Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አሁን ዋናው ጥያቄ ኢትዮጵያውያን እንዴት ተግባብተውና የጋራ ራዕይ ኖሯቸው ይቀጥሉ የሚለው ነው›› ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር)፣ የኅብር ኢትዮጵያ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር

በተፎካካሪ ፓርቲ ፖለቲካ ተሳትፏቸው ረዥም ዓመታት አሳልፈዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲን ከመሠረቱትና ከመሩት ሰዎች አንዱ እሳቸው ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ የኅብር ኢትዮጵያ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ ሆነው እየሠሩ ነው፡፡ ፖለቲከኛው ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) ፓርቲያቸው ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ለምን ይቅደም እንደሚል ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በወቅታዊ አገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ዮናስ አማረ ከይልቃል (ኢንጂነር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡የብሔራዊ መግባባት ጉዳይን እንደ አንድ የፖለቲካ አጀንዳ ይዛችሁ መጥታችኋል፡፡ ብሔራዊ መግባባት ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው? ለወቅቱ የሚመጥን የፖለቲካ አጀንዳ ነው?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- ምናልባት ይከብዳል፣ ወይም አጀንዳው ትልቅ ነው ካልሆነ በስተቀር ለወቅቱ የሚመጥን አጀንዳ ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ የብሔራዊ አለመግባባት አለመኖር ውጤት ነው፡፡ ላለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተበየነበት ሁኔታ የተዛባ ግንኙነት አለ ብሎ ነው የሚነሳው፡፡ ጨቋኝና ተጨቋኝ አለ ብለው ነው ኢሕአዴግም ሆነ አሁን ያለው ብልፅግና የመጡት፡፡ ሕገ መንግሥቱም የተጻፈበት ሁኔታ በዚያው መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ የሚታገሏቸውና የሚታገሉላቸው ኃይሎች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሌም በአጥቂና በተጠቂ መንፈስ እንዲኖሩ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን፣ የጋራ ራዕይ ኖሯቸው ወደፊት እንዳያዩ የሚያደርግ ነው፡፡ ስለግል ሕይወታቸውም ሆነ ስለጋራ አገራቸው የጋራ አመለካከት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ ሕወሓት የበላይ ነበር የሚለው የገነነ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የኦሮሞ ልሂቃን የበላይነት አለ የሚል አስተሳሰብ የጎላ ነው፡፡ የዜጎች መፈናቀል፣ መገደል፣ የቤታቸው መፍረስ፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ የተለያየ ጥያቄ መነሳቱ፣ በተለያዩ ቦታዎች በታጣቂዎች የሚደርሰው ጥቃትና ውጥረት ሁሉ የዚሁ ፖለቲካ ነፀብራቅ ነው፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የእርሻ ፖሊሲያችን እንደዚህ ሆነ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲያችን እንደዚያ ሆነ፣ ወይም የሥራ አጥ ቁጥር እንቀንስ፣ የባንክ ምንዛሪ በዚህ ይሁን፣ ወዘተ የሚሉ መደበኛ የፖለቲካ ጉዳዮች የሉም፡፡ አሁን ዋናው ጥያቄ ኢትዮጵያውያን እንዴት ተግባብተውና የጋራ ራዕይ ኖሯቸው ይቀጥሉ የሚለው ነው፡፡ ይህ የመጀመሪያው ጥያቄ መሆን አለበት፡፡ ስለልማት፣ ዴሞክራሲ ወይም ስለብልፅግና ለማውራት ዜጎች በአገራቸው ላይ ተመሳሳይ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የፖለቲካ ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን በአገራቸው ጉዳይ ልዩነታቸውን አክብረው የሚኖሩበት የጋራ ራዕይ መፍጠር የመጀመሪያው ሥራ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ወቅታዊና ትክክለኛም ነው ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ጥያቄው የህልውና አደጋ ገጥሞናል ከሚል ዕሳቤ የመነጨ ይመስላል፡፡ ምን ያህል የህልውና አደጋ ገጥሞናል ትላላችሁ?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- የህልውና ችግር የሚለውን ጉዳይ በምን መንገድ አንዳንዶች እንደሚረዱት ባላውቅም፣ እኔ ግን የህልውና አደጋ አለብን ነው የምለው፡፡ አንድ ሰው በአገሩ ተንቀሳቅሶ መሥራት ካልቻለ ለዚያ ሰው ከዚህ በላይ የህልውና ችግር ምንድነው? ዜጎች የሠሩት ቤትና ዕድሜ ልካቸውን ያፈሩት ሀብት በአንድ ሌሊት ፈርሶ ካደረና መንግሥት ለዚያ ምንም ዋስትና የማይሰጣቸው ከሆነ፣ በአገራቸውና በመንግሥታቸው ላይ የሚሰማቸው ስሜት ምንድነው? ለእነዚህ ሰዎች አገር ምንድነው? ሁለት ዓመት ሙሉ የእርስ በእርስ ጦርነት አድርገህ 20/30 ዓመታት አገርን ወደኋላ ከወሰድክ ከዚህ በላይ የህልውና አደጋ ምንድነው? ፖለቲካ ምን እንደሆነ የማያውቁ ሰዎች ከእነቤታቸው የሚቃጠሉበትና በየቦታው የሚረሸኑበት አገር የህልውና ሥጋት አለበት ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡

የህልውና አደጋ ሥጋት አለብን ብቻ ሳይሆን እዚያው አደጋው ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ በአገር ውስጥ ተፈናቃይ ብዛት ከዓለም የሚቀድመን የለም፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ነው ያለነው፡፡ የጅምላ ግድያ አለ፣ ማንነት ተኮር ጥቃት አለ፡፡ ስለዚህ እኛ የህልውና አደጋ ያጋጥመናል ብለን ሳይሆን፣ እዚያው ውስጥ ነው የምንገኘው በሚል ነው ጉዳዩን የምናነሳው፡፡ በመንግሥት በኩል የሚሰጡ መግለጫዎችም ሆኑ አስተያየቶች ይህን የሚቀርፍ ምንም ዓይነት ምልክት አይታይባቸውም፡፡ የመንግሥት ዕርምጃዎች አንዱን ይዞ ሌላውን የማጥቃት ዓይነት እንጂ፣ ሁሉንም የሚያግባባ የጋራ አገር የመፍጠር ምልክት አይታይባቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥትም በራሱ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያግዛል ያለውን ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አዋቅሮ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ በእናንተ በኩል ይህን የሚተካ ነገር ነው የታሰበው?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- አንድን ነገር በመጀመሪያ የተነሳበት መሠረታዊ ሐሳብ ይወስነዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ በግልጽ መናገር እንደሚቻለው በአገሪቱ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት አለ፡፡ በግልጽ አነጋገር የአገረ መንግሥት ግንባታው ወይም ይህ አገር የተገነባበት ታሪክ የማይስማማቸው ወገኖች አሉ፡፡ አገሪቱ የተገነባችው በአማራና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አመለካከት ነው የሚሉ አሉ፡፡ ይህ ደግሞ በእኛ ላይ በማንነታችን ላይ ጭቆና ጥሎብናል የሚሉ አሉ፡፡ ስለዚህ ይህን የተዛባ ግንኙነት እናርማለን ይላሉ፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት በሚል አገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው የፈጠሯት የሚል አዲስ ዓይነት ዕይታ ፈጥረዋል፡፡ በዚህ መንገድም ኢትዮጵያን ዳግም መቅረፅ አለብን ብለው እየታገሉ ይገኛል፡፡

ይህ ደግሞ ሁሌም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውዝግብ ሲፈጥር ይታያል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ ይቋቋም የሚባለው፣ ቤተ ክርስቲያን በየቦታው የሚቃጠለው፣ የአማራ ብሔር ተወላጆች ሰፋሪዎችና መጤዎች የሚባሉት፣ አገራችሁ አይደለም ውጡ የሚባለው ሁሉ ከዚያ የመነጨ ነው፡፡ በተቃራኒው ግን እነዚህ የሚሳደዱ ሰዎች የኖሩበት ቦታ አገራቸው እንደሆነ ነው የሚያውቁት፡፡ ሶማሌ ወረረ ሲባል ሶማሌ የት እንደሆነ የማያውቀው የጎንደር ገበሬ፣ በሶማሌ ጦርነት ወቅት ሲሞት አገሬ ተወረረ ብሎ ነው የሞተው፡፡ ያ ሰው ሶማሌ አገሩ እንደሆነ ነው የሚያውቀው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ቦታዎች ሰዎችን ነፍጠኛ እያሉ ነው የሚገድሉት ሲባል፣ ልጆች ነፍጠኛ ምንድነው ተብለው ሲጠየቁ እኔ አላውቅም ነው ያሉት፡፡ ይህን መሰሉን ችግር በብሔራዊ መግባባት የሚመለከታቸው ሁሉ ተሳትፈውበት አጠቃላይ የአገረ መንግሥቱ ግንባታ ትርክት በጋራ መሠራት አለበት ነው የምንለው፡፡

መንግሥት የሚለው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጫለሁ፣ ስለዚህ ሲንከባለሉ ለቆዩ ጥያቄዎች ብቻ መልስ ለማግኘት ራሴ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁሜያለሁ ነው የሚለው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ችግር አለበት፣ በዚያ የተነሳ እየተጠቃሁ ነው የሚል ወገንን በሕገ መንግሥቱ መሠረት እኔ መንግሥት ነኝና የምክክር ኮሚሽን መሥርቻለሁ የሚል አካል መልስ ሊሰጠው አይችልም፡፡ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር በተለያዩ አገሮች የተደረጉ ጥረቶች ብዙ ጊዜ ከከሸፉበት ምክንያት፣ ዋናው መንግሥት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በሚያደርገው ጫናና ጣልቃ ገብነት የተፈጠሩ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሲመሠረት በሒደቱ አልተሳተፋችሁም፡፡ ሕጉ ሲፀድቅ፣ አባላቱ ሲመረጡና መዋቅሩ ሲደራጅ ግብዓት በመስጠትም ሆነ የማሻሻያ ጥያቄ በማንሳት አልተሳተፋችሁም?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- መንግሥት ለዚህ ፈቃደኛ አይደለም፡፡ መጀመሪያ አነሳሱም ልክ አይደለም፡፡ መንግሥት ተነሳሽነቱን ቢወስድም ነገር ግን የተቃዋሚዎችን ግብዓት ለመቀበል ዝግጁ አልነበረም፡፡ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ላይ ከፍትሕ ሚኒስቴር የመጡ ሰዎች አስተያየት ለመቀበል ሞክረዋል፡፡ ሆኖም ያዘጋጁትን ሰነድ እንኳን ለተሰብሳቢው ለመበተን አልፈቀዱም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የተሰጣቸውን አስተያየትም ሰነዱ ውስጥ ማስገባት አልፈለጉም፡፡ ነገሩ ሁሉ በመንግሥት ፍላጎት በዋናነት በብልፅግና ፍላጎት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ራሳችንን ማታለል ካልፈለግን በስተቀር በተደጋጋሚ እንደታየው ብዙ እንዲህ ያሉ አካሄዶች ከሽፈዋል፡፡ የወሰንና የማንነት ኮሚሽን የሚባል ተቋቁሞ ነገር ግን የት እንዳለና ምን እንደሠራ አናውቅም፡፡ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ካርዲናሉና እነ የትነበርሽ ንጉሤ ያሉበት የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ተቋቁሞ ነበር፡፡ አሁን ግን የት እንዳለ አናውቅም፡፡ አሁንም ቢሆን ይህ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚባለው እስካሁን ምንም የሠራው ነገር የለም፡፡ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በሚመጥን መንገድም አይደለም አወቃቀሩ፡፡   

ሪፖርተር፡- የተሳካ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ምን ቢደረግ ይሻላል?  

