- ክቡር ሚኒስትር የክልል ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ ላይ ፓርቲያችን ማጣራትና ማረጋገጥ የሚፈልጋቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ነው እርስዎን ለማግኘት የጠየቅሁት።
- ሌሎች ፓርቲዎችም የእናንተን መንገድ ቢከተሉ ጥሩ ነበር።
- እንዴት?
- ምክንያቱም አበክረው ሲጠይቁት ለነበረው ጥያቄ መንግሥት ምላሽ ሲሰጥ ጾመኞች ነን አሉ።
- ክቡር ሚኒስትር እኛም ለመለየት ተቸግረናል።
- ምኑን?
- የትኛው የፍስክ፣ የትኛው ደግሞ የጾም እንደሆነ።
- ለምን?
- ምክንያቱም አንዳንድ አመራሮች መንግሥት ልዩ ኃይልን የማፍረስም ሆነ የመበተን ፍላጎት የለውም ይላሉ።
- እውነት ነው።
- ሌሎች አመራሮች ደግሞ በመንግሥት ውሳኔ መሠረት የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ መከላከያ እንደሚቀላቀሉ ይገልጻሉ።
- ልክ ነው!
- የቱ ነው ልክ?
- ሁለቱም፡፡
- የክልል ልዩ ኃይል አይፈርስም?
- እኛ ልዩ ኃይልን የማፍረስ ዕቅድ ጨርሶ የለንም። መልሶ የማደራጀት ውሳኔ ነው ያሳለፍነው፡፡
- ስለዚህ ወደ መከላከያ ይቀላቀላል የሚባለው ትክልል አይደለም?
- ትክልል ነው እንጂ! ይቀላቀላሉ።
- ካልፈረሱ እንዴት ሆነው ወደ መከላከያ የሚቀላቀሉት?
- ምን ችግር አለው? ቀላል እኮ ነው።
- በምን ዓይነት አደረጃጀት ሊቀላቀሉ ይችላሉ?
- ማለት?
- ከተቀላቀሉ በኋላ በመከላከያ ሠራዊት የአማራ ልዩ ኃይል ወይም የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ነው አደረጃጀታቸው?
- እርስዎም እንደ ሌሎቹ ተቃዋሚዎች ከሥጋው እጾማለሁ ሊሉ ነው?
- አይደለም፣ ተሳስተዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እርስዎ ነዎት የተሳሳቱት፡፡
- እንዴት?
- ምክንያቱም የጠቀሱት አደረጃጀት በሙከራ ጭምር የሚያስጠይቅ ነው።
- የምን ሙከራ?
- ሕገ መንግሥቱን በኃይል የመናድ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እንዴት እንደዚህ ይላሉ?
- በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የሌለ የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀትን ማንሳት ሕግ መንግሥቱን የመናድ ዕሳቤ ቅጥያ ነው!
- ክቡር ሚኒስትር ከእርስዎ ማብራሪያ ተነስቼ ያልኩት ነው?
- እኔ እንደዚያ ወጣኝ?
- መንግሥት የክልል ልዩ ኃይልን የማፍረስ ዕቅድ የለውም ነገር ግን ወደ መከላከያና ሌሎች የፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ይቀላቀላሉ አላሉም?
- ብያለሁ፡፡
- ታዲያ?
- እስኪቀላቀሉ ድረስ ነዋ!
- እንደዚያ ከሆነ ያድርጉልኝ?
- ከምኑ?
- ከሥጋውም ከመረቁ!
[የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪ ወደ ሚኒስትሩ ደውለው መንግሥት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ላይ ማብራሪያ እየጠየቁ ነው]
- ክብርት ሚኒስትር፣ ሰላም?
- ሰላም ነኝ፣ ምን እግር ጣለዎት?
- ምን ስልስ ጣለዎት ነው የሚባለው።
- ኪኪኪኪ … እውነት ነው። እንዲህ ስንደዋወል ደስ ይላል። ምን ጉዳይ ገጠመዎት?
- መቼም አንዳንዴ ግርታ አይጠፉም ወይም ያንን ስልት እኛ ላይም መጠቀም ጀምራችሁ ይሆናል።
- የቱን ስልት?
- ኮንፊውዝና ኮንቪንስን፡፡
- እንዴት?
- መንግሥት ሰሞኑን የሰጠው መግለጫ ግራ አጋብቶናል።
- ለምን?
- ክቡር ሚኒስትር በግልፅ እንደሚረዱት የመከላከያ ሠራዊት አካል ያልሆኑ የፀጥታ ኃይሎች ከትግራይ ክልል እንደሚወጡ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማስፈጸሚያ ተስማምተናል።
- አዎ። ትክክል ነው።
- በፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ የሰላም ስምምነቱ ዓላማ ተብለው የተዘረዘሩት ነጥቦች አንዱም በቀጥታ ከዚህ ጋር እንደሚገናኝ የሚገነዘቡ ይመስለኛል።
- ልክ ነው። እስኪ ያስታውሱኝ፣ የትኛው ነጥብ ነበር?
- በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል የተስተጓጎለውን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ወደነበረበት መመለስ አንደኛው የስምምነቱ ዓላማ ነው።
- አዎ። አስታወስኩት። ትክክል ነው።
- መንግሥት ሰሞኑን የሰጠው መግለጫ ግን ይህንን ያላገናዘበ ይመስላል። በእኛ ላይም ግራ መጋባትን ፈጥሯል።
- የትኛው መግለጫ ነው?
- የክልል ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ የተሰጠው።
- ይህ መግለጫ ደግሞ እናንተ ላይ እንዴት ግርታ ይፈጥራል?
- ፈጥሯል!
- እኮ እንዴት?
- ምክንያቱም የክልል ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ ከፕሪቶሪያው ስምምነት ጋር አይገናኝም ይላል።
- ልክ ነው ይላል።
- እርስዎም ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ የመንግሥት ውሳኔ ከሰላም ስምምነቱ ጋር አይገናኝም ብለው ቃል በቃል ደግመውታል።
- አይገናኝም ብቻ አይደለም ያልኩት፡፡
- እ…?
- ከሰላም ስምምነቱም አይጣረስም ብያለሁ!
- እንደዚያ ማለትዎን አልሰማሁም።
- እንደዚያ ነው ያልኩት።
- ከሆነማ መግለጫውም እንደ እርስዎ ነው።
- እንደ እርስዎ ማለት?
- ሰላማዊ ነው።
- ነገር ግን ስምምነቱን ለማስፈጸም ብለን የወሰነው አይደለም።
- ለምንድነው?
- የአገራዊ ዕቅዳችን አካል ስለሆነ ነው።
- ቢሆንም …ክቡር ሚኒስትር ቢሆንም?
- ቢሆንም ምን?
- ሚዛናዊ ነው!