- ሁለት የግብረ ሰናይ ድርጅት ሠራተኞች መገደላቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል
የኢትዮጲያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣ ከሰሞኑ የክልል ልዩ ኃይል አባላትን በአዲስ መልክ ለማደራጀት በተጀመረው ሥራ በዜጎች፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትና ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እንዲቆም ጠየቀ፡፡
ምክር ቤቱ ሚያዝያ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የክልሎችን ልዩ ኃይል መልሶ ለማደራጀት ከተደረሰው ውሳኔ ጋር ተያይዞ እየተፈጠሩ ያሉ ሁኔታዎችን ምክር ቤቱ በአንክሮ እየተከታተላቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡
የተፈጠረው ክስተት በተለይም በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት በሰዎች ላይ የአካል ጉዳትና የሕይወት መጥፋት መድረሱን እንዳረጋገጠ ጠቅሶ መንግሥት ለዜጎች ተገቢው ጥበቃም እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በመግለጫው፣ ሕይወታችው ካለፉ ሰዎች መካከል የካቶሊክ ሪሊፍ ሰርቪስ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሁለት ሠራተኞች እንዲሚገኙበት፣ እንዲሁም በሥራ ላይ በነበሩ የቀይ መስቀል ሠራተኞች ላይም ጉዳት የደረሰ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሰብዓዊ ድጋፍ ሥራ ላይ በተሰማሩ ሠራተኞች እየደረሰ ያለው ተደጋጋሚ ጥቃትና ህልፈተ ሕይወት በእጀጉ እንዳሳዘነው የጠቀሰው ምክር ቤቱ የመሰል ጥቃቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች የሚያከናውኑትን የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራን በማስተጓጎል፣ የዕለት ዕርዳታ የሚፈልጉ ዜጎች ተገቢው ድጋፍ በወቅቱ እንዳይደርሳቸው የሚያደርግ በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ አሳስቦኛል ብሏል፡፡
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኙ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