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- መንግሥት ጉዳዩን በሥልጣን ለመቆየት ሊጠቀምበትና የእሱን ፍላጎት ያማከለ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ ዋናው ችግር ይህ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአገሪቱ ችግር በሥልጣን ላይ ያለ አንድ የፖለቲካ ኃይል ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የሚመለከት በመሆኑ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች የዕርቅ ኮሚሽን የሚቋቋምበትን መሠረት በጋራ መሥራት አለባቸው፡፡ የአንድ መንግሥት ጉዳይ አይደለም፣ የፖሊሲ ጉዳይም አይደለም፡፡ ጉዳዩ አጠቃላይ የአገርን ምሰሶዎች የማቆም ሒደት ነው፡፡ ስለዚህ በሒደቱ ላይ የሚመለከታቸው ሁሉ የራሳቸው ድምፅ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ኮሚሽኑም ቢሆን ሁሉም ወገን የእኔ ነው የሚለውና የሚስማማበት መሆን አለበት፡፡

ኅብር ኢትዮጵያ ከመጀመሪያውም መንግሥት ቀድሞ ወደ ምርጫ ሳይገባ፣ ይህ ሁሉ ጦርነት ሳይፈጠር፣ መጀመሪያ እንነጋገርና በምንሄድበት መንገድ ላይ የጋራ ፍኖተ ካርታ ይኑረን ሲል ቆይቷል፡፡ መንግሥት ግን ለሥልጣኑ ሲል ጉዳዩን ባለመደገፉ አገራችንን ከባድ ኪሳራ ውስጥ ከቷታል፡፡ ጦርነቱ፣ የሰዎች ሞት፣ የኢኮኖሚው መጎዳትና ከዓለም መገለሉ የመጣው አንድ ቡድን ወይም ግለሰቦች በሥልጣን በመቀጠል ፍላጎት ነው፡፡ በእኛ እምነት ማዕቀፉ መሆን ያለበት የኢትዮጵያ ችግር ሥልጣን ላይ ካለው የገዥ ፓርቲ አቅም በላይ በመሆኑ መፍትሔውም ከዚያ ያለፈ መሆን አለበት፡፡ የኅብር ኢትዮጵያ መነሻ ሊሆን ይችላል፣ ወይም ኦፌኮ የሚያቀርበው አማራጭ ሊሆን ይችላል፣ አልያም አንድ የሰብዓዊ መብት ድርጅት የሚሰጠው ሊሆን ይችላል፡፡ ሁሉም መጥቶ በጋራ ውይይት በሰጥቶ መቀበል ፀድቆ ሁሉም ያመነበት የጋራ ምክክር ኮሚሽን መፍጠር ይቻላል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም የሽግግር ጊዜ መንግሥት ይቋቋም ስትሉ ነበር፡፡ አሁን የምትሉት ከዚያ ጋር ተመሳሳይ ነው?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- አንድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሕዝብ ድምፅ ተመርጫለሁ የሚል መንግሥት ነው ያለው እኮ?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- አንደኛ ኢትዮጵያ ምርጫ የምታደርግበት ጊዜ ላይ አይደለችም፡፡ ምርጫ የምታደርገው እኮ በሕገ መንግሥቱ ተስማምተህ፣ በአገር ግንባታ ሒደት ላይ ተስማምተህ ነው፡፡ ምርጫ ለአራትና ለአምስት ዓመታት የምትፈልገውን አስተዳደር የምታመጣበትና የምትሸኝበት የዴሞክራሲ ጨዋታ ሒደት ነው፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ነገር እኮ ከምርጫ ባለፈ ነው፡፡ ዜጎች በጅምላ የሚፈናቀሉት፣ ይህ ቦታ የእኔ ነው፣ ይህ አገር የእኔ ነው የሚባለውና የመገንጠል ጥያቄ ገናና የሆነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በትግራይ ራሱ ገና የፖለቲካ ውይይት እኮ አልተጀመረም፡፡ የፖለቲካ ውይይት ሲጀመር እኮ የመገንጠል ጥያቄ ሊነሳ ሁሉ ይችላል፡፡ እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ከምርጫ በፊት ኢትዮጵያ ልትሠራቸው የሚገቡ የቤት ሥራዎች ናቸው፡፡

ወደ ምርጫ ለመግባት ብዙ ሒደቶች መታለፍ አለባቸው፡፡ የጋራ ሕገ መንግሥት ሳይኖረን፣ አገራችን የምንገነባበት መንገድ ሳይቀመጥ፣ የምንደራጅባቸውና የዴሞክራሲ ተቋማትን መሠረት ሳንጥል ምርጫ በምን መንገድ ነው ልናካሂድ የምንችለው? ብሔራዊ ዕርቅ መፈጠር አለበት፣ የሽግግር ፍትሕ መደረግ አለበት፣ የሚያግባባን የጋራ ሕገ መንግሥት መኖር አለበት፡፡

ይህን ሁሉ ደግሞ ለማድረግ እኛ ገዥው ፓርቲ ይውጣ አላልንም፡፡ የእኛ የመጀመሪያ ፕሮፖዛል የገዥው ፓርቲ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ይሁን ነው የሚለው፡፡ በእኛ አገር ገዥው ፓርቲ ሁሉንም የሥልጣን አካልና መዋቅር የተቆጣጠረ ስለሆነ፣ እሱን ልክ እንደሌለ ነገር ወደ ጎን መግፋት ብዙ ነገሮችን ያደናቅፋልና ከዥው ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን እንዲይዝ ብለናል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ደግሞ ሁለት ሰዎች ይያዙ ነበር ያልነው፡፡ አንዱ የብሔር ፌደራሊዝምን የሚወክል፣ ሌላኛው ደግሞ በዜግነት መደራጀትን ወይም በሲቪክ ናሽናሊዝም የሚያምን እንዲሆን ዕቅድ አቅርበናል፡፡

ብሔራዊ ኮሚሽኑ ደግሞ ከሚመለከታቸው ከሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች በንፃሬ እንደ ድርሻቸው የሚወከሉበት እንዲሆን፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ ደግሞ የመከላከያ፣ የደኅንነት፣ የውጭ ጉዳይ፣ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን፣ የእውነትና የዕርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን፣ የምርጫ ቦርድ፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የመሳሰሉ ያልተግባባንባቸው መዋቅሮችን የሚገነቡ ኮሚቴዎች እንዲኖሩት ጠይቀናል፡፡ ይህ ሒደት ሳይቋረጥ ለሁለት ወይም ለሦስት ዓመታት ከተሠራና ከተገባደደ በኋላ ወደ ምርጫ መግባቱ የተሻለ ነው ብለን መክረናል፡፡ አሁን ባለው ሐዲድ፣ ባለው ሕገ መንግሥት እየሄድን ጥያቄ ካላችሁ እኔ በጎንዮሽ እመልስላችኋለሁ የሚል አካሄድ ነው መንግሥት የተከተለው፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ የት እንዳደረሰን እያየነው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ጊዜ ስለሽግግር ተጠይቀው እስከ ምርጫው ድረስ የነበረው ሒደት መሆኑንና እሱ ታልፎ በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ ሕጋዊ መንግሥት መመሥረቱን ተናግረዋል፡፡ ተመልሶ ወደ ሽግግር ጊዜ ሒደት መግባት እንዴት ይቻላል?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- አንተ የምታምነውና እንደ እግዚአብሔር ቃል የምትቀበለው የእሳቸውን ንግግር ከሆነ ያ ሊሆን አይችልም፡፡ አገሩ የ120 ሚሊዮን ሕዝቦች አገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እሳቸውን የማመንና ያለማመን ጉዳይ ሳይሆን የሽግግር ጊዜ አስተዳደር ለመፍጠር ጊዜው አልረፈደም ወይ ከሚል ነው ጥያቄው የተነሳው፡፡

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- እና ሌላ ምን ምርጫ አለን? ሰዎች እንደ ግለሰብ ብዙ ነገር ሊሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እንደ አገር በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው እውነታ ያን ሀቅ ላይነግረን ይችላል፡፡ ትግራይ በጦርነት ውስጥ ነው ያለፈው፡፡ ሰሞኑን በአማራ ክልል የሚታየው ሁኔታ በሙሉ በመንግሥት ላይ ተቃውሞ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የሚሆነውን የምታየው ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ ብዙ ሕዝብ ቤቱ እየፈረሰ እየተፈናቀለ ነው፡፡ በየቦታው የክልልነትና የአዲስ አደረጃጀት ጥያቄ ተወጥሮ ያለበት ነው፡፡ እሳቸው የሚሉት ነው ወይስ የምናየው ነው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሚለው መታየት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በፓርላማ ጭምር ስለሽግግር ጉዳይ ተጠይቀው፣ እስከ ምርጫው ድረስ የነበረው ጊዜ ነበር ያ ሒደት ብለው እሱ መታለፉንና በሕዝብ የተመረጠ ሕጋዊ መንግሥት መቋቋሙን መልሰው ነበር፡፡

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- እንደተባለው ችግሮቻችንን አልፈንና ተስተካክሎልን ከሆነ ያው በጀመርነው መሄድ ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ግን በእኔ ግምት በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚው ተሰባብረን ልናልቅ ጫፍ ላይ ነው ያለነው፡፡ አገር ለማፍረስ ከፈለግን ማን ያቆመናል የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የበቀደም ንግግር መንግሥትን ለማውረድ በቂ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ እያልክ ተመርጫለሁ አትንኩኝ ልትል አትችልም፡፡ ምርጫ እኮ የሕዝብ ተቀጣሪነትና ኃላፊነትን የሚጭን ነው፡፡ አገሪቱ የተገነባችው በሦስት ሺሕ ዓመታት በብዙ ሰዎች የደም መስዋዕትነት ነውና የእርስዎ ንግግር አግባብ አይደለም ተብሎ ሥልጣን ልቀቅ ሊባሉ ይችላል፡፡ የሥልጣንና የመመረጥ ጉዳይ ከተነሳ ፓርላማውን እኮ ራሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕግ ሊበትነው ይችላል፡፡ ይህን ቀላል ነገር ማለትም የመመረጥና ያለመመረጥ ጉዳይ በአገር ላይ እየደረሰ ካለ አደጋ ጋር ማወዳደር አይቻልም፡፡ ተመረጠ የተባለው ብልፅግና በቀላሉ በሕግ ሥልጣኑን ሊያጣ ይችላል፡፡ የአገሪቱ አደጋ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጭምር የተሳተፉበት የምርጫ ሒደት ነው ያየነው፡፡ የሽግግር ጊዜ ሒደቱ ታልፏል ብለው ባያምኑ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሒደቱ ለምን ተሳተፉ? የሽግግር ጊዜ ታልፎ ምርጫ ተደርጎ የተለያዩ ፓርቲዎች ሥልጣን የተጋሩበት አሁን ያለው ሥርዓት መገንባቱን አትቀበሉትም?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- ጦርነት ውስጥ እኮ ነው ያለነው፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) በምርጫ አልነበረም ወደ ሥልጣን የመጡት፡፡ አቶ ኃይለ ማሪያም የሚመሩት ኢሕአዴግ በ2007 ዓ.ም. በምርጫ አሸነፍኩ ብሎ 2008 ዓ.ም. ግን የሕዝብ ተቃውሞ ተነሳበት፡፡ በዚያ የሕዝብ ተቃውሞ አማካይነት ነው ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን የመጡት፡፡ አቶ ኃይለ ማሪያም ከነበሩበትም የባሰ ነው አሁን የምንገኝበት የፖለቲካ ሁኔታ፡፡ በዚያ ጊዜ ቢያንስ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ አልነበርንም፡፡ ሰዎች በጅምላ የሚታረዱበትና የሚፈናቀሉበት ደረጃ ላይ ቢያንስ አልደረስንም፡፡

