Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ለምርታማነት ማነቆ እንደሆነበት የአማራ ክልል አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአማራ ክልል የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር እንደገጠማቸውና ለሥራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው፣ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡

‹‹ኢንዱስሪዎች የሚገጥማቸው የኃይል አቅርቦት ችግር፣ የማምረት አቅማችንን ከማሳደግ አኳያ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል፤›› ሲሉ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በክልሉ 897 በአምራች ዘርፍ፣ 295 በሌሎች (በግብርና፣ በሆቴልና ቱሪዝም) ዘርፎች፣ በአጠቃላይ 1,192 ኢንዱስትሪዎች ሙሉ ለሙሉ የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳለባቸው የገለጹት ኃላፊው፣ ‹‹በኃይል አቅርቦት ችግር ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ባለመግባታቸውና ባለማምረታቸው፣ በአገር ደረጃ እያጋጠመ ላለው የምርት አቅርቦት ችግር ምክንያት ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ከምርታማነት አኳያ በተያዘው በጀት ዓመት ኢንዱስትሪዎች ቢያንስ 60 በመቶ የማምረት አቅማቸውን ማሳደግ አለብን ብለን እንደ አገር እየሠራን ነው ያለነው፡፡ እስካሁን ድረስ ባለው አፈጻጸም ግን ገና እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ አልተቻለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

እንጅባራ ኢንዱስትሪ መንደር፣ ከሚሴ ኢንዱስትሪ መንደር፣ ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ መንደርና ጎንደር አካባቢ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ሙሉ ለሙሉ የኃይል አቅርቦት ችግር ስላለባቸው መፍትሔ ለማምጣት ሥራዎች እንደተከናወኑ፣ ነገር ግን ችግሩን የመቅረፍ ሙከራ በተደረገባቸውና በሌሎች አካባቢዎች አሁንም የኃይል አቅርቦት ችግር ያለባቸው ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በኢንዱስትሪዎች የሚስተዋለው ችግር የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ብቻ ሳይሆን የመስመር ዝርጋታ፣ የትራንስፎርመርና የቆጣሪ አቅርቦት ጭምር እንደሆነ የገለጹት አቶ እንድሪስ፣ ችግሩን ለመቅረፍ በክልሉ ከሚገኘው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አንዳንዶቹ ኢንዱስትሪዎች የሚያመርቷቸው ምርቶች ለኤክስፖርት ጭምር እንዲሆኑ ታስቦ እንደ ተቋቋሙ፣ ሆኖም ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ችግር ከመፍታት አኳያ የኃይል አቅርቦቱ ራሱን የቻለ ተግዳሮት እንደፈጠረ ያብራሩት ኃላፊው፣ ‹‹ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው ባለመሥራታቸው ምክንያት መያዝ ያለባቸውን የሰው ኃይል በአግባቡ አለመያዝ ወይም ደግሞ አልቀጠሩም ብሎ መውሰድ ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ምን እየተሠራ እንደሆነ ኃላፊው ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ‹‹ኤሌክትሪክ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በክልሉ ያለውን የኃይል ችግር ለመፍታት የክልሉ መንግሥት በጀት እየመደበ ችግሮችን እያቃለለ ነው፡፡ ነገር ግን የፍላጎት ሰፊ መሆን፣ በክልሉ ያለው የኃይል አቅርቦት በሚፈለገው ልክ አለመሆን፣ በተለይ ከለውጡ በፊት በክልሉ ላይ ይደረግ በነበረው የኢኮኖሚ አሻጥር የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ክልሉ በሚሸከመው ኢኮኖሚ ልክ ባለመሆኑ፣ ክልላችን አሁን እየተስፋፋ የመጣውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከማፋጠን አኳያ አሉታዊ ተፅዕኖ እየተስተዋለበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህን ችግር ለመፍታት ደግሞ በተለይ በክልሉ የኃይል ማሠራጫ ጣቢያዎች (Substations) የሚያስፈልጓቸው አካባቢዎች ግንባታ እንደተጀመረ፣ ይህ ጅማሮ ቢኖርም ሰፋፊ የአውታሮች ዝርጋታና የኃይል አቅርቦት እንደሚያስፈልግ፣ ችግሩንም ለመፍታት ደረጃ በደረጃ ከመንግሥት ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ አቅም ደግሞ የመስመር ዝርጋታዎችንና አንዳንድ መለስተኛ ችግሮችን ለመፍታት የክልሉ መንግሥት በ2015 በጀት ዓመት ብቻ 400 ሚሊዮን ብር በመመደብ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ውስጥ ያሉ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የውኃ፣ በአጠቃላይ የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማቶችን ችግር ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያጋጠመውን የኃይል አቅርቦት ለመፍታት በተደረገው ጥረት፣ 667 (56 በመቶ) የሚሆኑ ኢንዲስትሪዎች የነበረባቸውን ችግር ለመፍታት መቻሉ ተብራርቷል፡፡

ባለሀብቶች ከአርሶ አደሩ መሬት ከተቀበሉ በኋላ ለማልማት ባስመዘገቡት ፕሮጀክት እንደማይሰማሩና የተሰጣቸውን መሬት አጥረው እንደሚጠፉ፣ በክልሉ የሚገኙ አርሶ አደሮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የአርሶ አደሮቹን ቅሬታ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ እንድሪስ፣ ‹‹ከምንም በላይ በተለይ ከአርሶ አደሩ መሬት ጋር ተያይዞ፣ ተበድረው የሚጠፉትን በተመለከተ በዋናነት ሁለት ሥራዎችን ማለትም አንደኛ ከተቋማችን አኳያ ያለውን የአሠራር ክፍተት በመዳሰስ፣ ሁለተኛ ደግሞ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተቋሙ ያሉትን የአሠራር ክፍተቶች ሲያብራሩም፣ ‹‹አንዳንዱ በራሳችን የአሠራር ክፍተት ምክንያት ባለሀብቶች መሬት ተፈቅዶላቸው ከወሰዱ በኋላ የክትትልና የቁጥጥር ችግር አለ፡፡ በመሆኑም ነገሮችን ማጠናቀቅ አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ምን ያህል ባለሀብቶች መሬት ተቀብለው እንደጠፉ፣ ባልተመዘገቡበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደተሰማሩ ለማብራራት አይቻልም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አንድ ባለሀብት መሬት ለመውሰድ ፈቃድ ማግኘት የሚችለው ምን ደረጃ ላይ ሲደርስ እንደሆነና ምን መሥፈርቶችን ሲያሟላ እንደሆነ እስካሁን በነበረው አሠራር የሚከታተሉበት አሠራር አለመኖሩንና አሁን አሠራር እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህ በኋላ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መፍታት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ በክልሉ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ግን እየጨመረ እንደመጣ፣ ባለፉት ሰባት ወራት ክልሉ 344.4 ቢሊዮን ብር ላስመዘገቡ ባለሀብቶች ፈቃድ እንደሰጠ፣ ከእነዚህም መካከል 2,755 የሚሆኑት ወደ ክልሉ ገብተው ኢንቨስት የማድረግ ፈቃዳቸውን እንደወሰዱ፣ ባለሀብቶቹ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ500 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ፣ በግንባታ ላይ ያሉትን ሳያጠቃልል በክልሉ በአጠቃላይ ከ3,200 በላይ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ተብራርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች