Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉሰው በተፈጥሮው አቃፊ እንጂ አግላይ አይደለም

ሰው በተፈጥሮው አቃፊ እንጂ አግላይ አይደለም

ቀን:

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ

የሰው ልጅ ወሰን አልባ ነው፣ ክልል አልባ ነው፣ ድንበር አልባ ነው። ራሱን ወስኖ ከአምሳያው ተገልሎ ብቻውን ሊኖር አይችልም። ሰው ቢመነኩስ እንኳን ብቸኛ መሆን አይችልም። ለመኖር የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገርች መሸመት ወደ ከተማ መምጣቱ ወይም አምሳያውን መላኩ አይቀርም። ደግሞም አብረው ሲኖሩ መናኩስታትም ይደጋገፋሉ። እናም ሰው በማኅበራዊ ኑሮ ላይ በተመሠረተና በተሳሰረ ሕይወት ነው መኖር የሚችለው። ተነጣጥሎ እንደ እንስሳት በዘር ተከፋፍሎ መኖር ከቶም አይችልም።

እንስሳት የተነጣጠለ በዘር ላይ የተመሠረተ ኑሮ ዕጣ ፈንታቸው ነው። አንዳንድ የዱርና የቤት እንስሳትም ክልላቸውን በሽንታቸው ምልክት በማድረግ ይታወቃሉ። የአንበሳ የኑሮ ዘይቤ ከተኩላ ጋር አይመሳሰልም። ነብር ከቀበሮ ጋር ተቀላቅሎና ኅብረት ፈጥሮ መኖር አይችልም። ወደ ቤት እንስሳም ስትመጡ የአኗኗር ዘይቤያቸው የተለያየ ነው።

በእርግጥ ገዣቸው ሰው ነው። ሰው በመሆኑም ልዩነታቸውን አውቆ  ፈረስን በበሬዎች በረት አያስረውም። የከብት ማደሪያ በረት ነው። የፈረስ፣ የበቅሎና የአህያ ማደሪያ ጋጣ ነው። የበግና የፍየል ማደሪያ ደግሞ ጉሮኖ ነው። በዚህ መልክ ነው ለይቶ የሚያኖራቸው። እነዚህ እንስሳት ተፈጥሮአቸው የተለያየ በመሆኑ በአንድነት ልታኖራቸው ከሞከርክ ውጤቱ አስከፊ ይሆናል። ይህንን አስቀድመህ በመገንዘብ እንስሳትህን በራሳቸው ክልል እንዲኖሩ ማድረግ ግዴታህ ነው።

አራዊትን ግን አንተ አታስተዳድራቸውም። እያንዳንዱ የዱር እንስሳ የራሱ አስተዳዳሪ ነው። በበይና በተበይ መደብም ተከፋፍሎ የሚኖር ነው። በሥጋ በልና በዕፅዋት በልነቱም በዓለም ላይ ለመኖ ፍለጋ ሲሰማራ ተቧድኖ ነው። በዘሩ ተሰባስቦ ማለት ነው። ሥጋም ሆነ ዕፅዋት በሌ የዱር እንስሳት ተደበላልቀውና ተሰበጣጥረው ለመኖር ከቶም አይችሉም። ሁሉም በየፊናቸውና በየመደባቸው ነው የሚኖሩት።

የሰው ልጅ ግን ከሚኖርበት ሥፍራ ውጪ ኑሮውን ለማሸነፍ ከሌሎች ሰዎች ጋር ትብብሩን እያሰፋ፣ እስከ ሕልፈቱ ድረስ ለኑሮው አስፈላጊ የሆኑ ድርጊቶችን እያከናወነ የሚኖር ፍጥረት ነው። የሰው ኑሮው በድርጊት የተሞላ ነው። በድርጊት ያልተሞላ ሕይወት ታሪክ እንደሌለው ያለንበት የዘመነ ዓለም ይነግረናል። እንዲሁም ሰው በተፈጥሮው አካታች ነው፣ አግላይ አይደለም።

