Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኮንትሮባንድ የሚወጣውን ጫት ለመከላከል ፈቃደኝነት እንደሌለ ተነገረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በምሥራቅ ኢትዮጵያ በሶማሌ ክልልና አካባቢው በኮንትሮባንድ የሚወጣውን ጫት ለመከላከል ተባባሪ እንዳልሆኑ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ሕግ ተገዥነት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በምሥራቅ ኢትዮጵያና አካባቢዋ ‹‹ጫት ለአገር ውስጥ ፍጆታ ነው›› በሚል፣ በሕገወጥ መንገድ ከአገር ውስጥ እየወጣ ነው፡፡

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ፣ ከሚወጣው ጫት በተጨማሪ በሕጉ መሠረት ኤክስፖርት እየተደረገ ያለው በፀጥታ ኃይል እጀባ ነው፡፡ ሥርዓቱንና ሕጉን ተከትሎ ላኪዎች አምነውበት ኤክስፖርት ለማድረግ እንኳን ሶማሌ ክልል፣ በአካባቢው የሚገኙ የፀጥታ አካላት ተባባሪ አለመሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

በዚህም ምክንያት የጫት ኤክስፖርት አደጋ ላይ መውደቁንና አዳር ጭምር ጥበቃ ተደርጎና ሰው እየቆሰለና እየሞተም ጭምር የጉምሩክና የፌዴራል ፖሊስ አገሪቱ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እንዳታጣ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የጫት ምርት ኤክስፖርት ለማድረግ ፈታኝ መሆኑን ያስረዱት አቶ ሙሉጌታ፣ በከፍተኛ ጥረትና የሰው ሕይወት ጭምር መስዋዕትነት ተከፍሎ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንዳታጣ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ችግሮች በርካታ ቢሆኑም፣ በቅንጅት አለመሥራት ትልቁ ፈተና መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኮንትሮባንድን የመከላከል ኃላፊነት የጉምሩክና የፌዴራል ፖሊስ ብቻ አይደለም የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፣ የክልል ገቢዎች ቢሮና በፀጥታ አካላት ጭምር ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለጻ፣ ኮንትሮባንድን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት አንዳንድ ክልሎች በተቃራኒ ይቆማሉ፡፡ በተለይ በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ውስጥ የጉምሩክ ኮሚሽን የሚዋጋው ከኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ጋር ብቻ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሲቲ ዞን ኮንትሮባንዲስቶች በታጠቁ ሚሊሻዎች ጭምር እየተደገፉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዚህ አካባቢ ሚሊሻዎች በቀጥታ የሚደግፉት የኮንትሮባንድ አሳላፊዎችና ነጋዴዎችን በመሆኑ፣ ችግሩን ለመቆጣጠርና ለመከላከል አዳጋች ሆኗል ብለዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ኅብረተሰቡ ከሕገወጦች ጋር እንዳይወግን፣ ግንዛቤ ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች