Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ባለፈው ሰሞን ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ ባልደራስ ኮንዶሚኒየም አቅጣጫ የሚወስደውን መንገድ ይዤ ቁልቁል ስወርድ፣ ከሾላ አቅጣጫ ወደ ግራ ታጥፈው ከፊቴ የተደረደሩ መኪኖች ብዛት ስለነበራቸው ጉዞአችን ለደቂቃዎች ተገታ፡፡ ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አንገቴን አውጥቼ ሳይ፣ ወረድ ብሎ አንድ ቶዮታ ኮሮላና ሃንዳይ ታሱን መኪኖች ተጋጭተው የትራፊክ ፖሊስ ደርሶ ምልክት እያደረገ ነበር፡፡ በዚህ መሀል አንገቴን ወደ ግራ ሳዞር አንድ ትምህርት ቤት ግንብ ላይ፣ ‹‹የምናደንቀው ጨረቃ ላይ ያረፈውን ሰው ሳይሆን ጨረቃ ላይ እንዲያርፍ ያደረገውን መምህር ነው›› የሚል ጽሑፍ በጉልህ ተጽፎ አነበብኩ፡፡ እኔ ደግሞ እንዲህ ለየት ያሉ አባባሎችን ወይም ጥቅሶችን ሳይ በአዕምሮዬ ማሰላሰል ደስ ይለኛል፡፡

የትምህርት ቤቱን ዋና በራፍ በሆነ ዓመት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች እንዳሠሩት ተጽፏል፡፡ ይህንን አስገራሚ አባባል እነሱ ወይም ሌሎች እንደጻፉት ባላውቅም፣ ለአባባሉ አመንጪ ግን ባርኔጣዬን አውልቄ አድናቆቴን ገልጫለሁ፡፡ እኔም ከተማሪና ከመምህር ግንኙነት ጋር በተገናኘ በርካታ ገጠመኞች ስላሉኝ ነው አባባሉ ቀልቤን የገዛው፡፡ ጨረቃ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳረፈ የሚነገርለት ኒል አርምስትሮንግ የተባለ አሜሪካዊ የጠፈር ሰው እንደሆነ ከድሮ ጀምሮ ስሰማ ነው ያደግኩት፡፡ ከእሱ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በመንኮራኩር ወደ ህዋ መምጠቁ የተነገረለት ደግሞ ሩሲያዊው ዩሪ ጋጋሪን እንደነበርም አውቃለሁ፡፡

ከእነዚህ ሰዎች በተጨማሪ ዓለማችን በርካታ የፈጠራ ሐሳብ አመንጪ ሰዎችን አፍርታለች፡፡ እነ ኮፐር ኒከስ፣ ቶማስ ኤልቫ ኤዲሰን፣ ጀምስ ዋት፣ አልበርት አንስታይን፣ ጋሊሊዮ ጋሊሌ፣ ሉዊ ፓስተር፣ አይዛክ ኒውተን፣ አሌክሳንደር ግርሃም ቤልና የመሳሰሉ ታሪክ የሚዘክራቸው ብዙዎች አሉ፡፡ በዚህ ዘመንም ዕፁብ ድንቅ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለዓለም እያዳረሱ ያሉ ሳይንቲስቶችና ቴክኖሎጂስቶችም ብዙ ናቸው፡፡ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ መስክም በዓለማችን በቻት ጂፒቲና በጂፒቲ ፎር እየታዩ ያሉ አስደናቂ ጅምሮችም ይታወቃሉ፡፡ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሕክምና፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በፋይናንስ፣ ወዘተ በርካታ የቴክኖሎጂ ግስጋሴዎች እየታዩ ነው፡፡

- Advertisement -

ከእነዚህ ሁሉ ግኝቶች በስተጀርባ ያለው ግን ዕውቀት የሚቀሰምበት መምህር ነው፡፡ መምህር በሁሉም መስኮች ብቁና ንቁ ባለሙያዎችን የሚያፈራ ሆኖ ሳለ፣ በማኅበረሰባችን ውስጥ የተሰጠው ቦታ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ድሮ መምህርነት በጣም የሚያስከብር ሥራ እንደነበረ እኔ ጭምር አውቃለሁ፡፡ ‹‹የእኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ ወሰደሽ አስተማሪ›› ተብሎ ከመዘፈኑም በላይ፣ በአዲስ አበባም ሆነ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከበረ ነበር፡፡ በቀደም ዕለት ጨረቃ ላይ ካረፈው ይልቅ እንዲያርፍ ያደረገው መምህር፣ ለጊዜው ስሙን ያላወቅኩት ትምህርት ቤት ግንብ ላይ በዚህ መጠን ሲወደስ ማየቴ ለእኔ ከፍተኛ ሐሴት ነው የፈጠረልኝ፡፡