የሰው ተፈጥሮ  አካታች  ወይም አቃፊ ነው። የእንስሳት (የዱርም ሆነ የቤት እንስሳት) ተፈጥሯዊ ባህሪ አግላይ ነው። ሌላውን የማያስጠጋ ነው። የሥጋ በሌዎቹ እንስሳት ባህሪም ዕፅዋት በሌዎቹን ብቻ ሳይሆን ሥጋና ዕፅዋት በሌዎችንም ጭምር ሰልቃጭ ነው። ጅብ አንበሳን ለመብላት ቢያደባ አይግረምህ። አንበሳም የራበው ቀን   ከነብር ጋር ቢተናነቅ አያስገርምም።

የሰው ልጅ ግን እንደ ዱር እንስሳ አይደለም። አንዱ ሌላውን ለመሰልቀጥ አልተፈጠረም። ሆኖም ሰልቃጭና አውዳሚ ይሆን ዘንድ የሚገኝበት ንቃተ ህሊና፣ እንዲሁም የሥጋ ፍላጎቱ ያስገድደዋል።

የታዳጊ አገር ልሂቃንና የመንግሥት ሥልጣንን የተቆጣጠሩ ግለሰቦች ብዙኃኑ ዜጋ በሚገኝበት ንቃት ላይ ተመሥርተው ዛሬን ኖሮ ሕይወቱን በዕውቀት ድጋፍ እንዲለውጥ ከማድረግ ይልቅ፣ የትናንት ቂሙን እንዲያስታውስ በማድረግና ከሰው ይልቅ የእንስሳን ባህሪ እንዲያጎለብት ሌት ተቀን ቀምቶ በመብላት ፍላጎት እንዲጦዝ በማድረግ፣ ለኃላፊ የሥጋ ጥቅም ሲል በፖለቲካና በዕምነት ሰበብ አግላይና ሰው አዳኝና ገዳይ ያደርጉታል።

በዓለም ላይ የምናየው እውነት ይህ ነው። ለምሳሌ ዩክሬንን መጥቀስ ይቻላል። የዩክሬንን ወጣትና ስሜታዊ መሪ ተመልከቱ። ሁሉም ነገር እንደ ፊልም ስክሪፕት ጽሑፍ በቀላል ፍሰት የሚንሸራሸር መስሏቸው የዩክሬንን ሕዝብና ሀብት በሩሲያ ሠራዊት እንዲወድም የበኩላቸውን የጥፋት ድርሻ ተወጥተዋል።

በእሳቸው ግትርነትና የዩክሬን ጦርነትን ማትረፊያ ባደረጉ ከዓለም ሕዝብ 0.001 በመቶ በማይሆኑ ቱጃሮች ሴራ ሕዝቡ ተሰደደ። ዜጋው ከሀብታምነት በአንድ ጀንበር ሞላጫ ደሃ ሆነ። ስንዴ እንደ ጉድ የሚመረትባት አገር፣ የሱፍ ዘይትን ለዓለም በከፍተኛ መጠን አቅራቢ የሆነች የታታሪ ዜጎች አገር የጦር አውድማ እንድትሆን ቱጃሮቹ ወሰኑባት። ልብ በሉ ከሚበቃቸው በላይ ሀብት ያላቸው፣ ሰማይን በእርግጫ እየደበደቡ ያሉ ቱጃሮች ናቸው ይህንን ታታሪ ሕዝብ ስደተኛና ተመፅዋች ያደረጉት።

የጦርነቱ ዋና ሰበብም ከጎረቤቱና ወንድም ከሆነው ከሩሲያ ሕዝብ ይልቅ አውሮፓውያኑ ቱጃሮች ዩክሬን የኔቶ አባል እንድትሆን በመወሰናቸው ነው (የዩክሬን መንግሥት የኔቶ ቃል ኪዳን ጦር አባል የመሆን መብት ቢኖረውም፣ ለሩሲያ ሕዝብ ግን የኔቶ ወደ ዩክሬን መምጣት ትልቅ ሥጋት መሆኑ እየታወቀ፣ በኃያላኑ ተማምኖ ከኑክሌር ኧረር ጋር ለመፋለም እንደ አበደ ሰው ዘሎ ፀብ አጫራ መሆን አልነበረበትም። ዞሮ ዞሮ የጦርነቱ ፍፃሜ አንድም ድል ማድረግ፣ አንድምም ድርድር መሆኑ ላይቀር…)፡፡

