የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር መሥራችና ቃል አቀባይ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው በባህር ዳር ከተማ ሆምላንድ ሆቴል በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር ውሎ መታሰሩ ተገለጸ፡፡
ሚያዚያ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ምሽት 11፡30 ሰዓት በባህር ዳር ከተማ በቁጥጥር ሥር የዋለው ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ሠራተኛ ለጥያቄ እንደሚፈለግ ተነግሮት ከነበረበት ሆቴል ወደ ውጭ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ የመከላከያ ልብስ የለበሱ ሰዎች በመኪና ጭነው እንደወሰዱት የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
የአራት ኪሎ ሚዲያ ተባባሪ መሥራችና የቅርብ ጓደኛው ጋዜጠኛ አላዛር ተረፈ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ጋዜጠኛ ዳዊት በተባለው ቀን በባህር ዳር በቁጥጥር ሥር እንደዋለ መስማቱን፣ ነገር ግን ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን የሰማ ቢሆንም እንዴትና በምን እንዳመጡት መረጃው እንደሌለው አስታውቋል፡፡
ጋዜጠኛ ዳዊት በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣ ሪፖርተር ጋዜጣ ወደ ህትመት እስከገባበት ሰዓት (ሐሙስ ሚያዚያ 5 ቀን 2015 ዓ.ም.) ድረስ ወደ ፍርድ ቤት አለመቅረቡ ተረጋግጧል፡፡ በአራት ኪሎ የሚገኘውንና ‹‹አራት ኪሎ ሚዲያ›› የሚሠራበትን ቢሮ የፀጥታ አካላት ፈትሸው፣ በቢሮው ውስጥ የነበሩ ሁለት ላፕቶፖችና አራት ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች እንደተወሰዱ ጋዜጠኛ አላዘር ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡ ጋዜጠኛው የት እንዳለ መረጃ እንደሌለው ጋዜጠኛ አላዛር ተናግሯል፡፡
ጋዜጠኛ ዳዊት ወደ በባህር ዳር ያመራው በቅርቡ በአራት ኪሎ የሚገኘው ስቱዲዮ ውስጥ የነበሩ ካሜራና የቀረጻ መሣሪያዎች ባልታወቁ ኃይሎች በመዘረፉ ሀብት ለማፈላለግ ወደ ባህር ዳር መሄዱን ጋዜጠኛ አላዛር አክሎ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ጥበቡ በለጠ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ጋዜጠኛ ዳዊት መታሰሩን መስማታቸውን ገልጸው፣ ‹‹በተለያዩ ትልልቅ መገናኛ ብዙኃን ሠርቷል፡፡ ጎበዞች ከምላቸው ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው። ለሙያው ታታሪ ነው። አገር ወዳድ ነው። ተስፋ ከጣልኩባቸው ወጣት ጋዜጠኞች ውስጥ ዳዊት ከፊቴ ወዲያው ድቅን ይላል። ዳዊት ታሰረ ሲባል ጋዜጠኝነት፣ ሙያው ራሱ ይደነግጣል›› ብለዋል፡፡ አቶ ጥበቡ የሚመለከተው ክፍል የማኅበራችንን መሥራችና አመራር አባል የሆነውን ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻውን ቶሎ ብሎ ወደ ሥራ ገበታው እንዲመልስልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ጋዜጠኛ ዳዊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በፋና ቴሌቪዥን፣ በኢትዮጵያ ፕሬስ፣ በኢቢኤስ ቴሌቪዥንና በበርከታ ሚዲያዎች የሠራ ሲሆን፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የ‹‹አል አይን ኒውስ›› ጋዜጠኛ ነበር፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት ‹‹አራት ኪሎ ሚዲያ›› የተሰኘ የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መሥርቶ እየተንቀሳቀሰ እየሠራ ይገኛል፡፡