Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዋጋ ግሽበት ምጣኔ መስፋት አባባሽ ምክንያቶችና የሚቀርበው አመክንዮ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዋጋ ግሽበት በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ባደጉ አገሮች ጭምር ፈተና መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያም እ.ኤ.አ. በ2023 በዓለም ደረጃ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከተመዘገበባቸው አሥር አገሮች ተርታ ውስጥ የተመደበች ሲሆን፣ በአፍሪካ ደግሞ ከአምስቱ በርዕሰ ጉዳዩ ተጠቃሽ አገሮች ውስጥ አንዷ ናት፡፡

በእያንዳንዱ ከተሞች በተመረጡ ወካይ ከተሞች ውስጥ ያሉ የገበያ ቦታዎች መሠረት ጥናት በማድረግ የተመረጡ ዕቃዎችና አገልግሎቶች የዋጋ መረጃ የሚሰበሰበው የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ወርኃዊ አገር አቀፍ የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ሪፖርትን በየጊዜው ይፋ ያደርጋል፡፡

በተያዘው ሳምንትም በመጋቢት ወር የነበረው የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት፣ የምግብ ዋጋ፣ እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑ ውጤቶች የዋጋ ግሽበት ከቀደመው ወር እንዲሁም ዓምና ተመሳሳይ ወር  ከነበረው ዓውድ ጋር በማነፃፀር ይፋ አድርጓል፡፡

የመጋቢት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር፣ እንዲሁም በጥር ወር 2015 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር ጨምሯል፡፡ ለማሳያ ያህል አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከጥር ወር 2015 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር በ5.7 ነጥብ ከመቶ የጨመረ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የምግብ የኢንዴክሱ ክፍሎች በተመሳሳይ በ7.0 ነጥብ ከመቶ ጭማሪ ተመዝግቦባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት 3.9 ነጥብ በመቶ ያሻቀበ ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከጥር 2014 ዓ.ም. አንስቶ ከሰላሳ ቤቶች ውስጥ ዝቅ አለማለቱን ሪፖርተር የተመለከተው የዋጋ ግሽበት ሁኔታ ገላጭ ሪፖርት ያሳያል፡፡ 

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የመንግሥትን የ2015 በጀት ዓመት የመጀመርያ ስምንት ወራት ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸሞችን በተመለከተ ከሰሞኑ ከቀረበው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ማብራሪያ ጋር በማስተሳሰር በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ይህንን አሥፍሯል።

ባለፉት ተከታታይ 12 ወራትና ከዚያም በላይ የዓለም አቀፍ የምርት ዋጋ መጨመር የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ መገለጫና ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል። ለዚህም ብዙ ምክንያቶች የሚገለጹ ሲሆን፣ በዋናነት የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በዓለም የምግብ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተፅዕኖ በመጥቀስ፣ በኢትዮጵያም ባለፉት ስምንት ወራት የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ ሁኔታ ከፍተኛ የሚባል ነው ሲል ያስቀምጣል።

ይህ እንደጠበቀ ሆኖ በመንግሥት እንደሚቀርበው አመክንዮ ከመጋቢት ወር አስቀድሞ በነበሩት ያለፉት አራት ተከታታይ አራት ወራት የዋጋ ሁኔታ የሚጨምርበት ምጣኔ ቅናሽ ማሳየቱን በማጣቀሻነት በማንሳት፣ ወቅታዊ የዋጋ ንረትን በሚያሳየው አገር አቀፍ የተመሳሳይ ወራት የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ አመላካች ሥሌት መሠረት፣ የ2015 በጀት ዓመት የየካቲት ወር ጠቅላላ 32 በመቶ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች  ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ኢኮኖሚውን አስመልክቶ እንዳሉት፣ በዚህ ሁለትና ሦስት ወራት በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት ገታ ያለ እንጂ  እንደሚባለው አይደለም፡፡