ለሽግግሩ ዕድሉ ተሰጥቶ ነበር ቢባል እንኳ እንዳየነው ግን አልሠራም፡፡ በጊዜው እኛ እንደማይሆን ብናውቀውም ሕዝብም ወዷቸውና ተቀብሏቸው ስለነበር ሽግግሩን ለመምራት ዕድሉን አግኝተው ነበር፡፡ ጊዜ እንስጣቸው፣ እያዋከብን በጥርጣሬ ከምንሄድ ዕድሉ ይሰጣቸው ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሞክሯል፡፡ በመጨረሻ ግን ያለንበት ሁኔታ ላይ ነው የወደቅነው፡፡ ተመርጫለሁ ማለትም አልሠራም፡፡ በእኛ ግምገማ ደግሞ የኢትዮጵያ ችግር በምርጫ ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ፣ ከዚያ በፊት የቤት ሥራችንን በደንብ ሠርተን እንለፍ ነው እያልን ያለነው፡፡ የቤት ሥራችንን በአግባቡ ባለመሥራታችን እኮ ነው መንግሥታቸው እንቅፋት እንዲገጥመው ያደረገው፡፡ የቤት ሥራችንን እንደ አገር ሠርተን ቢሆን ኖሮ አሁን የገጠሙን ችግሮች ብዙ ባልነበሩ ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ ሦስት ዓመታት ጠብቀን ሌላ ምርጫ ብናደርግ ችግሩ አይቀረፍም፡፡ የመምረጥና የመመረጥ አይደለም ጉዳዩ፡፡ በስህተታችን አንድ አሰቃቂ ጦርነት ዓይተናል፡፡ ከዚህ ካልተማርን ደግሞ ለ20 ዓመታት ለሚዘልቅ ሌላ ዙር ጦርነት ልንዳረግ እንችላለን፡፡ ይህ መቀልበስ ካለበት ደግሞ ከግለሰቦች ሥልጣን፣ ከቡድኖች ሥልጣን፣ ከተራ ሽኩቻና ከግትርነት ባለፈ የአገሪቱን ሁኔታ ሰፋ ባለ መንገድ ማየትና መፍትሔ መፈለግ ይጠይቃል የሚል ነው የኅብር ኢትዮጵያ አቋም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ለመድበለ ፓርቲ ወይም ለፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት አመቺ ሁኔታ አለ?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- ግራ አጋቢ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የትግሉ ሁኔታና እንቅስቃሴው አስቻይ አይደለም የሚል ግምገማ ላይ ነው የሚያደርሰን፡፡ ሕዝቡ የዚህ ፓርቲ ወይም የሌላ ፓርቲ ደጋፊ በማይባል ደረጃ ነው ጥያቄ እያቀረበ ያለው፡፡ ሕዝብ እንደ አጠቃላይ የጋራ ጥያቄ እያነሳ ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ የአማራ ክልል ሁኔታን ብናይ በውስጡ የእኛን ጨምሮ አብንን፣ ብልፅግናን፣ ኢዜማን ወይም ሌላ ፓርቲ ሊደግፍ ይችላል፡፡ ነገር ግን የአማራ ጥያቄ በሚለው ጉዳይ ላይ እንደ ሕዝብ ሲቆም እየታየ ነው፡፡ ይህ ማለት በአገሪቱ ያለው የሕዝቡ ጥያቄ ከፓርቲዎች አልፏል ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በመንግሥት ፍርኃት የተነሳ የተፈጠረው የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ዜጎችን መንቀሳቀስም እየከለከለ ነው፡፡ እንኳን የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ይዘህ፣ የሚደግፍህና የማይደግፍህ ባለበት ፖለቲካ ለማራመድ ቀርቶ መደበኛ ሕይወትም የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ሕዝብ ማደራጀትና መንቀሳቀስም ከባድ በመሆኑ የፓርቲዎችን ሥራ እጅግ ከባድ አድርጎታል፡፡

አገሪቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ካለች፣ ሕዝብ በጋራ ጥያቄ እያነሳ ከሆነ የፖለቲካ ትግሎችን የተደራጀ የሚያደርግና አቅጣጫ የሚሰጥ ወገን ከሌለ አደጋ የሚፈጠር በመሆኑ የፓርቲዎች አስፈላጊነት የግድ ነው እንድትል ያደርግሀል፡፡ ጥያቄዎች እየበዙ ከሄዱና ሕዝብ የሚያዳምጠው የፖለቲካ ድርጅት ከሌለ ቀውሱ ይብሳል፡፡ ሕዝቡን አቅጣጫ የሚሰጥ፣ በተለያዩ ሁኔታዎች ወክሎ የሚደራደር ድርጅትና ተቋማት ከሌሉ ነገሩ ወደ ሥርዓተ አልበኝነት ሊያመራ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሥርዓተ አልበኝነት ሲሉ ምን ማለት ነው?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- ከሞላ ጎደል ገብተናል፡፡ ያን ለመቋጨትም ቢሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቱ ያስፈልጋሉ፡፡ ነባራዊ ሁኔታውና የሕዝቡ ጥያቄ ደግሞ ተቃዋሚዎችን አላስፈላጊ አድርጎ ተሻግሮ ሄዷል፡፡ እነዚህን ነገሮች አስታርቀን መሄድ አለብን፡፡ ሕዝቡም ጥያቄውን የሚያቀርብበት መንገድ መቀጠል አለበት፡፡ ተቃዋሚዎች ደግሞ ራሳቸውን አደራጅተውና አጠናክረው ሕዝብ ሊሰማቸው በሚችል ተክለ ቁመና ላይ መገኘትና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን ማጠናከር አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወዴት እየገሰገሰ ነው ይላሉ?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- በኢትዮጵያ አሁን በሚሆነው ሁኔታ ባዝንና ብጨነቅም ነገር ግን ብዙም አልገረምም፡፡ እኔም ሆነ ፓርቲያችን ከመጀመሪያው ጀምሮ ይህ እንደሚመጣ ስንወተውት ነበር፡፡ ለውጥ አለ/የለም በሚለው የመጀመሪያ ጥያቄ ላይ የነበረኝ ግንዛቤ ኢሕአዴግ እየተሰባበረ ነው የሚል ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ተሰባበረ እንጂ ብልፅግና የሚባል አዲስ ድርጅት አልተፈጠረም፡፡ ኢሕአዴግ ጠንካራ ድርጅት ነበር፡፡ ያን ጠንካራ ድርጅት አስኳሉን ይዞ የቆየው ደግሞ ሕወሓት ነበር፡፡ ሕወሓት ደግሞ በሕዝብ ትግልና በውስጣዊ ሽኩቻ ጠንካራ ማዕከላዊነት ከነበረው ድርጅት ተፈንቅሎ ወጥቷል፡፡

ሕወሓትን ለመፈንቀል በሚል ሌሎች ድርጅቶች ተሰባስበዋል፡፡ ነገር ግን ያልታረቁና የጠራ ራዕይ የሌላቸው ስለሆኑ ጊዜውን ጠብቀው እርስ በእርስ ይሻኮታሉ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመበታተን ውስጥ ነው እንጂ ያለው ወደ መሰባሰቡ አልገባም፡፡ መበታተኑና መሰነጣጠቁ አብቅቶ መሰባሰብ እስኪጀምር ደግሞ ቀውሱ ይቀጥላል የሚል ነበር ግምገማዬ፡፡ መጀመሪያ ሕወሓት ወጣ፡፡ አሁን ደግሞ በኦሮሞና በአማራ ብልፅግና መካከል በሚመስል ሁኔታ ሽኩቻ ይታያል፡፡

ሰዎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የሚከለከለው፣ መንግሥትን ለመገልበጥ እንቅስቃሴ እተደረገ ነው የሚባለው፣ ሸገር የሚባል ከተማ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገነባው፣ ሰዎች የሚፈናቀሉት የመሳሰለው ሁሉ ከኢሕአዴግ የተነሳው መሰነጣጠቅ ሁለተኛ ምዕራፍ መቀጠሉን አመላካች ይመስላል፡፡ ይህ በአግባቡ እስካልተቋጨ ድረስ የመሰነጣጠቅ ሒደቱ የሚፈጥረው ቀውስ ይቀጥላል፡፡

ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያ የምትገኘው በመሰነጣጠቅ ፖለቲካ ውስጥ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ያኔ በኢሕአዴግ ውስጥ የሕወሓት የቡድን አምባገነንነት ነበር፡፡ የጋራ አመራር ነበረው፣ ማዕከላዊ የሆነ፣ ሌሎች የሚታዘዙለትና የአሸናፊነት ሥነ ልቦና የሚንፀባረቅበት ሕወሓት ነበር፡፡ ከጦርነቱ በኋላ የተወሰኑ የሕወሓት አባላት ተነጥለው ወጡ፡፡ እነ ስዬና ገብሩ የመሳሰሉ ሰዎች ሲወጡ ከቡድን አምባገነንነት ወደ አንድ ግለሰብ አምባገነንነት ቅርፁ ተለወጠ፡፡ ይህ ግለሰባዊ አምባገነንነት ደግሞ አቶ መለስ ዜናዊ ሲሞቱ ተቆረጠ፡፡

አቶ ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ሲመጡ የሕወሓት የበላይነትና የኃይል ሚዛኑ ማዕከላዊነት ሲጠፋ የተለያዩ ኃይሎች ሽኩቻ ተፈጠረ፡፡ ሽኩቻው ተባብሶ በመቀጠሉና አቶ ኃይለ ማሪያም ተቋቁመው ለመቀጠል የማይችሉበት ደረጃ ሲደርሱ ደግሞ፣ ሕወሓት ተገፍቶ ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መጡ፡፡ ከዚያ ወደ ጦርነት ተገባ፡፡ ከጦርነት በኋላ እንደምናየው ደግሞ የኦሮሞና የአማራ ብልፅግና አዲስ ሽኩቻ የተፈጠረ ይመስላል፡፡