የዓለም ትንንሽ አገሮች ብዙ ጊዜ የሚዘነጉት የአውሮፓም ሆነ የአሜሪካ መንግሥታት በውጭ ፖሊሲያቸው የሚያራምዱት የቱጃሮቻቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሆኑን ነው። ኃያላኑ የፖለቲካ ፖሊሲያቸው ከቱጃሮቻቸው ጥቅም አንፃር የተቃኘ ነው። ይህንን ዓይነት መንገድ በመከተልም አፍሪካን ከማበልፀግ ይልቅ እያደኸዩ የማኖር ዕቅዳቸውን ዛሬም አልከለሱም።

ዛሬም ኃያላኑ ሕዝባቸውን አቃፊ በሆነ ሰውኛ መንገድ እያስተዳደሩ፣ በኢኮኖሚም ሆነ በቴክኖሎጂ ኋላቀር የሆነችውን አፍሪካን በእንስሳዊ መንገድ አግላይ ሥርዓት እንድትመራ በማድረግ ላይ ተጠምደው እናስተውላለን።

በዚህ ዓይነት የረቀቀ ሴራ የአፍሪካ ሕዝብ ሠርቶ የሚለወጥበትን መንገድ አጥረውበታል፡፡ ለሕይወት ያለው ግንዛቤ ፈጽሞ እንዳይታደስ፣ ጠያቂ የሆነ አዕምሮ እንዳይኖረውና ከማይምነት እንዳይወጣ አድርገውታል። የተለያየ ነፃ አውጪ ነኝ ባይ አቋቁመው ሁሌም በሥጋት ኗሪ እንዲሆን፣ ልክ እንደሚታደን እንስሳ በርጋጊ ፍጡር ሆኖ ከንቱ ሕይወት እንዲኖር ፈርደውበታል። ወደ ሰማይ ብቻ አንጋጦ እንዲኖርም በየመንደሩ ውስጥ በቀቢፀ ተስፋ የሚጮኸ ትውልድ እንዲበራከት አድርገዋል።

 “ባህልህ ይኼ ነው፣ ጠብቀው…” እያሉትም ራቁትነቱን ያወድሳሉ። ማነው በዚህ በ21ኛው በቴክኖሎጂ በረቀቀ ክፍለ ዘመን ዛሬም በጦርና በጋሻ፣ እንዲሁም በ18ኛው ክፍለ ዘመን ዓይነት ሥርዓት መመራት የሚፈቅደው? የአፍሪካ ሰው አሁን ዓለም በደረሰችበት የሥልጣኔ ደረጃ ልክ እንዳያስብ ዕውቀትን ያሳጣው ማነው? ትናንትም በቅኝ ገዥነት ዛሬም እርስ በርስ በማጋጨት በእንስሳዊ ባህሪ ውስጥ ሰምጦ እንዲዳክር የሚያደርጉት፣ በዕውቀት የመጠቁት የምዕራብ መንግሥታት ቱጃሮች በታላላቅ የፖለቲካ ሊቃውንቶቻቸው ታግዘው አይደለምን?

ይህንን ሀቅ ኢትዮጵያዊያን በቅጡ ልንገነዘብ ይገባናል። በዚህች ምድር የዛሬ አሥር ሺሕ ዓመት ድንበር አልነበረም። ሕዝቡም በጣም ትንሽ ነበር። ድንበርም፣ ፓስፖርትና ቪዛም አልነበረም። ለምሳሌ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአሥር ሺሕ ዓመተ ዓለም አጠቃላይ የዓለም ሕዝብ ቁጥር ሁለት ሚሊዮን ነበር ተብሎ ይገመታል። በዚህ ሁኔታ እንዴት ድንበርና የድንበር ጠባቂ ሊኖር ይችላል? የዚያን ዘመን ሰው ዓለም አገሩ ነበረች። እግሩ ወደ አደረሰው እየተጓዘ ልቡ የፈቀደው አገር ይኖር ነበር።

ሰው ሰው ሆኖ ከሚሊዮን ዓመታት በፊት በአፍሪካ ተፈጥሮ ዓለምን ዘሬ እንደሞላትም አትዘንጉ። ታሪክን ማወቅ ይጠቅመናል። ዕውቀት ከጥፋትና ከመጠፋፋት ያድነናል። የመጀመርያው ሰው ዓባይ ይኑር አፋር ታሪክ እቅጩን ባይነግረንም፣ የሰው ዘር መገኛ ኢትዮጵያ እንደሆነች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዕድሜ ያላት አፋሪቱ ድንቅነሽ (ሉሲ) አረጋግጣለች።

ጽሑፌን የምደመድመው ኢትዮጵያውያን ሰው መሆናቸውን እንዲያስቡና ቋንቋ ከመግባቢያነት ውጪ ሌላ ፋይዳ እንደሌለው በማስገንዘብ ነው። ዜጎች ሰው በመሆናቸው የሚተቃቀፉ እንጂ በጠላትነት የሚተያዩ፣ እርስ በርሳቸው የማይቀራረቡ፣ እንደ አውሬ ተሳዳጅና አሳዳጅ ፍጡራን ከቶም አይደሉም። ትናንትናም ሆነ ዛሬ ዜጎችን ተሳዳጅና አሳዳጅ ያደረጋቸው የጥቅም ሴራ ነው።

ሰው ቢገባው ዓለም ሁሉ የእሱ ናት። መሥራት፣ መፍጠር፣ ለዓለም ታላቅ አበርክቶ ለማድረግ የሚችል ጭንቅላት ያለው ሰው ሁሉ በየትኛውም የዓለም ክፍል  ተዘዋውሮ መሥራት ይችላል፣ እየሠራም ነው።

ዓለም የበለጠ የሚያዘምናትን፣ ተፈጥሮን በወጉ የሚጠብቅላትን፣ በፍቅር የሚያስተሳስራትን እንጂ እርስ በርስ የሚያጫርሳትን አትፈልግም። ለመጨራረስና ዓለምን ለማውደም ከተፈለገ ከበቂ በላይ ኑክሌር የታጠቁ ኃያላን አገሮች አሏት።

የኑክሌር ጥፋት ከንቱና አላስፈላጊ የሞኝ ድርጊት ነው የሚሆነው። ከዚህ ይልቅ ዓለምን የተሻለች ለማድረግ የነገ አፈሩ የዛሬው የዓለም ትውልድ በቅንነትና በትብብር በጋራ ቢሠራ ይበጀዋል። ሰው በተፈጥሮው ሰውን አቃፊ እንጂ አግላይ አይደለምና፡፡

ጽሑፌን የምደመድመው ዛሬ ሰው በምድር ላይ እንደ አሸዋ ሳይበዛ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ከ123 ሚሊዮን በላይ ሳይሆን የዓለም ሕዝብ ከሁለት ሚሊዮን ተነስቶ በአሥር ሺሕ ዓመታት ውስጥ ስምንት ቢሊዮን እንዴት እንደ ደረሰ የሚከተለውን ጠቋሚ እንድትመለከቱ በመጋበዝ ነው።   

ክርስቶስ በአንደኛው ዓ.ም. እንደተወለደ … 188 ሚሊዮን ሕዝብ በዓለም ላይ ነበር፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአንድ ሺሕ ዓመተ ዓለም … 115 ሚሊዮን ሕዝብ ነበር፡፡

በ2‚000 ዓመተ ዓለም … 72 ሚሊዮን

በ3‚000 ዓመተ ዓለም … 45 ሚሊዮን                 

በ4‚000 ዓመተ ዓለም … 28 ሚሊዮን                  

በ5‚000 ዓመተ ዓለም … 18 ሚሊዮን                   

በ6‚000 ዓመተ ዓለም … 5 ሚሊዮን                      

በ9‚000 ዓመተ ዓለም … 4 ሚሊዮን                         

በ10‚000 ዓመተ ዓለም … 2 ሚሊዮን

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው godmyc1955godmyc@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡                     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...