Saturday, July 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የታክስ አስተዳደር ፈተናዎችና ጥላ ኢኮኖሚ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገርን ለመገንባት፣ የሕዝብን ጥያቄዎች ለመመለስና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ፣ የሀብት ክፍፍልን መሠረት በማሳደግ የሚሠሩ ማናቸውም ዓይነት የልማት ሥራዎች ዋነኛ የገቢ ምንጭ መሠረት ከዜጎችና የሚሰበሰበው ታክስ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ለሕግና ሥርዓት ተገዥ ሆነው፣ ታክስ የሚከፍሉ ዜጎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡ የታክስ ገቢ ለአንድ አገር ዕድገት፣ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ቢሆንም፣ ሥርዓቱን ተከትለው የሚከፍሉ ጥቂቶች ናቸው፡፡ በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ታክስና ግብር መክፈል ዋነኛ እንደሆነ ቢነገርም፣ ሒደቱ ጤናማ ባለመሆኑ ኢኮኖሚው ሙሉ በሙሉ ከሚያመነጨው ገቢ ማግኘት እንዳልቻለች ይነገራል፡፡

ዜጎች ታክስ እንዲከፍሉ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም ዘርፉ በብዙ ዓይነት ብልሹ አሠራሮች የተተበተበ እንደሆነ ይነገራል፡፡

የችግሮቹ መነሻ ዜጎች ስለታክስ ያላቸው ግንዛቤ አናሳ መሆን፣ ለሕግ አለመገዛትና ሕገወጥ ንግዶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዚህ ዙሪያ ገቢዎች ሚኒስቴር ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ‹‹አገራዊ የታክስ አስተዳደር ችግሮች›› በሚል በሚል መነሻ ሐሳብ ሰፊ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ገዙ፣ በታክስ ዙሪያ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

አገራዊ የታክስ አስተዳደር ፈተናዎችን በሦስት ከፍለው ገለጻ ያደረጉት አቶ ሲሳይ፣ አገራዊ የታክስ ሞራል፣ ዝቅተኛ የታክስ ሕግ ተገዥነትና ጥላ ኢኮኖሚ (ኢመደበኛ) በማለት ችግሮቹን ያብራሩታል፡፡

አገራዊ ታክስ ሞራል ዜጎች ታክስ ለመክፈል ያላቸው አመለካከት (ባህል) እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አቶ ሲሳይ ያስረዳሉ፡፡

ባደጉ አገሮች ዜጎች ታክስ የመክፈል ባህሪ (አመለካከት) ከፍተኛ በመሆኑ፣ ‹‹ታክስና ሞት የማይቀር ነው›› የሚል ብሒል እንዳላቸው በምሳሌነት ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ደግሞ በታክስ መክፈል ጉዳይ ያለው አረዳድ ካደጉ አገሮች ጋር ሲነፃፀር የተገላቢጦሽ በመሆኑ፣ ታክስ ለመሰብሰብና ለማስተዳደር ፈተና መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባደጉ አገሮች ታክስ የማይከፍል ዜጋ ከማኅበረሰቡ እንደሚገለል አስረድተው፣ ‹‹ፍሪ ራይደር›› የሚል ስያሜ ጭምር እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታክስ ያለመክፈል ችግርን ለመፍታት ጊዜ ቢወስድም፣ የዜጎች አመለካከት፣ ማኅበራዊ ደንቦችና ማኅበረሰባዊ የታክስ ባህል መገንባት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

እንደ አገር በታክስ ላይ የማኅበረሰቡ አመለካከቶች አሉታዊ መሆኑን፣ ችግሩንም በዘላቂነት ለመቅረፍ የታክስ ሞራል ለመገንባት ግንዛቤ ማስጨበጥና ማሳወቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በሁለተኛነት የተቀመጠው አገራዊ የታክስ አስተዳደር ፈተና የታክስ ሕግ ተገዥነት ዝቅተኛ መሆኑ አንዱ እንደሆነ፣ ዜጎች የሰበሰቡትን ታክስ በአግባቡ ለመንግሥት መስጠት ላይ ያለው ችግር ጎልቶ እንደሚታይ አስረድተዋል፡፡