የጤፍ ዋጋ ጨምሯል፣ የስንዴ ዋጋ ጨምሯል፣ የአንዳንድ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ጨምሯል፡፡ ቢሆንም በዚህ ዙሪያ እየተወሰዱ ያሉት የማስተካከያ ዕርምጃዎች ተጠናክረው እየቀጠሉ በመሆናቸው  የሚረጋጋና ወደ ነበረበት የሚመለስ ይሆናል ብለው ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ፡፡

ይህ ይባል እንጂ በመጋቢት ወር በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች የታየው የጤፍ ዋጋ ጭማሪ ወርኃዊ የምግብ ዋጋ ግሽበትን እንዲያሻቅብ ማድረጉን፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታውቋል፡፡

በተጠናቀቀው ወር ከሰብል እህሎች በተለይም የጤፍ፣ እንዲሁም የአትክልና ፍራፍሬና የጥራጥሬ ምርቶች ዋጋ ጭማሪ እንዳሳየ የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የተጋነነ የጤፍ ዋጋ ጭማሪ መታየቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ባለፈው ወር በተለይ በስንዴና በጤፍ ላይ የተፈጠረው የዋጋ ንረትና መናጋት፣ በኢትዮጵያ ያለውን የኑሮ ውድነት ምንጭና ምን ሊደረግ ይገባል ስለሚለው ጉዳይ ብዙ ሲያወያይ ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ የሚታየው የኑሮ ውድነት ወይም የዋጋ ንረት ጤናማ ያልሆነና ኢኮኖሚያዊ መነሻ የሌለው ነው የሚል አስተያየትም ይሰማል፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠመው የዋጋ ንረት  ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በእጅጉ  የሚጎዳ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህ የሆነበት ምክንያት  ባለፉት ሃያ ዓመታት በተከታታይ  በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት እያደገ በመሆኑ፣ በአምራችና በሸማች መካከል ያለውን ርቀት  ማጥበብ ባለመቻሉ፣ ከሌሎች የዓለም አገሮች  ጋር ባለ ግንኙነት ግሽበትም የምትሸምት አገር በመሆኗ ከጦርነት ጋር ተደማምሮ የፈጠረው  ጫና ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ  የተፈጠረው የዋጋ ግሽበት ምርት ባለመኖሩና  ወደ ውጭ በመላኩ ምክንያት አይደለም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የምርት እጥረት የለም፡፡ በየአርሶ አደሩ ቤት ከፍተኛ የምርት ክምችት አለ፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ዋጋ ይጨምራል በሚል የተከሰተና የተያዘ ነው፡፡ በየመንገዱ የተፈጠሩት ኬላዎችም አርቲፊሻል ችግሮች ሆነዋል፤›› ብለዋል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ደግሞ፣ የዋጋ ንረትና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አሁንም የሸማቾች መሠረታዊ ችግር ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ ፍላጎትን ያገናዘበ በቂ ምርት ኖረም አልኖረም በዘፈቀደ በምርቶችና በሸቀጦች ላይ የሚጫን ዋጋ ገበያው እንዳይረጋጋ አድርጎታል በማለት ያስረዳሉ፡፡

ባለሙያዎች አክለውም፣ ገበያን አገናዝቦ ዋጋ ለመስጠት የሚሻ እንደሌለ፣ የተትረፈረፈ ምርት ቢኖር እንኳን ከነበረው ዋጋ ቀንሶ ለመሸጥ ያልተለመደ በመሆኑ የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል ይላሉ፡፡ 

የዋጋ ግሽበት ብዙ ጊዜ ከሚባባስባቸው አንዱና ዋናው ምክንያት በዓላት መሆናቸውን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚገልጹ ሲሆን፣ በዓላትን ተከትለው የሚመጡ የዋጋ ጭማሪዎች በተለይም የምግብ ዋጋ ግሽበትን ከፍ እንደሚያደርጉት ያስረዳሉ፡፡ ከበዓል ማግሥት በምግብ ሸቀጦች ላይ የሚስተዋለው ዋጋ እንደሚያንሰራራ ሪፖርተር ከዚህ ቀደም የበዓል ማግሥት ባደረገበት ወቅት ያነጋገራቸው ሸማቾች ያረጋገጡት ሀቅ ነው፡፡

