Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚያቋቁመው ረቂቅ አዋጅ በርካታ አደረጃጀቶችን ይዞ መምጣቱ ጥያቄ አስነሳ

ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚያቋቁመው ረቂቅ አዋጅ በርካታ አደረጃጀቶችን ይዞ መምጣቱ ጥያቄ አስነሳ

ቀን:

  • የቦርድ አባላት ስብጥር ከመንግሥት አካላት የፀዳ እንዲሆን ተጠይቋል

የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን ለማደራጀት በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ፣ በትምህርት ተቋማቱ ይዋቀራሉ ተብለው የታሰቡት አደረጃጀቶች መብዛት፣ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሥራ መጠላለፍና መደራረብ ይፈጥራል የሚል ሥጋት እንዳለባቸው ምሁራን ገለጹ፡፡

በቅርቡ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ሥራ ለማስገባት ታሰቦ በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጂ በርካታ አደረጃጀቶች እንደሚኖሩት ተደንግጓል፡፡ በዚህም መሠረት ቻንስለር፣ የሥራ አመራር ቦርድ፣ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ሴኔት፣ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል፣ ማኔጂንግ ካውንስልና ሌሎችም በራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚደራጁ የተለያዩ መዋቅሮች እንደሚኖሩ ተብራርቷል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ሰፋ ያለ መዋቅራዊ አደረጃጀት በተቋማቱ ውስጥ የአሠራር ክፍተትና በሥራ ላይ መሰናክል እንዳይፈጥር፣ የቀረቡት አደረጃጀቶች ከወዲሁ እንዲታዩ ተጠይቋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ረቂቅ አዋጅ ላይ ግብዓት ለመሰብሰብ ከዩኒቨርሲቲ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከትምህርት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሚያዝያ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት አድርጓል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተወከሉት መምህር ዘገየ ሙሉዬ (ዶ/ር)፣ ከአደረጃጀቶቹ መካከል የዩኒቨርሲቲ ካውንስል ምንም ዓይነት ሚና የሌለው መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ምንድነው ተግባሩ ቢባል ይኼ ነው የሚባል ሚና የለውም፤›› ብለዋል፡፡    

በመሆኑም የዩኒቨርሲቲ ካውንስል ሪፖርት የማዳመጥና ዕቅድ የማፅደቅ ሚና ብቻ ያለው በመሆኑ፣ ምንም የማይሠራ መዋቅር ከመፍጠር ዘርዘር ያሉ ተግባራት ቢቀመጡለት የተሻለ ነው ብለዋል፡፡

የሰው ሀብት ልማት ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ከዚያም በተጨማሪ ሴኔት፣ የኤግዘክዩቲቭና የማኔጂንግ ካውንስልና ሌሎች አደረጃጀቶች መብዛት የኃላፊነት መጣረስ እንዳያመጣና ለውሳኔ አሰጣጥ ክፍተት እንዳይፈጥር ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም እንዲህ ዓይነት የአደረጃጀት መስፋት አስቸኳይ የሆኑ ጉዳዮች ሲኖሩ ለውሳኔ አመች ላይሆን ይችላል ብለዋል፡፡

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ አገልገሎት ኃላፊ አቶ ምሕረት ዓለማየሁ፣ በአስተዳደር መዋቅር የዩኒቨርሲቲና ማኔጂንግ ካውንስሊንግ በሥራ ላይ ባለው 1152/2011 አዋጅ ላይ የሠፈሩ ቢሆንም፣ አሁን የተጨመረው ኤግዘክዩቲቭ ካውንስል ከእነዚህ በሥራ ላይ ካሉት ካውንስሎች በተለየ ሊሠራው የሚችለው ጉዳይ እንደማይኖር፣ የሥራ ኃላፊነቶች የበለጠ የማኔጂንግ ካውንስሉ የሚያከናውናቸው ስለሆኑ፣ የዚህ አደረጃጀት አስፈላጊነት እንደገና እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ የዩኒቨርሲቲ ካውንስል አስፈላጊነት ላይ ሰፋ ያለ ውይይት እንደተደረገበት፣ ነገር ግን ለእነዚህ አደረጃጀቶች የተለያየ ኃላፊነት እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህ ካውንስሎች ዝም ብሎ መዋቅር መፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ ትልልቅ የትምህርት ተቋማትን የሚያማክሩና በተወሰነ ደረጃ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰቡ በውሳኔ አሰጣጥ ሒደቱ እንዲሳተፍ ለማድረግ አደረጃጀቱን እያሰፋ መሄድ ጠቃሚ ነው በሚል መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይ ተጨማሪ የሥራ መደላድሎችና ኃላፊነቶች ሲመጡም ለእነዚህ ካውንስሎች ዕድል ለመስጠት ታሳቢ ተደርጎ ነው ብለዋል፡፡

ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ አካላት በተሳተፉበት በዚህ የውይይት መድረክ፣ በረቂቅ አዋጁ እንደ አዲስ እንደሚቋቋም በተገለጸው የሥራ አመራር ቦርድ ውስጥ፣ የቦርድ ስብጥር አሁን በሥራ ላይ ካለው አሠራር በተለየ አለመምጣቱን፣ አዲሱ አሠራር በሥራ ላይ ካለው በተለየ ሁኔታ ለዩኒቨርሲቲዎች ሰፋ ያለ ኮታ የማይሰጥ ነው ተብሏል፡፡

በሥራ ላይ ባለው የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ 1152/2011 መሠረት ቦርድ እየተዋቀረ ያለው በአመዛኙ በትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት ከተቋማቱ ውጪ በመሆኑ፣ በዚህኛው አደረጃጀት ለዩኒቨርሲቲዎች ሰፋ ያለ ዕድል እንዲሰጥ የጠየቁት ከሲቪል ሰርቪሰ ዩኒቨርሲቲ የተወከሉት ዮሐንስ ተስፋዬ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ተሳታፊ ዘገየ (ዶ/ር) እንዳሉት ደግሞ፣ አንድ ራሱን የቻለ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋም አስፈላጊ ነው ከተባለ ጠንካራ የሆነ የሥራ አመራር ቦርድ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ነው በሚል ከዚህ በፊት በነበረው ዓይነት የመንግሥት አካላት የሚመደቡበት ከሆነ፣ ጉዳዩ በአጭሩ ሳይሳካ ይቀራል ብለዋል፡፡ በመሆኑም የቦርድ አመራረጥና ስብጥር ጥንቃቄ እንደሚያሻው ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲዎች በሒደት ራሳቸውን ችለው መቆም ካለባቸው ገለልተኛ የሆነ የሥራ አመራር ቦርድ እንዲኖረው ማሰብ ይጠይቃል ሲሉ አክለዋል፡፡

 በዘርፉ ልምድ ያላቸው ሰነድ አንብበው መጥተው ያንን ዩኒቨርሲቲ ሊያሳድጉ የሚችሉና ብዙ ነገር አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የቦርድ አባላት መሆን እንዳለባቸው ጠይቀዋል፡፡ አሁን እንደሚታየው የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ጊዜ የሌላቸውና የሚላክላቸውን ሰነድ እንኳ በሙሉ አንብበው አይመጡም ብለዋል፡፡

‹‹እንዲህ ዓይነት ሰዎችን አሁንም የምናስቀምጥ ከሆነ ዩኒቨርሲቲዎች ሥራውን ሳይጀምሩት፣ ለበጎ ብለን ያሰብነው ነገር ወደ መጥፎ ያመራል፡፡ የቦርዱ አሰያየምና ስብጥር ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የመንግሥት ሚና አብሮ መቀነስ መቻል እንዳለበትና የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሠራተኞች በቦርዱ እንዲሳተፉ ቢደረግ፣ የመምህሩንና የሠራተኛውን መብት የሚያስጠብቅ ተደርጎ መዋቀርና የባለቤትነት ስሜት የሚሰጠው አካል እንዲኖር መወከል ያለባቸው ቢደረጉ የተሻለ አማራጭ ነው ብለዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የቦርድ አወቃቀሩ አሁን በሥራ ላይ እንዳለው እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ቦርዱ እንደ በፊቱ ጊዜና ስለተቋማቱ ምንም መረጃ የሌላቸውን ሰዎችን ሳይሆን፣ ጠንካራ የሆኑና የዩኒቨርሲቲን ሥራ የሚያውቁ ሰዎች ይሆናሉ ብለዋል፡፡ በተወሰነ ደረጃ የመንግሥት በጀት ያለበት በመሆኑ የመንግሥትና የማኅበረሰቡን ጥቅም መጠበቁን የሚከታተሉ፣ ነገር ግን ጊዜያቸውን የሚሰጡ አመራሮች እንዲኖሩ ተረጋግጦ ይዋቀራል ብለዋል፡፡

በቦርዱ ውክልና ውስጥ የዩኒቨርሲቲውን የወደፊት አቅጣጫ ለመወሰን፣ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለው ማኅበረሰብ በተወሰነ መጠን ውክልና እንዲኖረው ይደረጋልም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...