የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ19ኛው መደበኛ ስብሰባው ተወያይቶ ለፓርላማው እንዲፀድቅ የላከው የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ፣ የፌዴራል ግዥዎች ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ በኤሌክትሮኒክስ እንዲያካሂዱ የሚደነግግ መሆኑ ተነገረ፡፡
ረቂቅ አዋጁ ከዚህ ቀደም የነበሩ በግዥና በንብረት አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የሚታዩ የተንዛዙና ብልሹ አሠራሮችን ይቀርፋል የተባለ ሲሆን፣ በሦስት ወይም በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ፀድቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጁን ተመልክቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ በመራበት ወቅት፣ አዋጁ የተቋማትን ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚያጎለብት መሆኑን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ይህን በተመለከተ የተጠየቀው የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣንም፣ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ብዙ የግዥ ኃላፊነቶችን ለተቋማት የሰጠ ነው ብሏል፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ረቂቅ አዋጁ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ የፌዴራል ግዥዎች በኤሌክትሮኒክስ እንዲካሄዱ የሚያስገድድ ብቻ ሳይሆን፣ እስከ 90 በመቶ ድረስ የግዥ ኃላፊነቶችን ለራሳቸው ለተቋማቱ የሚሰጥ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ሐጂ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከቀድሞው የሚለይባቸውን ሌሎች ነጥቦች ሲያስረዱም፣ ‹‹ቁጥጥሩ የጠበቀ ነው፡፡ ድሮ የቅጣት መመርያ የለውም ነበር፡፡ አሁን ግን በገንዘብ ሚኒስቴር የፋይናንስ አዋጅ ላይ ያሉ ቅጣቶች በሙሉ ይተገበራሉ፤›› ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ ከዚህ ቀደም ያልነበረ አዲስ ነገር ይዞ መምጣቱን ያከሉት አቶ ሐጂ ‹‹የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በዚህ የግዥ አዋጅ እንዲታቀፉ ተደርጓል፤›› በማለት አክለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በራሳቸው መንገድ ግዥ ሲያካሂዱ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ አሁን ግን ይህ ተለውጦ በአዲሱ አዋጅ ይካተታሉ ነው ያሉት፡፡
በመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን እየተተገበረ ያለው የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዢ (Electronic Government Procurement/e-GP) በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ74 በላይ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ማቀፉን፣ በታኅሳስ 2015 ዓ.ም. የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ ደግሞ 169 ድርጅቶችን ወደ ማዕቀፍ እናስገባለን፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹በሚቀጥለው ዓመት ማለትም በ2016 ዓ.ም. በሁሉም የመንግሥት ተቋማት አሠራሩ ተግባራዊ እንዲሆን እየሠራን ነው፤›› ብለው ነበር፡፡
በዲጂታል ቴክኖሎጂ በሚወጣ ጨረታ የሚከናወነው የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር በማስፈን፣ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን እንደሚያስቀር ይነገራል፡፡ አሠራሩ የወረቀት ወጪን ከማስቀረት ጀምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚቆጥብ፣ የተንዛዛ አሠራርን በማስቀረት ጊዜና ጉልበትን ከብክነት እንደሚታደግ ሲነገር ቆይቷል፡፡
ከሁሉም በላይ የተጫራቾችን ወይም የዕቃና የአገልግሎት አቅራቢዎችን አማራጭ በማስፋት ጥራቱ የተጠበቀ፣ ፈጣንና የተቀላጠፈ ግዥ የመንግሥት ተቋማት እንዲያደርጉ ያግዛል ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ አሠራሩ በሁሉም ደረጃ ባሉ መሥሪያ ቤቶች እንዳይተገበር የአዋጅ ክፍተት አንዱ ችግር ነው ሲባል ቆይቷል፡፡
ይህንን ዕውን ያደርጋል የተባለ አዲስ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል፡፡ አዋጁ በምክር ቤቱ ውይይት ተደርጎበት ግብዓትና ማሻሻያ ተካቶበት በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚፀድቅ ነው የሚጠበቀው፡፡
የመንግሥት ተቋማት ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ የሚፈልጉትን ዕቃና አገልግሎት ለመግዛት በአገሪቱ ያለው ገበያ አለመረጋጋት፣ በተለይም የዋጋ በፍጥነት መቀያየር ችግር እንደሆነባቸው ሲያማርሩ ይሰማል፡፡ አዋጁ ለዚህ ችግር መፍትሔ ይሆን ዘንድ ስለማስቀመጡ የተጠየቁት የግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዳይሬክተሩ፣ አቶ ሐጂ፣ እሱ በመመርያ እንጂ በአዋጅ አይመለስም ብለዋል፡፡ መጀመሪያ አዋጁ ይፅደቅ እንጂ ከወቅቱ ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ግዥ ለማካሄድ የሚረዳ መመርያ እንደሚዘጋጅ ነው የተናገሩት፡፡