ከፍተኛ ደረጃ የከበረ ማዕድን አምራቾች ይከፍሉ የነበረውን የሮያልቲ ክፍያ መጠን፣ ከሰባት ወደ አምስት በመቶ ዝቅ እንዲል የሚያደርገውን የማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አፀደቀ፡፡
የማዕድን ማምረት ሥራ ባለፈቃዶች ከማዕድን ማምረቻ ሥፍራ ከሚያወጡት የማዕድናት ምርት በየጊዜው በመቶኛ እየተሰላ የማምረቻና የሥጋት ወጪን ሳይጨምር፣ ለመንግሥት የሚፈጽሙት ክፍያ ‹‹ሮያልቲ›› የሚል ትርጓሜ አለው፡፡
የከፍተኛ ደረጃ የከበረ ማዕድን አምራቾች አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ መሠረት ይከፍሉት የነበረው የሮያልቲ መጠን ከሰባት ወደ አምስት በመቶ ዝቅ እንዲል ያስፈለገው፣ በዘርፉ መዋዕለ ንዋይ የሚያፈሱ ኢንቨስተሮችን እንዲስብ ተደርጎ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የማዕድን ማምረት ሥራ ባለፈቃዶች የተመረተውን ማዕድን ከሸጡበት የወቅቱ የገበያ ዋጋ ላይ ሮያልቲ የሚከፍሉ ሲሆን፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀው ረቂቅ አዋጅ በከፍተኛ ደረጃ የማዕድን ማምረት ሥራ ባለፈቃዶች የሚከፍሉት ሮያልቲ መጠን ለከበሩ ማዕድናት አምስት በመቶ ሆኗል፡፡
በከፊል የከበሩ ማዕድናት፣ የብረት ነክ ማዕድናት፣ የኬሚካል ማዕድናት፣ የኢንዱስትሪ ማዕድናት፣ የኮንስትራሽን ማዕድናት፣ እንዲሁም ጨው አምራቾች የሚከፈሉት ሮያልቲ መጠን አራት በመቶ ሆኗል፡፡ በአንፃሩ በባህላዊና በአነስተኛ ደረጃ የማዕድን ማምረት ባለፈቃድ የሚከፈለው የሮያልቲ መጠን በክልል ሕጎች እንደሚወሰን አዋጁ ያስረዳል፡፡
የኬሚካል ማዕድናት እንደ አዲስ በአዋጁ የተካተቱ ሲሆን፣ እነዚህ ማዕድናትን የሚያመርት ባለፈቃድ አራት በመቶ ሮያልቲ እንዲከፍል ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል የኮንስትራክሽን ማዕድን ማምረት ሥራ ባለፈቃድ ደግሞ በቀድሞው አዋጅ ሦስት በመቶ ሮያልቲ ይከፍል የነበረ ሲሆን፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀው ረቂቅ ወደ አራት በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጎ ተካቷል፡፡
የማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ እንደሚያስረዳው በአዋጁ አንቀጽ 60 የማዕድን ማምረት ሥራ ባለፈቃዶች የሚከፍሉት የሮያልቲ መጠን ሲወሰንና ረቂቁ ሲዘጋጅ፣ በተለያዩ አገሮች የማዕድን ማምረት ሥራ ባለፈቃዶች የሚከፍሉት የሮያልቲ መጠንን ከግምት ውስጥ አስገብቷል ተብሏል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የከፍተኛ ደረጃ ማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድ ለባለፈቃድ ሲሰጥ ማዕድን የሚመረትበት ክልል ከሚመረተው ማዕድን ‹‹ሕዝባችን ተጠቃሚ አይደለም›› የሚል ቅሬታ ያነሳ ስለነበረ፣ ክልሎች ሁለት በመቶ የተሳትፎ ድርሻ ያለ ምንም ክፍያ እንዲያገኙ ይደነግጋል፡፡
ቀደም ሲል ከአነስተኛ ማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድ ማዕድኑ የሚመረትበት ክልል ያለ ምንም ክፍያ ሊይዝ የሚችለው የተሳትፎ ድርሻ መጠን ያልተወሰነ በመሆኑ፣ ፈቃዱን የሰጠው ክልል ሰባት በመቶ ነፃ ድርሻ እንዲይዝ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡
በሥራ ላይ ባለው አዋጅ፣ አንድ የማዕድን ምርመራ ሥራ ፈቃድ እየታደሰ ለአሥር ዓመት የሚቆይ ሲሆን፣ ባለፈቃዶች የወሰዱትን የፈቃድ ቦታ ለረዥም ጊዜ ይዘውት እንዲቆዩ የሚያደርግ የነበረ በመሆኑ፣ የቀደመው ባለፈቃድ በአግባቡ ባይሠራና የፈቃድ ክልሉን ለሌላ ባለሀብት ማስተላለፍ ቢያስፈልግ፣ ለቦታው ፈቃድ እንዳይሰጥ የሚያደርግ በመሆኑ፣ ከበፊቱ የፈቃድ ቆይታው ላይ ሦስት ዓመት ተቀንሶ ጣሪያው ሰባት ዓመታት ብቻ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
የአነስተኛ ደረጃ ማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድ ለአምስት ዓመት እንዲሰጥ የከፍተኛ ደረጃ የማዕድን ማምረት ፈቃድ ደግሞ ለአሥር ዓመት እንዲሆንና ሥራው እየታየ ግን ይታደሳል ተብሏል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ አንድ የአነስተኛ ደረጃ ማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድ ለአሥር ዓመታት ያህል፣ እንዲሁም የከፍተኛ ደረጃ ማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድ ደግሞ ለ20 ዓመት ያህል እንዲሰጥ የሚፈቅድ ሲሆን፣ ነገር ግን ይህ መሆኑ ባለፈቃዶች አንድ ጊዜ ፈቃድ ከተሰጣቸው የተወሰነ ሥራ ብቻ በመሥራት ፈቃዱን ያላግባብ ይዘው እንዲቆዩ የሚያደርግ መሆኑ ተብራርቷል፡፡
በአዋጁ ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሚመለከተው የመንግሥት አካል በማናቸውም የፈቃድ ክልል ውስጥ ለሚገኝ ማንኛውም የማይንቀሳቀስ ንብረት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት፣ ለሕጋዊ ባለፈቃዱ ተገቢውን ካሳ በመክፈልና ባለፈቃዱ ለሥራው ያወጣውን ወጪ በመተካት የፈቃድ ክልሉን ሊያስለቅቀው ይችላል የሚለው ተደንግጓል።
ከላይ የተገለጸው አንቀጽ ከዚህ ቀደም ለማዕድን ሥራ የተሰጠን የፈቃድ ቦታ መንግሥት ለሌላ ሕዝባዊ አገልግሎት ቢፈልገው፣ መሬቱን በፈለገበት ጊዜ ሊያስለቅቅ የሚችልበት አግባብ በቀድሞው አዋጅም ሆነ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር1161/2011 ያልተካተተ ነበር፡፡
ሚያዚያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 19ኛ መደበኛ ጉባዔ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች ውስጥ፣ የማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅ አንዱ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ እንደሚያሳየው፣ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ከመስጠቱም ባሻገር በሚያካሄዳቸው የለውጥ ሥራዎች ውስጥ ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ለማድረግ፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉ የማዕድን ሥራ ሕጎች ላይ ጥናት በማከናወን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