በኢትዮጵያ በፊትም ሆነ አሁን ብዙዎቹ የአገሪቱ ልሂቃን ያለፉት በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደሆነ አሌ አይባልም፡፡ እነሱም ከመምህራኖቻቸው ጋር ልዩ የሆነ ትዝታ እንዳላቸው ይገባኛል፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥ ያለፈ ማንኛውም ሰው በትምህርት ከሚያገኘው ዕውቀት በተጨማሪ፣ በሚወዱዋቸው መምህራን በመመሰጥ ወይም በማስተማር ዘዴያቸው በመማረክ የወደፊት ሕይወታቸውን የመረጡ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ሒሳብ፣ ባዮሎጂ፣ ቋንቋ፣ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪና ሌሎች ትምህርቶችን ከመምህራን የትምህርት አሰጣጥ አኳያ በመውደድ እስከ ትልቅ ደረጃ የደረሱ ብዙ ናቸው፡፡

እስካሁን የማይገባኝ ግን አብዛኞቹ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ልሂቃንና አጋፋሪዎቻቸው ጉዳይ ነው፡፡ በጣም ጥቂት ከሚባሉት ይልቅ የእነዚያን ትጉህና ታታሪ መምህራን ባህሪም ሆነ የአገር ፍቅር ስሜት ያልወረሱ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች፣ ከራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት በላይ አገር የምትባል የጋራ መኖሪያ እንዳለች የረሱ ይመስለኛል፡፡ በተለይ በዚህ ጊዜ ደግሞ ሰብዓዊ ፍጡር መሆናቸውን ዘንግተው፣ ከብሔራቸው ውጪ ምንም ዓይነት ነገር አልታይ ያላቸው መብዛታቸውን ሳስተውል አዝናለሁ፡፡ በጋማ ከብት እየተጓዙ፣ ከደራሽ ውኃ ጋር እየታገሉና ሕይወታቸውን ለዱር አውሬ ጭምር አጋልጠው በገጠር አካባቢዎች ሳይቀር የዕውቀት ጮራ የፈነጠቁ መምህራንን ውለታ ሳስብ የዘመናችን ነገር ያሳስበኛል፡፡

ለረጅም ዓመታት በትግራይ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በምዕራብና በአዲስ አበባ ያስተማሩ አንድ ጡረተኛ መምህር ጎረቤት አሉኝ፡፡ ከአርባ ዓመታት በላይ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ መምህርነት ድረስ አገልግለው በጡረታ ሲሸኙ፣ የራሳቸው መኖሪያ ቤት ወይም መኪና ኖሮአቸው አያውቁም፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ እየተጠባበቁ የሚኖሩት ከ60 ዓመት በላይ የሆነው አሮጌ የቀበሌ ቤት ውስጥ ነው፡፡ አንድም ቀን ለአገልግሎታቸው ዕውቅና የሰጣቸው መንግሥታዊ አካል የለም፡፡ ልብ በሉ ከአርባ ዓመታት በላይ አገልግለው የደረት ምልክት (ፒን) እንኳን የላቸውም፡፡ ሲታመሙ በቀበሌ አማካይነት በገቡት የጤና መድን ነው የሚታከሙት፡፡ የተሻለ ክሊኒክ ወይም ሆስፒታል ለመሄድ አቅማቸው አይፈቅድም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ መሰሉ ታሪክ የብዙዎች ነው፡፡ አገሩን ደሙን አፍስሶና አጥንቱን ከስክሶ የጠበቀ ጀግና ወታደር ዕጣ ፈንታው፣ በአነስተኛ ክፍያ የግለሰብ ወይም የድርጅት ጥበቃ መሆን ነው፡፡ መምህራንም ቢሆኑ ዕጣቸው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ብዙዎቹ በአነስተኛ ደመወዝ የእርጅና ጉልበታቸውን ይበዘበዛሉ፣ ወይም ከእነ ጭራሹ ቀጣሪ አያገኙም፡፡ እነሱ አስተምረው ለወግ ለማዕረግ ያበቋቸው ፖለቲከኞች የጡረታ አበል ለመጨመር ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ጭራሽ ይባስ ብለው አገር በብሔር እየከፋፈሉ የከፋ በደል እየፈጸሙ መሆናቸው ያሳዝናል፡፡ ለወግ ለማዕረግ የበቁት ጨረቃ ላይ ወጥተው ወይም ጠፈር እያሰሱ መምህራኖቻቸውን ሲያስመሠግኑ፣ የእኛዎቹ ደግሞ በክፋት ሥራቸው መምህራኖቻቸውን አንገት ማስደፋታቸው ከፍተኛ በደል ነው እላለሁ፡፡

(ሳሙኤል በዕወቀቱ፣ ከለቡ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...