ሪፖርተር ‹‹ከዚህ ቀደም የኑሮ ውድነት ፖለቲካዊ ገጽታዎች በኢትዮጵያ›› በሚል ባቀረበው ትንታኔ ሙያዊ አስተያየታቸውን ያጋሩ ምሁራን የዋጋ ንረቱና የኑሮ ውድነቱ ከዚህ ቀደምም ቢሆን በንግድ አሻጥርና በሕገወጥ ግብይት የመጣ ነው የሚል አመክንዮ ሲያሰጥ ቢቆይም፣ አሁን አሁን ደግሞ ችግሩ በመንግሥት ሚዛኑን ያልጠበቀና አላስፈላጊ የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነት የመጣ ሊሆን ይችላል የሚል ሙግትም ማንሳታቸውን ማስነበቡ የሚታወስ ነው፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥትን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም መነሻ በማድረግ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የኢኮኖሚ ውድቀት የሚያጋጥመው በመሠረታዊነት በሦስት ጉዳዮች ምክንያት ነው፡፡

የመጀመርያው ከፍተኛ ባለ ዕዳ መሆን (እንደ አገር ለመክፈል የሚያዳግት ዕዳ ሲኖር)፣ ሁለተኛው የእሴት ዋጋ መውረድና  ሦስተኛው የገቢ መቀነስ ናቸው፡፡ በተጨማሪነት የዋጋ ግሽበት ሲታከልበት ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን የሚችል መናጋትን ሊፈጥር  እንደሚችል ዓብይ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት መንስዔ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡  ችግሩ ዛሬ የጀመረ ሳይሆን ለዓመታት ተጠረቃቅሞ አሁን ላይ ገዝፎ የወጣ መሆኑም በተደጋጋሚ ተደምጧል፡፡ ቅጥ ያጣው የግብይት ሥርዓት ብልሽት፣ የደላሎች ጡንቻ ፈርጥሞ መውጣት፣ ገበያን ለማረጋጋት ኃላፊነት የተሰጣቸው መንግሥታዊ ተቋማት መልፈስፈስ፣ አልጠግብ ባይ ነጋዴዎች እንዳሻቸው መሆንና የመሳሰሉት ችግሩን ስለማባሳቸውም ሰርክ የሚገለጽ ጉዳይ ሆኗል፡፡

መንግሥት በዚህ ወቅት ውስጣዊ ቀውሶችና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ሊያስከትሉ የሚችሉትን የዋጋ ንረት ለመቀነስ በጥናት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ሊኖረው እንደሚገባ፣ ይህንም ለማስፈጸም የሚያስችል አቅም መፍጠር የግድ እንደሚለው ሪፖርተር በተለያየ ወቅት ያነጋገራቸው ባለሙያዎች የሚያቀርቡት ምክረ ሐሳብ ነው፡፡

ባለሙያዎቹ አክለውም፣ ገበያው ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ የሚያስችል አሠራር መዘርጋትና ገበያውን ሊያውኩ የሚችሉ ማንኛውም ክስተቶችን መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች ቢያንስ ከውጭ እንዲገቡ በመንግሥት የተፈቀዱ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጠነ ዋጋ እንዲያገኙ ማስቻል ትልቁ የመንግሥት የቤት ሥራ መሆን አለበት ባይ ናቸው፡፡

በጠቅላላው ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ለመቅረፍ አሁንም መንግሥት ቀዳሚው ቢሆንም፣ አሁን ላይ ከሚታየው ሁኔታ አንፃር ግን ለመፍትሔው መንግሥትን ብቻ መጠበቅ ተገቢ አይሆንም የሚለውን ባለሙያዎቹ የሚያሰምሩበት አስተያየት ነው፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት ልክ እንደ ሌሎች አገሮች ሁሉ ለረዥም ዓመታት ሳያቋርጥ የቀጠለው የዋጋ ግሽበት የኑሮ ውድነትን እየወለደ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ግን፣ ውጤቱ ወዴት ያመራል የሚለው ጉዳይ ደግሞ አሳሰቢነቱ የጎላ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች