Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሕዝባችን ጦርነት በእጅጉ ጎድቶናል በእጅጉ ሰልችቶናል እያለ ነው!

ሕዝበ ክርስቲያኑ የኩዳዴን ፆም አጠናቆ የትንሳዔን በዓል እያከበረና ሕዝበ ሙስሊሙ የረመዳን ፆም የመጨረሻ ሳምንት ውስጥ እያለ፣ የአገርንና የወገንን ጉዳይ ለአፍታም ቸል እንደማይል የታወቀ ነው፡፡ የአገርና ውሎና አዳር ጉዳይ በእጅጉ አስጨናቂ ሆኖ ከፍተኛ ሥጋት ባጠላበት በዚህ ወቅት፣ ሕዝበ ክርስቲያኑም ሆነ ሕዝበ ሙስሊሙ በአንድነት በመሆን ዘለቄታዊ ሰላም እንዲሰፍን የሚፈለግበትን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑም ይታመናል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ከፍተኛ ዕልቂትና ውድመት ያደረሰ ጦርነት በማድረግ፣ ምናልባት ከዩክሬን ቀጥላ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት አገር መሆኗ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ በብዙ መቶ ሺዎች ያለቁበትና ሚሊዮኖች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉበት አውዳሚ ጦርነት በቅጡ ሳይቆም፣ እንደገና ለባሰ ጦርነት በሚያነሳሱ አይረቤ ምክንያቶች ተጠልፎ የመውደቅ አደገኛ እንቅስቃሴዎች በስፋት ሲታዩ ማስቆም ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመከራና ከጦርነት ጋር ፍቅር የያዘው እስኪመስል ድረስ፣ እየተመላለሱ ዕልቂትና ውድመት ውስጥ መገኘት ጤነኝነት አይደለም፡፡ ሕዝባችን ጦርነት ሰልችቶታል፣ ድህነት አስመርሮታል፣ በሥጋትና በፍራቻ መኖር በቃኝ እያለ ነው፡፡ 

በሰላማዊ መንገድ መነጋገርና መደራደር ሲቻል አገር አጥፊ ግጭት መቀስቀስ ወንጀል ነው፡፡ ልዩነትን በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ማስተናገድ እየተቻለ ጦር መነቅነቅ የአዋቂ አጥፊነት ነው፡፡ የአገር ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታቸው የእምነት ተቋማት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወኪሎች በኢትዮጵያ ምድር እንደገና የንፁኃን ደም እንዳይፈስ ድምፃቸውን ያስተጋቡ፡፡ መንግሥትም ሆነ ከመንግሥት ጋር ጉዳይ አለን የሚሉ ወገኖች ለሰላማዊና ለሕጋዊ ንግግሮች ቅድሚያ ይስጡ፡፡ ከዚህ ቀደም የፈሰሰው የንፁኃን ደም ሳይደርቅ እንደገና ለፍጅት መዘጋጀት አይገባም፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከመቀስቀሱና ያንን ሁሉ ዕልቂትና ውድመት ከማስከተሉ በፊት፣ የበርካቶች በዕንባና በልመና የታጀበ ተማፅኖ ወደ ጎን ተገፍቶ የደረሰው ሰቆቃ አይዘነጋም፡፡ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የገሃነም ተምሳሌት ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጅምላ ጭፍጨፋ ክሶች፣ አሁንም ድረስ ከአድማስ እስከ አድማስ እያስተጋቡ ናቸው፡፡ ከትናንቱ ጥፋት መማር አቅቶ ለሌላ የከፋ ጥፋት ዝግጅት ሲደረግ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ ማስቆም አለበት፣ ተገቢም ነው፡፡

በኢትዮጵያ በሽምግልና ችግርን መፍታት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የፈራረሰችውን ዩጎዝላቪያ የሚያስታውሱ ምልክቶች በኢትዮጵያ ከበቂ በላይ እየታዩ ስለሆነ፣ የሚመለከታቸው ሁሉ አገራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ደም መፋሰስን ያስቁሙ፡፡ ፋይዳ ቢስ ጥላቻና ቂም ይዞ የትም መድረስ እንደማይቻል መገንዘብ ይገባል፡፡ ትውልድ ገዳይ የሆነው ጥላቻና ቂም በቀለኝነት እንዲወገድ ዕገዛ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዓመታት የተረጨውን የከፋፋይነት መርዝ ማጥፋት የሚቻለው፣ ልዩነትን በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ለማስተናገድ ፈቃደኛ በመሆን ብቻ ነው፡፡ የእምነት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ዜጎች በማስተባበር፣ በአገር ላይ እያንዣበበ ያለውን አደጋ ለማስወገድ ይረባረቡ፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑና ሕዝበ ሙስሊሙ በዚህ እጅግ በጣም አሳሳቢ በሆነ ጊዜ ውስጥ ሆነው፣ ለአገራቸው ጠቃሚ የሆነ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉት ያጋጠሙ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሲያግዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዕፎይ ብላ መላው ሕዝቧም ተንፈስ የሚለው የጦርነት ጉሰማ ሲቆም ነው፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚሳተፉ በሙሉ፣ አገራቸው ኢትዮጵያ እየገባችበት ካለው የቁልቁለት መንገድ ማስቆም አለባቸው፡፡ ከእነሱ የሥልጣን ፉክክር በላይ ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ትሻለች፡፡ ከእነሱ ጥቅምና ፍላጎት በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ያለህ እያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከወጡበት ብሔር ወይም ከሚያራምዱት ዓላማ በታች ያደረጉ የፖለቲካ ልሂቃን፣ ራሳቸውን አደብ አስገዝተው ድርጊታቸውን ያስተውሉ፡፡ ፖለቲከኞችና አጃቢዎቻቸው ከራሳቸው ፍላጎትና ጥቅም በፊት አገር እንድትቀድም የማድረግ ዓላማ ከሌላቸው፣ ልዩነትን በሰላም አስተናግዶ መነጋገርም ሆነ የጋራ መፍትሔ መፈለግ አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ በሰላምና በዕድገት ወደፊት መራመድ የምትችለው፣ ከራሳቸው በላይ ለአገራቸው የሚቆረቆሩ ፖለቲከኞች ሲበዙ ነው፡፡ አሁን እንደሚታየው ግን የብዙኃኑ ድምፅ ታፎኖ አየሩን የተቆጣጠሩት፣ ከአገር በፊት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያስቀድሙ ብቻ ናቸው፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ምንም ዓይነት ፋይዳ የሌላቸው ከንቱ ድርጊቶች ላይ ጊዜን፣ ገንዘብንና ጉልበትን መጨረስ የሚያስከትለው መዘዝ ይታሰብበት፡፡ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖ በአገራዊ የምክክር መድረክ በርካታ ችግሮችን መልክ ለማስያዝ መረባረብ ሲገባ፣ እንደገና የግጭት አዙሪት ውስጥ ተንደርድሮ መግባት ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት ነው፡፡

በሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ በመሆን ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ ማስተናገድን የመሰለ የሠለጠነ ተግባር እያለ፣ በሕዝብ ስም እየማሉ ግጭት መጥመቅ ከባድ ኪሳራ አድርሷል፡፡ ሰላም አደፍራሽ ድርጊቶች ከየአቅጣጫው ሲከሰቱ ዝም ብሎ ማየት፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተዘዋዋሪ መንገድ ተባባሪ መሆን ማለት እንደሆነ መረዳት የግድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሕገወጦች ሕግ የለም የሚል መልዕክት በግልጽ እያስተላለፉ እንዳሻቸው ሆነው ጥፋት ሲፈጽሙ በስፋት ታይቷል፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጭምር ከሕገወጦች ጋር ሲተባበሩም ተስተውሏል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓተ አልበኝነት በሕግ የበላይነት ካልመከነ፣ የእርስ በርስ ፍጅት ያስከትላል፡፡ ይህ ደግሞ አገርን ያጠፋል እንጂ አያኗኑርም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ከማየት ይልቅ፣ እንወክለዋለን ለሚሉት ብሔር ወይም የፖለቲካ ጎራ ወገንተኝነት በማሳየት ለአንድነት የሚደረገውን ትግል መገዳደር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የከፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በሙሉ በሰላምና በነፃነት የሚያኖሩ ጠቃሚ ተግባራት ላይ ትኩረት ይደረግ፡፡

በተለይ በፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያ የተኮለኮሉ ጭፍን ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ከሐሳብ ጥራት ይልቅ፣ ስም አጥፊነት ላይ ተሰማርተው ኢትዮጵያውያንን አይከፋፍሉ፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ልዩነቶቻቸውን ይዘው በአገር ጉዳይ በአንድነት መቆም ይልመዱ፡፡ በማይረቡ ምክንያት ወጣቶችን፣ አዛውንቶችን፣ የሃይማኖት መሪዎችንና ለአገር የሚጠቅሙ ወገኖችን አይዝለፉ፡፡ ‹‹በሐሳብ መለያየት ጠላትነት አይደለም›› ተብሎ በሚቀነቀንበት ዘመናዊ ዓለም ውስጥ እየኖሩ፣ ከጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት መውጣት እያቃታቸው ለአገር መዋል ያለበትን ጊዜና ሀብት አያባክኑ፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም የማንም ጠላት ሳይሆን፣ ይልቁንም ሁሉም ከእነ ልዩነቶቻቸው በአገር ጉዳይ አንድ ላይ መቆም ይገባቸው ነበር፡፡ ጠላትነትን በመስበክ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርሳቸው ማላተም ሰይጣናዊ ድርጊት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ትብብር ታላቅ አገር መሆን እንደምትችል እየታወቀ፣ ጠላትነትነትን በማስተጋባት በብሔርም ሆነ በሃይማኖት መከፋፈል የለየለት ወንጀል ነው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑና ሕዝበ ሙስሊሙ በጋራ ሆነው እንዲህ ዓይነቱን የክፋት ድርጊት ማስቆም ተቀዳሚ ኃላፊነታቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነት በእጅጉ ጎድቶናል በእጅጉ ሰልችቶናል እያለ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...