ሚያዝያ 16 ቀን 1999 ዓ.ም. በሶማሌ ክልል ከደገ ሀቡር ከተማ 30 ኪሎ ሜትር በሚርቀው አቦሌ የነዳጅና ጋዝ መፈለጊያ መንደር የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት ዘጠኝ የቻይና ዜጎችን ጨምሮ 74 ሰዎች መገደላቸው ተሰማ፡፡ የቻይናው ፔትሮሊየምና ኬሚካል ኮርፖሬሽን (Sinopec) አጋር ድርጅት የሆነው ዞንግዩዋን ፔትሮሊየም ኤክስፕሎሬሽን ድርጅት (ZPAB) በዚህ አካባቢ የነዳጅና ጋዝ ፍለጋ ያካሂድ ነበር፡፡ በድርጅቱ ሠራተኞች ካምፕ ላይ የደፈጣ ጥቃቱ ሲፈጸም ከተገደሉት ውጪ ሰባት ቻይናውያን መታገታቸውም ተነግሮ ነበር፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጥቃቱን የተደራጀ ጥቃት ብለው ሲገልጹት፣ የጊዜው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ በረከት ስምኦን በበኩላቸው ጨካኝ ጥቃት ነው ማለታቸው ተዘግቦ ነበር፡፡ አቶ በረከት ይህን ጥቃት ያደረሱትን ኃይሎች ተከታትሎ፣ የገቡበት ገብቶ አድኖ የእጃቸውን ለመስጠት፣ የመከላከያ ሠራዊት ዘመቻ መጀመሩን ማስታወቃቸው እንዲሁ ተዘግቦ ነበር፡፡
በጊዜው ከነበረው ሁኔታ አንፃር ግን ጥቃቱ የሶማሌ ክልል ፀጥታ ሁኔታ እየተባባሰ መሄዱን አመላካች ተደርጎ ነበር የታየው፡፡ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር የሚፈጽማቸው የደፈጣ ጥቃቶችና ግድያዎች የክልሉን መንግሥት በጅግጅጋና በተወሰኑ ከተሞች የተወሰነ አድርጎት ነበር ይባላል፡፡ በጅግጅጋ ከተማም ጭምር የቦምብ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተደጋግሞ ይሰማ የነበረ ሲሆን፣ በክልሉ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም በወታደራዊ ኮንቮይ አጀቦች የታገዙ ነበሩ፡፡
የቻይናው ነዳጅ ፈላጊ ኩባንያ ካምፕ መጠቃትን ተከትሎ ግን በፌደራል መንግሥቱ እገዛ በክልሉ የፀጥታ መዋቅር ትልቅ ለውጥ መደረግ እንደተጀመረ ይነገራል፡፡ እስከዛን ጊዜ ድረስ በአካባቢ ሚሊሻዎች ይታገዝ የነበረው የመከላከያና የክልሉ ፖሊስ የፀጥታ ጥበቃ አዲስ አደረጃጀት ወደ መፍጠር ተዛወረ፡፡ የልዩ ኃይል (ልዩ ፖሊስ) ምሥረታ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማሌ ክልል ተጀመረ፡፡ ከዚህ ጥቃት በኋላ የተካሄዱ የኦብነግ ኃይሎችን የማደንና የመደምሰስ ዘመቻዎች በልዩ ኃይል መታገዝ እንደጀመሩ ይነገራል፡፡
አመሠራረቱ ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ከፖሊስ ሠራዊት መተዳደሪያ ሕጎች ጋር የማይጋጭ መሆኑ የተነገረለት ልዩ ፖሊስ፣ በሶማሌ ክልል ዋናው የፀጥታ አስከባሪ ወደ መሆን በአንዴ ተሸጋገረ፡፡ በይፋ የተመሠረተው እ.ኤ.አ. 2009 ነው ቢባልም ከ2007 ጀምሮ ግን ወደ ሥራ ገብቶ እንደነበር ይነገራል፡፡ ዛሬ በእስር ላይ የሚገኙት የክልሉ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ልዩ ፖሊሱን እንደመሠረቱት ይነገራል፡፡ በክልሉ የፍትሕና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊነታቸው ወቅት ልዩ ፖሊስ የሚለውን አደረጃጀት በመፍጠር፣ በእሳቸው ዕዝ ሥር ሆኖ እንደ ኦብነግ ያሉ ታጣቂዎችን የማደን ሥራ ሲሠራ መቆየቱ ይነገራል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሲሆኑም አደረጃጀቱ በራሳቸው እንዲታዘዝ አድርገው እንዳስቀጠሉት ነው በስፋት የሚታወቀው፡፡
የክልል ልዩ ፖሊስ ወይም ልዩ ኃይል የማደራጀቱ ጉዳይ እ.ኤ.አ. በ2016 የጎላ ወቀሳና ትችት ሲቀርብበት አልታየም፡፡ በሶማሌ ክልል የልዩ ኃይሎች ፀጥታ ለማስከበር በሚል ሰላማዊ ዜጎችን ሰለባ የሚያደርጉ ዕርምጃዎች ይወስዳሉ የሚለው የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ስሞታ ለብዙ ዓመታት በቸልታ ሲታለፍ መኖሩ ይነገራል፡፡
የሰብዓዊ መብት ጥሰት ልዩ ኃይሎች ይፈጽማሉ የሚለው ወቀሳ ኦብነግና አልሸባብን የመሳሰሉ ኃይሎችን ከሶማሌ ክልል ከማጥፋታቸው ጋር ተነፃፀሪ ሆኖ እየቀረበ ልዩ ኃይሎች ክልሉን አረጋጉ እንጂ፣ ወንጀል አልፈጸሙም የሚል መከላከያ በመንግሥት በኩል ሲቀርብ ነው የቆየው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 ግድም ልዩ ኃይል ፖሊሶች ከክልሉ አልፈው ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች ጋር ግጭት መፍጠር ጀመሩ የሚለው ጉዳይ ሲነሳ ግን የልዩ ኃይል አደረጃጀት ጉዳይ ፈተና ሆኖ ብቅ አለ፡፡
በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በልዩ ኃይሎች መካከል የሚፈጠረው ግጭት ወደ አንድ ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች መፈናቀል ሰበብ እንደሆነ ተነገረ፡፡ ልዩ ኃይል የክልሎች መከላከያ ሠራዊት እየሆነ መጥቷል የሚለው ስሞታም አሳሳቢ ነው ተብሎ መነሳት ጀመረ፡፡ የልዩ ኃይል የሚባለው የፖሊስ አደረጃጀት በዚህ ጊዜ በሁሉም ክልሎች መፈጠሩንና ይህም ለአገር ህልውና ፈተና መደቀኑ መነገር ጀመረ፡፡ ልዩ ኃይሎች ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጋር የሚገዳደር የመሣሪያ ትጥቅ መያዛቸውና በክልል መንግሥታት በኩል በጠንካራ የሎጂስቲክስ አቅርቦት ይደገፋሉ መባሉ ደግሞ ሌላ የአገር ራስ ምታት ሲባል ቆየ፡፡
በሶማሌ ክልል ተጀምሮ በሌሎች ክልሎች የተስፋፋው የልዩ ኃይል ፖሊስ አደረጃጀት ጉዳይ በአገራዊ ለውጡ ዋዜማና በለውጡ ማግሥት አገራዊ ችግር ነው ተብሎ ደጋግሞ ሲነሳ ነበር፡፡ የልዩ ኃይል ፖሊሶች የትጥቅና የሎጂስቲክስ እንዲሁም የኃይል አጠቃቀም መሥፈርት በሕግ የተደነገገ ስታንዳርድ ሊወጣለት ይገባል የሚለው ጥያቄ ጎልቶ ቢነሳም፣ በተጨባጭ ዕርምጃ ለመውሰድ አለመቻሉ ግን ሲያነጋግር ነው የቆየው፡፡ የሚወስዱት ሥልጠናም ቢሆን መሥፈርት ይኑረው ተብሎ ነበር፡፡ የልዩ ኃይል ፖሊሶች የሥልጣን ወሰንና ሕግ የማስከበር መሥፈርት እስከምን መሆን አለበት የሚለው ጉዳይም እንዲሁ በእንጥልጥል ሲንከባለል ነው የቆየው፡፡
በኢትዮጵያ ወጥ የሆነ የፀጥታ ኃይል አደረጃጀት ይፈጠር የሚለው ጉዳይ ብዙዎችን ቢያግባባም፣ ይህ ጉዳይ ዕልባት ሳያገኝ የለውጡ ዓመታት መንጎድ ጀመሩ፡፡ ከለውጡ በኋላ በመጡ ውዝግቦች የተነሳ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል አለመግባባቱ መስፋት ሲጀምርና አዳዲስ የኃይል አሠላለፍ ሲፈጠር ደግሞ፣ የተፈጠሩትንም የልዩ ኃይልና የተለያዩ ፀጥታ ኃይሎች መዋቅር ወደ አንድ ለመሰብሰብ ፈተናው የበለጠ እየከበደ መሄዱ ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የፀጥታ ችግር መባባሱ፣ ግጭቶችና መፈናቅሎች መስፋፋታቸው በተለያዩ ክልሎችና የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን ቁርሾና አለመተማመን የበለጠ እያሰፋው ሄደ፡፡ ይህን ጊዜ ደግሞ የልዩ ኃይል መዋቅርን ከማፍረስ ይልቅ የበለጠ እያጠናከሩ መቀጠል እየተስፋፋ የመጣ አዲስ የፖለቲካ ፋሽን መሆን እንደ ጀመረ ይነገራል፡፡ ይህ ጉዳይ ሳይፈታ ዓመታት መቆጠራቸው ደግሞ አገሪቱ አሁን ለገባችበት ቀውስ አንድ መነሻ እንደሆነ ነው ብዙዎች የሚስማሙት፡፡
የትግራይ ክልል ጦርነት ከመፈንዳቱ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከብሔራዊው ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ‹‹የልዩ ኃይል በማብዛትና የፀጥታ ኃይል ቁጥር በመጨመር ሰላምና ፀጥታን ያረጋገጠ ክልል የለም፤›› ብለው ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹ይህን ያህል አስመረቅኩኝ እያለ በቴሌቪዥን ይነግረናል እንጂ፣ ባስመረቀው ኃይል ልክ ክልሉን ሰላም ያደረገ የለም፡፡ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ የትኛውም ክልል የክልሉን ሰላም የማረጋገጥ ብቃት አልፈጠረም፡፡ መከላከያ ድንበር መጠበቁን ትቶ በየክልሉ ሰላም ለማስፈን የሚሰማራበት ምክንያት ክልሎች የራሳቸውን፣ የከተማቸውንና የዞናቸውን ሰላም መጠበቅ ስላልቻሉ ነው፡፡ ኦሮሚያ፣ አማራ ወይም ሶማሌ ሊወጋኝ ይችላል ብሎ የሚያደርገው የትጥቅ ክምችት ካለ፣ አማራ ከጎኑ ያሉትን እየጠረጠረ የትጥቅ ክምችት የሚያደርግ ከሆነ እንደ አገር ማደግ አንችልም፡፡ ሌሎች ኃይሎች መጥተው እንዳይወሩን እንጂ መጨነቅ ያለብን፣ እርስ በእርስ የምናደርገው የውጊያ ዝግጅት ጥፋት ብቻ ነው የሚሆነን፤›› ብለው ተናግረውም ነበር፡፡
በጊዜው ክልሎች የልዩ ኃይል ሠራዊት በማስመረቅ ተጠምደው ነበር፡፡ እከሌ ክልል ይህን ያክል ልዩ ኃይል አስመረቀ የሚለው ዜናም በተደጋጋሚ መደመጡ ቀጥሎ ነበር፡፡ መንግሥት በወቅቱ ይህን የልዩ ኃይል የማደረጃት የክልሎች ሽሚያ ለምን አላስቆመም ነበር የሚለው ጥያቄ ዛሬም ድረስ በተለያዩ ወገኖች ይነሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ያን ንግግር ከተናገሩ በኋላ በአገሪቱ ብዙ ነገሮች ተፈጥረዋል፡፡ በተለይ የትግራይ ክልል ጦርነት መፈንዳት የልዩ ኃይሎችንና የታጠቁ ኃይሎችን አደረጃጀት የበለጠ ተፈላጊ እንዳደረገው ይታወሳል፡፡ ሕወሓት ጦርነቱን የጀመረው የልዩ ኃይልና የሚሊሻ ኃይል ተጠቅሞ ነበር፡፡ በኋላ የትግራይ ሠራዊት (ቲዲኤፍ) የሚል ስም እስኪወጣ ድረስ ውጊያው በትግራይ በኩል ይደረግ የነበረው ከመደበኛ ውጪ በሆኑ የታጠቁ ኃይሎች መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
የኢትዮጵያ ኃይሎች በሚል ሕወሓትን የገጠመው ኃይልም በመከላከያ ዕዝ ሥር እየተመራ ውጊያውን ያካሂድ እንጂ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ እንዲሁም የሌሎች ክልሎች ልዩ ኃይሎችን ያስተባበረ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዚያ ወቅት ደግሞ ለእነዚህ ከመደበኛው ውጪ ለሆኑ የታጠቁ ኃይሎች ከፍተኛ አድናቆትና ውዳሴ ሲቀርብላቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የልዩ ኃይልን የውጊያ ሚናዎች በተደጋጋሚ በማድነቅ ማንሳታቸው አይዘነጋም፡፡ በህልውና ውጊያው ወቅት የተሠለፉ የክልል ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ የተነሱ ወቀሳዎችን መንግሥት በተደጋጋሚ ውድቅ ማድረጉም እንዲሁ፡፡
‹‹የፌደራል መንግሥት እስከወሰነበት ጊዜ ድረስ የአማራ ልዩ ኃይል ወደ ውጊያው አልገባም፡፡ እኛም የወሰንነው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥልጣን ስላለን ነው፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል እዚህ ጋ ሸፍንልን፣ የአፋር ልዩ ኃይል እዚህ ቦታ ሸፍን፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ደግሞ ኃይል እያወጣን ስለሆነ ይህን ቀጣና ሸፍን ብለናል፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ሁሉም ኃይል በአንድ ዕዝ ሥር እንዲገባ አድርገናል፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ እንችላለን፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል ከዚህ ይውጣ ወይም ወደ እዚህ ቦታ አይግባ ማለት አይቻልም፡፡ ነገ ጠዋት መንግሥት ከፈለገ የአማራ ልዩ ኃይል የመከላከያ ሠራዊት አካል ነው ሊል ይችላል፡፡ ከሌላ አገር የመጣ አስመስሎ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል መስዋዕት እየከፈለ ያለው በመንግሥት የተሰጠውን ግዳጅ ለመወጣት ነው፡፡ ከፈለገ መንግሥት ነገ ጠዋት ጅግጅጋ ጫፍም ሊያሰማራው ይችላል፡፡ ኢትዮጵያዊ ነው ያስታጠቅነውና ያሠለጠንነው ኢትዮጵያን እንዲከላከል ነው ሌላ ምንም ምክንያት የለም፤›› በማለት ዓብይ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት በፓርላማ መናገራቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በፍጥነት ተለዋዋጭ ነው በሚባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በአጭር የጊዜ ልዩነት የልዩ ኃይልም ሆነ ሌሎች የትጥቅ አደረጃጀቶችን ተፈላጊነት እንደቀየረው ነው የሚነገረው፡፡ በተለይ ጦርነቱ ወደ መገባደዱ ሲቃረብ መንግሥት ከመደበኛው ውጪ የሆኑ የትጥቅ ኃይሎችን እንደማይፈልግ ምልክቶች መታየት ጀምረው ነበር፡፡
አምና በተለይ ኢመደበኛ አደረጃጀት በሚል የተጀመረው የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታትና የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ እንቅስቃሴ፣ መንግሥት ልዩ ኃይልና መከላከያ ብቻ ይበቁኛል ሌሎቹ ትጥቅ ይፍቱ የሚል ዕቅድ ያለው መሆኑን የጠቆመ ነበር ይባላል፡፡ በተለይ በአማራ ክልል በሰፊው የተካሄደው ኢመደበኛ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታትና በቁጥጥር ሥር የማዋል ዕርምጃ በዋናነት የአማራ ፋኖ አደረጃጀትን ለማፍረስ የተካሄደ ነው በሚል ተቃውሞ ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡ ያም ቢሆን ግን መንግሥት ኢመደበኛ ያላቸውን ኃይሎችን ትጥቅ በማስፈታት ሕግ የማስከበር ሥራውን በስኬት ማገባደዱን ገልጾ ነበር፡፡
‹‹የጀገነ አንድም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር አባል ይሆናል፣ የአማራ ልዩ ኃይል አባል ይሆናል፣ የሚሊሻ አባል ይሆናል፣ አልያም ስትፈልጉ ጥሩኝ ብሎ ቤቱ ገብቶ ያርሳል፡፡ በየመንደሩ ተሰባስቦ ኢመደበኛ ኃይል መፍጠር ጥሩ አይደለም›› በማለት በጊዜው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ በኢመደበኛ አደረጃጀት ችግር የፈጠሩ ኃይሎች ላይ መንግሥት የማስታገስ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በመንግሥት ሠልጥኖ ታጥቆ ከመከላከያ ክላሽ እየቀማ የሚከዳና አገር የሚረብሽ ኃይል መፈጠሩን መናገራቸው አነጋጋሪ ነበር፡፡
መንግሥት ኢመደበኛ ያላቸውን ኃይሎች የማስታገስና የሕግ የበላይነት የማስከበር ዕርምጃ መውሰዱን ይፋ ካደረገ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ፣ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን መልሶ የማቋቋም ዕርምጃ እንደሚወስድ ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡ ይህ ዕርምጃ በሁሉም ክልሎች የሚካሄድና የአገሪቱን ህልውና ከአደጋ የመጠበቅ ነው ተብሏል፡፡ የክልል ልዩ ኃይል አባላት ከፈለጉ መከላከያ ሠራዊትና መደበኛ ፖሊስን እንዲቀላቀሉ ይደረጋል ያለው መንግሥት መደበኛ ከሚላቸው መከላከያ፣ የፌደራል ፖሊስና የክልል ፖሊስ ኃይሎች ውጪ በአገሪቱ ልዩ ኃይል ወይም ልዩ ፖሊስ እየተባለ የሚቀጥል አደረጃጀት እንደማይኖር ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡ በመደበኛ የፀጥታ ኃይል መዋቅሮች ውስጥ መቀጠል የማይፈልግ የልዩ ኃይል አባል ደግሞ መቋቋሚያ ድጋፍ ተደርጎለት ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲገባ እንደሚደረግ ነው መንግሥት ያስታወቀው፡፡
ይሁን እንጂ አምና ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ይፍረስ ሲባል ከተፈጠረው ቅሬታ በላይ የልዩ ኃይል መልሶ መደራጀት ጉዳይ በአማራ ክልል ተቃውሞና ቁጣ መቀስቀሱ እየታየ ነው፡፡ መንግሥት የአማራ ልዩ ኃይልን ሆን ብሎ ለማፍረስና አማራ ክልልን ለማዳከም የፈጠረው ሴራ ነው ያሉ ወገኖች ዕርምጃውን ክፉኛ እየተቃወሙት ነው፡፡ በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች ደግሞ ትጥቅ አንፈታም ያሉ የልዩ ኃይል አባላት ከመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ማድረጋቸው እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ተቃውሞና አለመረጋጋት ደግሞ ተባብሶ ሌላ ቀውስ እንዳይፈጥር ሥጋት ፈጥሯል፡፡
የተለያዩ ክልሎች በበኩላቸው ዕርምጃውን ተቀብለው ተፈጻሚ ማድረጋቸውን ይፋ እያደረጉ ነው፡፡ ሰኞ ዕለት የሶማሌ ክልል የዛሬ 16 ዓመት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሠረተውን የልዩ ኃይል መዋቅር መልሶ የማደራጀቱን ውሳኔ ተቀብሎ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል፡፡ አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን ጨምሮ ሌሎች ክልሎች ተመሳሳይ ዕርምጃ እየወሰዱ መሆኑን መግለጫ በማውጣት ላይ ናቸው፡፡
የአማራ ክልልም ቢሆን ውሳኔውን የተቀበለውና ከሁሉም ክልሎች ጋር ተስማምቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግፎ ያፀደቀው ውሳኔ መሆኑን ይፋ ቢያደርግም፣ የክልሉን ልዩ ኃይል መልሶ የማደራጀቱ እንቅስቃሴ ግን ከባድ ተቃውሞ እንደገጠመው እየታየ ነው፡፡ ጉዳዩን የተቃወሙ ወገኖች የልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት ዕርምጃው ቢባልም፣ መዋቅሩን ፈጽሞ የማፍረስና አማራ ክልልን ጠባቂ የማሳጣት ነው ሲሉ እየተቹት ነው፡፡
የፕሪቶሪያው ስምምነት አካል ባለመሆኑ ውሳኔውን አንቀበለውም ያሉ ወገኖች በርካታ ናቸው፡፡ መንግሥት በጓዳ በር በኩል የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን አፍርሶ የአማራ ክልል መሬቶችን ለሕወሓት አሳልፎ ለመስጠት ከአይኤምኤፍና ከአሜሪካ ጋር ተሻርኮ ጉዳዩን ለፖለቲካ አሻጥር ማስፈጸሚያ እየተጠቀመበት ነው የሚል ከረር ያለ ወቀሳ የሚያቀርቡ ወገኖችም በርክተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱ ግን ዕርምጃውን በተመለከተ የተሳሳተና ሆን ተብሎ የሐሰት መረጃ በመሠራጨቱ የተዛባ ግንዛቤ በመፈጠሩ እንጂ፣ ውሳኔው አማራ ክልልንም ሆነ ኢትዮጵያን እንደ አገር የሚጠቅም ነው እያሉት ይገኛል፡፡ ይህ ጉዳይ የፈጠረው አለመግባባት የበለጠ ተካሮ ከባድ አደጋ እንዳይፈጠር የሚሉ ወገኖች ግን ጉዳዩ በሰከነ መንገድና በጥንቃቄ እንዲያዝ እየመከሩ ነው፡፡
በኢትዮጵያ አንድ ወጥ የፀጥታ ኃይል መደራጀትን ሲደግፉ የቆዩ ወገኖች በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር ተቀምጦ በመነጋገርና መተማመንን በመፍጠር እንዲፈታ እየጠየቁ ነው፡፡ አብንና ኢዜማ ፓርቲዎችን ጨምሮ ጉዳዩ የፈጠረው አለመረጋጋት ያሠጋናል ያሉ ወገኖች የተሻለ የሚሉትን መንገድ በመጠቆም ላይ ናቸው፡፡
ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ ከእስር ከተፈታ በኋላ በሰጠው የመጀመሪያ ቃለ መጠይቅ ላይ፣ ‹‹የታጠቀ ኃይልን የፌደራል መንግሥትና የክልል መስተዳድር ተረባርበው ትጥቅ ሊያስፈቱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ትልቁ ችግር የጠብመንጃ ብቻ አይመስለኝም፡፡ መሣሪያን ማስፈታት ቀላል ነው፡፡ አዕምሮን ከጠብመንጃ አስተሳሰብ ማላቀቅ ግን ከባድ ነው፡፡ በአገራችን በከፍተኛ ሁኔታ የጦረኝነት አመለካከት በሰፊው ተፈጥሯል፡፡ ይህን መቀየር ነው ትልቁ የቤት ሥራ፤›› ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡
ጃዋር በዚህ ቃለ መጠይቁ በአንድ አገር አንድ ወጥ የሆነ የታጠቀ ኃይል ብቻ መኖር አለበት የሚለውን መርህ እንደሚቀበል ተናግሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በጦርነቱ ወቅት ሁሉም እንዲዘምት ጥሪ መቅረቡንና የቻለም ከጠላት መሣሪያ ነጥቆ እንዲታጠቅ መፈቀዱን ያስረዳል፡፡ ይህንን ራሱ መንግሥት የሰጠውን አዋጅ ተከትሎ ብዙ የታጠቀ ኃይል መፈጠሩን ያስታወሰው ጃዋር፣ ከጦርነቱ በኋላ የታጠቀውን ኃይል በአንዴ ትጥቅ ካልፈታ ብሎ የአጭር ጊዜ ዕቅድን የተከተለ ዕርምጃ መውሰዱ አደገኛ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል ተናግሮም ነበር፡፡ በራሱ ዕይታ የተሻለውና አዋጪው መንገድ የረዥም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ ሰዎችን ትጥቃቸውን ማስፈታት፣ ከዚያም ባለፈ ከጦረኝነት መንፈስ አላቆ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሱ የተሻለው መንገድ መሆኑንም መክሮ ነበር፡፡