እኛ የጋራ ራዕይ ይኑረን የምንለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የነበረች አገር ናት፣ ስለዚህ ነገሮችን አስተካክሎ አገሪቱን ማስቀጠል ይቻላል የሚልና አይ ኢትዮጵያን እንደ አዲስ እንፈጥራለን የሚል ሁለት ተቃራኒ ኃይል ነው ሥልጣኑን የያዘው፡፡ ያ ደግሞ መልክ ባለመያዙ አሁን ላይ ሌላ ዙር መሰንጠቅ ጀምሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የሚሉት ነገር የመሪ ፖለቲካ ኃይሉን እንጂ የአገሪቱን ፖለቲካ መለወጥ የሚያሳይ ነው?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- ይያያዛል፡፡ አገሪቱ የምትገዛበትና የሚሻኮቱበት አመለካከት ሕገ መንግሥታዊ ሆኗል፡፡ የቡድኖቹ ብቻ ቢሆን ቢሻኮቱ በአገር ላይ የሚፈጥረው ችግር ያነሰ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥታዊ ቅርፅ ይዟል፡፡ ለዚህም ነው የሽግግር ጊዜ ፈጥረን የጋራ ራዕይ፣ የጋራ ሕገ መንግሥት፣ የጋራ ፍኖተ ካርታ አበጅተን ከዚህ ለመውጣት ጉዞ እንጀምር የምንለው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የጋራ ፍኖተ ካርታችን አይደለም፡፡ ከ30 ዓመታት በላይ የተጓዝንበት ፖለቲካ የመሪ ፖለቲካ ኃይሉ ብቻ ሳይሆን ተቋማዊም ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት ከፈለጉ ለመገንጠል ይችላሉ የሚለው አመለካከት አሁን የምንገኝበትን ሁሉ ችግር የፈጠረ ነው፡፡ ወይ ይህንኑ ተቀብሎ መጓዝ መቀጠል ነው አልያም ሌላ አማራጭ መከተል ነው፡፡

የብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ ማቋቋም የመነጨው ከዚህ ነው፡፡ ክልሎች ወደ ኮንፌዴሬሽን የሚጠጋ በሚመስል ሁኔታ አንዱን ባለአገር ሌላውን አገር አልባ የሚያደርጉት ሁሉ ከዚህ የሚነሳ ነው፡፡ ይህ አይሁን ዜግነትና አገር የጋራ ይሁን ብለን ቋንቋና ብዝኃነት የተከበረበት ሚዛኑን የጠበቀ ሥርዓት እንገንባ እያልን ነው፡፡ ይህን የምንፈጥርበት ዕድል እስከሌለ ድረስ ችግሩ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ እኛ ትክክል ነን ለማለት ጠንቋይ ሆነን ሳይሆን የነገሮችን ወዴት አቅጣጫ ማዝገም የሚጠቁሙ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም የነበረው ኢሕአዴግ ልማታዊ ዴሞክራሲን እከተላለሁ ይል ነበር፡፡ ከእሱ የቀደመው ደግሞ ኮሙዩኒስታዊ መንግሥት ነበር፡፡ አሁን ያለው መንግሥት ምን ዓይነት ጠባይ ያለው መንግሥት ነው?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- ምንም ጠባይ የለውም፡፡ ጠባይ ካለው አቋም የሌለውና ተለዋዋጭ በሚል ነው ሊገለጽ የሚችለው፡፡ የፖሊሲው መሠረት ማሳትና ማምታታት (ዲሴፕሽን ኤንድ ማኒፑሌሽን) ነው፡፡ ተገማች አለመሆንን የሚከተል ነው፡፡ ሕወሓቶች ጋ ሲሄድ ሌላ ነገር ማውራት፣ ለኦሮሞዎች የሚያወራው ሌላ፣ ለአማራው የሚናገረው ሌላ፣ ለቻይኖቹ የሚያወራው ሌላ፣ ለፈረንጆቹ ደግሞ የሚያወራው ሌላ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት የሚገለጸው አቋም የለሽና የማይገመት ብዙዎችን ነገሮች በታክቲክ ብቻ እያለፈ ዛሬን የማደርና ሥልጣንን ብቻ ያተኮረ ተብሎ ነው ሊገለጽ የሚችለው፡፡ ግልጽ የሆነ ራዕይ የሌለውና ሕዝብን ማሰባሰብ ያልቻለ ነው፡፡ ጊዜያዊና ስሜት ቀስቃሽ ጉዳዮች ላይ እያተኮረ የሚዋትት ድርጅት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ አሁን ያለው የኃይል አሠላለፍ ምን መልክ እየያዘ ነው ታዲያ?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- በአንድ አገር ውስጥ በፖለቲካ ልዩነትና በፕሮግራም አለመግባባት ቢኖር ምንም ማለት አይደለም፡፡ ይህ ጤናማ ነው፡፡ ፓርቲዎች አንዱ ከሌላው በጋራ ሊቆሙ ይችላሉ፡፡ በጋራ መንግሥት እስከ መመሥረት ድረስ ሊሠለፉ ይችላሉ፡፡ በእስራኤል ለምሳሌ መንግሥት ይሠራል፣ ይፈርሳል፡፡ ስምንት ፓርቲዎች ሆነው ኔታኒያሁን ለመግፋት ሞከሩ፡፡ ናፍታሌም የተባለው መጣ፡፡ አሁን ደግሞ ኔታኒያሁ መጥቷል፡፡ ይህ ጤናማ የፖለቲካ ሁኔታ ባለበት አገር የሚታይ ነው፡፡ እኛ አገር ግን የብሔረሰብ ፖለቲካ አደረጃጀት በሰፈነበት፣ እንዲሁም የአገር ምሥረታ ሒደት ላይ ባልተግባባንበት ሁኔታ የኃይል አሠላለፍ ልዩነት ሲመጣ በጣም አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡ በኃይል አሠላለፍ ምክንያት በጦርነት ውስጥ ነበርን፡፡ አሁን ደግሞ በኃይል አሠላለፍ የተነሳ አለመተማመን ሲፈጠር እያየን ነው፡፡ የሰሞኑ የአማራ ክልል የተቃውሞ ሠልፍ ካለመተማመን የመነጨ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣኔን ሊቀሙኝ ነው ማለት የመጣው ከዚህ ነው፡፡

አሁን በቀጣናው ብዙ ዓይነት ተዋንያን አሉ፡፡ ኤርትራን ይዘው የተሠለፉ የምሥራቅ ኃይሎች አሉ፡፡ ሕወሓትና ብልፅግናን ይዘው ምዕራባዊያኑ የኤርትራን የቀጣናዊ ሚና ለመገደብ ሲንቀሳቀሱ ይታያል፡፡ ምዕራባዊያኑ ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዳትገባና በቀጣናው ያላት ሚና እንዲዳከም ይፈልጋሉ፡፡ እንደ ቻይናና ሩሲያ ያሉ ኃይሎች ደግሞ በቀይ ባህርና በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ያላቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ኤርትራንም ይፈልጋሉ፡፡

መጀመሪያ ሕወሓትን በመግፋቱ ረገድ የአሜሪካ መንግሥት እጅም ነበረበት፡፡ በኋላ ግን የተዳከመውን ሕወሓትን ሲደግፍ የታየው የኤርትራን ሚና ለማዳከም ጭምር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በእነዚህ የኃይል አሠላለፎች መካከል የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች የሚያስደስተው ብቻ ሳይሆን፣ የሚያስከፋው ወገንም ሊኖር ይችላል፡፡ አውሮፓዎችና አሜሪካኖቹ ሕወሓትን እየደገፉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አስታርቀው ለማስቀጠል ሲሠሩ፣ በተቃራኒው ሕወሓትን መልሰው አምጥተው በላያችን ላይ ሊጭኑብን ነው የሚል የአማራና የኤርትራ ኃይል አለ፡፡ ይህ ደግሞ ውጥረት እያመጣና ምልክቶቹም እየታዩ ነው፡፡

ቻይናን የመሳሰሉ ኃይሎች አሜሪካን በይፋ ለመጋፈጥ የተዘጋጁበት ወቅት እየመጣ ይመስላል፡፡ በአሜሪካ የውጭ ግንኙነቱን አሁን የሚመሩት ደግሞ ኒዮ-ኮንዘርቫቲቭ የሚባሉት አሜሪካ የዓለም ኃያል ሆና መቀጠል አለባት የሚሉ ናቸው፡፡ በየትኛውም ቦታ የሚፈጠር ነገር በእኛ ቁጥጥር ሥር መሆን አለበት የሚሉ የሪፐብሊካንና የዴሞክራቶች ጥምረት ያለው ቡድን ነው፡፡ ኃይለኛ የሆነ የውጭ ግንኙነት ዕርምጃን የሚከተሉ በመሆናቸው በተቃራኒው ከምሥራቁ ዓለምም ጠንካራ አፀፋዎችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን በጥንቃቄ በማስተዋል ችግሮችን መፍታት ካልቻለች እንደ ሌሎች አገሮች ወደ ግጭት ልትገባ ትችላለች፡፡

ሪፖርተር፡- በአማራ ክልል ከሰሞኑ ከልዩ ኃይል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ምን ይላሉ?

ይልቃል (ኢንጂነር)፡- የመንግሥት ተቋም ቢሆንም እንኳን ልዩ ኃይልን ትጥቅ የማስፈታቱ ዕርምጃ ጊዜውን ያልጠበቀ ነው፡፡ ጉዳዩ ከሕወሓትና ከፕሪቶሪያው ስምምነት ጋር በሥጋት የሚታይና ብዙ ሰው ያልደገፈውና በድብቅ የተካሄደ ነው፡፡ ብዙ ነገሩ ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ አጠቃላይ ሕዝባዊ ንቅናቄን አምጥቷል፡፡ ይህ ነገር ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዳይወስደን ሥጋት አለኝ፡፡ ያለ መተማመን ምልክቶች ማሳያ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ለወትሮው አማራ የሚታማው አንድ አገር፣ አንድ መከላከያ፣ ወይም አንድ ፀጥታ አስከባሪ በሚል አገራዊ የፖለቲካ ዝንባሌ ነበር፡፡ ዛሬ አንድ ወጥ ሕግ አስከባሪ ይፈጠር ሲባል ልዩ ኃይሉ አይነካ የሚል ተቃውሞ ከአማራ ክልል የተፈጠረው ካለመተማመን በመነጨ እንጂ በሌላ አይመስለኝም፡፡ ጉዳዩ የለየለት ቀውስና ችግር ከመፍጠሩ በፊት ዕቅዱ መከለስ አለበት ነው የምለው፡፡ በመርህ ደረጃ ኢትዮጵያ አንድ ዓይነት መከላከያና ፖሊስ ቢኖራት የሚጠላ የለም፡፡ ችግሩ አለመተማመን በመፈጠሩ የመጣ ነው፡፡                      

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...