ደረሰኝ ማጭበርበር፣ ደረሰኝ ያለመቁረጥ፣ ሐሰተኛ ግብይትና ከዋጋ በታች ደረሰኝ በመቁረጥ መንግሥት ከታክስ ማግኘት ያለበትን ገቢ የሚያሳጡ ችግሮችና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየተፈተነበት ያሉ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላው ትልቁ ችግር ብለው ያስቀመጡት ‹‹ጥላ ኢኮኖሚ›› ወይም ኢመደበኛ ግብይት ሲሆን፣ ይህም የንግድ ዓይነት በድብቅና ማንነቱ በማይታወቅ ግለሰብ የሚከናወን ነው፡፡

ኢመደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ በሚስጥር የሚከናወን መሆኑን፣ በዙሪያ የሚሽከረከረው ገንዘብ ባለመታወቁ ከጊዜ በኋላ፣ ምን እንደሚሠሩ ሳይታወቅ ሚሊዬነር የሚሆኑ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዚህ የተሰማሩ ዜጎች ያገኙት ገንዘብ ከኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያገኙ ቢሆንም፣ አገር ማግኘት ያለባትን ገቢ ግን የሚያሳጡና የአገርን ዕድገት ወደኋላ የሚጎትቱ መሆናቸውን አቶ ሲሳይ አስረድተዋል፡፡

የዚህ ንግድ እንቅስቃሴ ትልቁ ችግር በሐሰተኛ ማንነትና ማስረጃዎች በመያዝ የሚሠሩ በመሆናቸው፣ ቁጥጥር ለማድረግና ለሕግ ለማቅረብ አስቸጋሪ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

በዚህ የሚሰማሩ ግለሰቦች ከቀበሌ መታወቂያ ጀምሮ ሐሰተኛ መታወቂያ በማውጣት የሚጠቀሙ ሲሆን፣ ታክስ ዕዳ ሲመጣባቸው ድርጅቱም፣ ግለሰቡም  የሌሉ ሆነው ይገኛሉ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

የጥላ ኢኮኖሚ መገለጫዎች ከላይ የተዘረዘሩት ብቻ አለመሆናቸውን፣ አንዳንድ ጊዜም በሐሰተኛ ማንነት፣ በሞተ ሰው፣ በማይታወቅ ሰው ጭምር ከንግድ ፈቃድ ጀምሮ ሐሰተኛ ማስረጃዎች ይዘው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

አቶ ሲሳይ የተለያዩ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ከአጠቃላለይ ኢኮኖሚው ከ40 እስከ 60 በመቶው በኢመደበኛ ኢኮኖሚ እንደሚሸፈን ገልጸዋል፡፡

‹‹ከአጠቃላይ ኢኮኖሚውን 40 በመቶ የሚያመነጨው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወደ ታክስ እንደማይቀየርና ይህም አገሪቱ ከታክስ ማግኘት ያለባትን ገቢ እያጣች መሆኑን አውስተዋል፡፡

በዚህም ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሐሰተኛ ማንነት ንግድ ፈቃድ የነበራቸው ከ450 በላይ ድርጅቶች መያዛቸውን አስታውሰው፣ በአብዛኛው አስመጪና ላኪ በሚል ታርጋ የተያዙ ናቸው ብለዋል፡፡

እነዚህ ድርጅቶች ያለ ደረሰኝ የሚሠሩና በብዙ የታክስ ማጭበርበር ውስጥ የተወዘፉ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ግብይት ውስጥ የተጨማሪ እሴት ታክስ ዕቃዎቹ በሚስጥር የሚከናወኑ በመሆናቸው፣ ለማጋለጥም ፈታኝ ነው ብለዋል፡፡

የጥላ ኢኮኖሚ (ኢመደበኛ) መቀነስና የመደበኛ ኢኮኖሚውን ማሳደግ ትልቅ መፍትሔ መሆኑን፣ የሌሎችም አገሮች ተሞክሮ የሚያወሳው ይህንኑ ነው ብለዋል፡፡

በዓለም ላይ የጥላ ኢኮኖሚ ማጥፋት ባይቻልም፣ ለታክስ አሰባሰብና ሒደቱን በማዘመን ችግሩን በእጅጉ መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ዝቅተኛ የሕግ ተገዥነት ሌላው ችግር ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት ቢሊዮን ብሮችን አገር እያጣች ነው ይላሉ፡፡

አጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ያህል ታክስ ገቢ ያመነጫል የሚለው ጥናት እንዳልተሠራ ጠቁመው፣ በተጨማሪ እሴት ታክስ በ2011 IMF ላይ ያወጣውን ጥናት ዋቢ አድርገው ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት በተጨማሪ እሴት ታክስ የተሰበሰበው ኢኮኖሚው ያለውን አቅም አመላክቷል፡፡

በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በሁለት ምክንያቶች ያልተሰበሰቡ ተጨማሪ እሴት ታክስ ምክንያት ስምንት በመቶ ለጂዲፒው አስተዋጽኦ የሚደረገውን ገቢ በየዓመቱ እያጣች መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ጥናቱ በሁለት የተከፈለ ሲሆን፣ በሕግ አለማስከበር ምክንያት ያልተሰበሰበው (የሕግ ተገዥነት ችግር) 4.5 በመቶውን እንደሚይዝና አላስፈለጊ የሆነ ከታክስ ክፍያ ነፃ በማድረግ የታጣው ደግሞ 3.5 በመቶውን እንደሚይዝ ገልጸዋል፡፡ ይህም በድምሩ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለ‹‹GDP›› አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል ሀብት ታጣለች፡፡

በሐሰተኛ ደረሰኝና ሐሰተኛ ግብዓት በከፍተኛ ሁኔታ መበራከቱን የገለጹት አቶ ሲሳይ፣ ከመንግሥት ካዝና መልሶ በመውሰድ ጭምር የከበሩ ዜጎች መኖራቸውን አልሸሸጉም፡፡

ከዋጋ በታች ደረሰኝ መቁረጥና ከዋጋ በላይ ደረሰኝ መቁረጥ ሌላው ችግር መሆኑን ጠቁመው፣ መኪናና ሌሎች ግዥዎች በዚህ ችግር የተተበተቡ ናቸው ብለዋል፡፡

ሐሰተኛ ደረሰኝ የሚያዘጋጁ ሰንሰለታቸው ረዥም መሆኑን፣ ሚስጥርነታቸውን ለማግኘት ውስብስብና ከባድ መሆኑን በሥራቸው እንደገጠማቸው ያክላሉ፡፡

በዚህ ሕገወጥ ሥራ የከበሩ መኖራቸውን በመጠቆም፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በጥልቀት መሥራት እንደሚገባና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊሳተፉ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በገለጻው የመፍትሔ ሐሳብ ያስቀመጡት አቶ ሲሳይ፣ ትኩረት ተሰጥቶ አገራዊ የታክስ ሞራል መገንባት እንዳለበት፣ ለዚህም የሚዲያ ተቋሞች ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን አገር ማግኘት ያለባትን ጥቅም ለማስጠበቅ የማኅበረሰቡን ሞራል ከመገንባት አንፃር ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ፣ ደረሰኝ የመጠየቅ ባህል ማሳደግና መንግሥት በጀት አጠቃቀም ክፍተትን በድጋሚ መፈተሽ አለበት ብለዋል፡፡

በተለይ በብዙ ውጣ ውረድ የመጣውን ገቢ መንግሥት መሠረተ ልማት ላይ ሲያውለው በጥራትና በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡

የጥላን ኢኮኖሚ ድርሻ በመቀነስ መደበኛ ኢኮኖሚውን በማበረታታት የሚደርሰውን ከፍተኛ ክስረት ማስቀረት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

በተለይም የጥሬ ገንዘብ ግብይቶችን በማስቀረት ዘመናዊ የክፍያ ዘዴዎችን በመጠቀም ለገዥው (ደንበኞች) ማበረታቻ በመስጠት በተወሰነ መልኩ ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

አገራዊ የታክስ አስተዳደር አቅምን ማጎልበት ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች በከፊል የሚቀርፍ መሆኑን፣ ሚዲያዎች የማኅበረሰቡ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው አቶ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡

በታክስና ተያያዥ ጉዳዮች የሚሠሩ ወንጀሎች ከፍተኛ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ለዚህም ችግር ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና የማኅበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያግዙ ዘዴዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ግብር ለአገር ክብር!›› በሚል መሪ ቃል ከየካቲት እስከ የካቲት ለሚካሄደው የታክስና ጉምሩክ ሕግ ተገዥነት አገራዊ ንቅናቄ ፕሮግራም የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. መጀመሩ ይታወሳል፡፡

የዚህ ንቅናቄ አካል የሆነው ለታክስና ለጉምሩክ ሕግ ተገዥነትና ገቢ አሰባሰቡ ውጤታማነት የሚያግዝ የውይይት መድረክ ከሚዲያ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ተካሄዷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች