ.ወ) በትውፊታቸው እንዲህ ሲሉ ያልተኖረ ወጣትነት ምን ያህል እንደሚያስጠይቅ ተናግረዋል፡፡ ‘የአንድም ሰው እግር፣ በምፅዓት ቀን አራት ጉዳዮች ሳይጠየቅ በፊት ወደ የትም (ወደገነት ወይም ሲኦል) አይንቀሳቀስም፡፡ ከአራቱ ጥያቄዎች መሀከል አንደኛው፣ ‘ወጣትነትህን በምን አጠፋኸ?’ የሚለው ነው። ፋይዳ-ቢስና ያልተኖረ ወጣትነት በምድረ-ዓለም ላይ ከሚያጋጥሙ ኪሳራዎች ሁለ ቁንጮው ነው፡፡ በእርጅና ዘመን የፀፀት ጉያ ነው፡፡’›› (ወጣትነት፣ በዓብዱራህማን ሰዒድ (ሜጢ)፣ ገጽ 105-106)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው habeshaw2022@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles