ግብርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከሚያደርጉ ዘርፎች አውራው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ዘርፍ 80 ከመቶ የሚሆነውንና ከፍተኛ ድርሻ ያለውን የሰው ኃይል የያዘና የአገሪቱን አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት (ጂዲፒ) 33 በመቶ የሚሸፍንም ነው፡፡
ከ75 እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት መነሻ ይኼው ግብርና በመሆኑ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ከፍተኛውን ሚና በመጫወት በጉልህ የሚነሳ ነው፡፡
በግብርና ዘርፍ ውስጥ ደግሞ በተለይም የሰብል ልማት ግብርና ለአጠቃላይ ጂዲፒ (GDP)ው ከሚያበረክተው ውስጥ ከ68 በመቶ ያላነሰውን በመያዝም ሆነ የውጭ ምንዛሪ በማመንጨት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ የሆኑት መለስ መኮንን (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡
እንደ መለስ ገለጻ (ዶ/ር)፣ ከሰብል ልማቱ ደግሞ ከፍተኛ የሆነውን ድርሻ የሚሸፍኑትና አስተዋፅኦ የሚያደርጉት የቅባት እህሎች ናቸው፡፡ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ሱፍ፣ ኦቾሎኒ የመሳሰሉት ለአገሪቱ ከፍተኛ አቅም ከመሆን ውጪ ከፍተኛ አበርክቶት ያላቸው ምርቶች ናቸው፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን አገሪቱ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ መጠን ያለውን የምግብ ዘይት ከውጭ የምታስገባ አገር ናት፡፡ ይህ ደግሞ ሊሆን የቻለው በተለይም በቅባት እህሎች ዝቅተኛ የሆነ ምርትና ምርማነት በመኖሩ፣ በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ እጥረት በመኖሩ፣ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች በሚፈለገው ልክ የተሟላ ባለመሆኑ፣ እንዲሁም የገበያ መረጃ ተደራሽትና መሠረተ ልማት ውስንነትና እጥረት በመኖሩ ምክንያት እንደሆነ ይገለጻል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ባዘጋጀው የአሥር ዓመታት ዕቅድ ውስጥ በትኩረት ሊሠራባቸው የሚገቡ ተብለው ከተለዩ አሥር ኢንሼቲቮች አንዱ የቅባት ሰብል ኢንሼቲቭ የተባለው ሲሆን፣ ሚኒስቴሩም በዕቅዱ ላይ በ2025 ዓ.ም. 25 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የምግብ ዘይት ፍላጎት ለማሟላት በሰሊጥ፣ በአኩሪ አተር፣ በሱፍና በኦቾሎኒ ላይ መንግሥትና ሌሎች የልማት አጋሮች፣ እንዲሁም ባለሀብቶች ርብርብ አድርገው ለማሳካት ግብ ጥሏል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በዋናነት በአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሌሎች አካባቢዎች የአኩሪ አተር ምርትና ምርታማት እየሰፋ መምጣቱን የሚገልጹት መለስ (ዶ/ር)፣ በቀጣይም ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ እንዲሁም ተጨማሪ ለቅባት ሰብል ምቹ መሬት ባላቸው ክልሎች ላይ ተጠናክሮ እየሰፋ የሚሄድ ይሆናል፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ከጀምሩ ያጋጠመ ተግዳሮት አለ፡፡ ይህም የገበያ ትስስር ነው፡፡ የገበያ ትስስሩና ሥርዓቱ መነጋጋርና መፍትሔ ማበጀትን ይሻል፡፡
በቅባት እህሎች የእሴት ሰንሰለት ሒደት ላይ፣ አዎንታዊ ሁኔታና የገጠሙ ተግዳሮቶችን ሁሉም ባለድርሻ አካል እንደ ድርሻው መግባባት ላይ መድረስ ያለበት ሲሆን፣ በሌላ በኩል በቅባት እህል አምራቾችና እሴት ጨማሪ አካላት ያሏቸው ተግዳሮቶች መለየት ያስፈልጋል፡፡
ሚያዚያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል ግብርና ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽ ኢንስቲትዩት፣ እንዲሁም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ብሔራዊ የቅባት እህሎች የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ሲያካሂዱ የዘርፉ አሁናዊ ውጤቶችና ተግዳሮች በስፋት ተዳሰዋል፡፡
ከአማራ ክልል መተማ የመጡትና የቅባት ሰብሎችን እንደሚያመርቱ የሚናገሩት አቶ ምሕረት አማረ፣ በተለይም ከቅባት እህሎች ጋር ተያይዞ በአምራቹና ኤክስፖርተሩ ወይም አቀናባሪ መካከል በተለይም ከዋጋ ጋር ተያይዞ ስላለው ክፍተት ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት አምራቹ መነሻ የሚያደርገው ወቅታዊ ዋጋ መሆኑ ነው፡፡
ለአብነትም የአኩሪ አተር ዋጋ በማንሳት ምርቱ ሲመረት ሦስት ነገሮችን ይይዛል (ታሳቢ ያደርጋል) ይላሉ የማቴሪያል፣ የሰው ኃይልና የአገልግሎት ወጪዎች ናቸው፡፡ ይህንን ሥሌት ይዞ ምርቱ ቢመረትም አሁን ላይ በመሬት ላይ ያለ ዋጋ ከወጪው ያነሰ (ያሽቆለቆለ) በመሆኑ፣ እነዚህ ነገሮች እንዴት መጣጣም አለባቸው የሚሉትን መመለስ ያስፈልጋል፡፡
አምራቹን ማበረታታት ከተፈለገ መነሻ የመሸጫ ዋጋ ላይ ያሉ ችግሮች መታየት ይገባቸዋል ባይ ናቸው፡፡ በየመጋዘኑ ከከርሞ ጀምሮ የተከማቹ የቅባት እህሎች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ምሕረት፣ ‹‹በተለይም ሰፊ የሆነ የአኩሪ አተር ክምችት እንዳለ በማንሳት፣ በአንፃሩ በወቅታዊ ዋጋ እየተሻለ ወደመጣው የሰሊጥ ምርት፣ አኩሪ አተር በመተው አምራቹ ሊገባ ይችላል፡፡ ስለሆነም ምርት ተመርቶ ዋጋ በሚያሽቆለቁልበት ጊዜ እንዴት ተደርጎ ነው ሊጣጣም የሚችለው? የሚለውን የሚመለከተው የመንግሥት አካል መፍትሔ መስጠት አለበት፡፡
‹‹ቢያንስ ምርቱን ሸጠን ማምረት ይገባል፤›› የሚሉት አቶ ምሕረት፣ ካልሆነ አምራቹ በቀጣይ ወደ ሌሎች ምርቶች እንደሚገባ፣ ለዚህ የአኩሪ አተርና የጥጥ ዋጋ መውረድ በምሳሌነት በመጥቀስ ጉዳዩ ዕልባት የሚፈልግ መሆኑን ያስረዳል፡፡
ከጎፋ ዞን እንደመጣ የሚናገረው አቶ ካሳዬ በበኩሉ፣ ሰሊጥ በክላስተር እንደሚያመርት የሚያስረዳ ሲሆን፣ ነገር ግን ምርቱን ማምረቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሚገጥሙትን ስድስት ዓበይት ነገሮች ያነሳል፡፡
አንደኛ የሚመረተው ምርት ወደታሰበው ገበያ እንዳይደርስ የመሠረተ ልማት በተለይም የመንገድ ችግር አለ፡፡ በሌላ በኩል በቂ የደኅንነት ጥበቃ ከልዩ ኃይልም ሆነ ሌላ የፀጥታ አካል ባለመደረጉ ‹‹ዘላኖች›› ገብተው ዘረፋ ይፈጽማል፡፡
ሦስተኛው ማነቆ ተደርጎ የተነሳው ጉዳይ አቶ ካሳዬና መሰል አምራቾች ያመረቱትን ምርት ለማከማቸት የሚያገለግል መጋዘን የለም፡፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ደላሎች ገበያው ላይ ተንሰራፍው ገብተው ዋጋ እንዲወርድና እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ከቡቃያ እስከ ምርት ድረስ ተባይ የተመረተውን ምርት የሚያበላሽ መሆኑን ይገልጻል፡፡ አቶ ካሳዬ እንደሚገልጹት፣ የመስኖ ግብዓቶች ችግር፣ በተለይም ፓምፕ አለመኖር የውኃ ሀብት እያለ ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚያደርግ መሰናክል ነው፡፡
በሌላ በኩል በውይይቱ ላይ ከኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የመጡት ተወካይ፣ በተለይም ኅብረት ሥራ ማኅበራት አንዱ የግብይት ተዋናይ እንደመሆናቸው የሚገጥማቸውን ጉዳይ፣ አምና የአኩሪ አተር ዋጋ ከፍ ብሎ ስለነበር የተመረተውን ምርት ለመሰብሰብ ተፈትነው እንደነበርና በአንፃሩ ምርቱን ባልሰበሰቡበት ወቅት ደግሞ ዋጋ መውረዱን ይገልጻሉ፡፡
ኅብረት ሥራ ማኅበራት ቀጥታ ከምርት ገበያ ውጪ አገር ውስጥ ባለ የግብይት ትስስር መገበያያት እንዳይችሉ በሕግ የተከለከለ መሆናቸው የሚያነሱት ተወካዪ ወይ ኤክስፖርት ማድረግ አለባቸው፣ ካልሆነ ወደ ምርት ገበያ ማስገባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ችግር ቢፈታ ማኅበረቱ ከኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ከሌሎች ላኪዎች ጋር ትስስር ፈጥረው ውጤት ማግኘት ይቻላል፡፡
ምርት ለመሰብሰብ ከፍተኛ ፋይናንስ ስለሚጠይቅ ማኅበራት ዘወትር ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች ፋይናንስ ዋነኛው ነው፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ምርት ለመሰብሰብም ሆነ ለማከማቸት የፀጥታ ችግሮች ሌላው ተግዳሮቶች በመሆናቸው እስከነ አካቴው ምርት ከመሰብሰብ የተቆጠቡም የኅብረት ሥራ ማኅበራት እንዳሉ ተገልጿል፡፡
አቶ ሙሉ ዓለም የተባሉት ባለሀብት እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ፣ የቅባት እህሎችን የሚያቀነባብር የአግሮ ኢንዱስትሪ በባህሪው ከፍ ያለ ሥራ ማስኬጃ ይጠይቃል፡፡ ወደ ሥራ የገቡ አግሮ ፕሮሰሲንግ ድርጅቶች የሥራ ማስኬጃ የሚሆን የፋይናንስ ድጋፍ ካላገኙ ሁነኛ መፍትሔ አይመጣም፡፡ በሌላ በኩል በቀጣይም ወደ እዚህ ሥራ የሚገቡ ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸው ተለክቶ 70 በመቶ መንግሥት በልዩ ሁኔታ አይቶ የሥራ ማስኬጃ ካልመደበ ወደ ፊትም ምርቱ ቢያድግ ውጤት እንደማይመጣ አቶ ሙሉዓለም ያስረዳሉ፡፡
የውይይት መድረኩን የመሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደሚገልጹት፣ ስለቅባት እህል ሲነገር በዓለም ደረጃ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሸፍነውና ለብዙ ኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት ሊያገለግል የሚችለው የፓልም ዛፍ በማልማት ረገድ ኢትዮጵያ ቀላል የማይባል አቅም አላት፡፡
ምንም እንኳን እንደ ሰሊጥ ዓይነት ያሉ የቅባት እህሎችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ኢትዮጵያ ትልቅ ድርሻ ያላት ቢሆንም፣ በአንፃሩ ያለቀለት (የተቀነባበረ) ምርት በማስገባት ረገድ በየዓመቱ በሚሊዮን ሊትሮች የሚቆጠር የምግብ ዘይት ወደ አገር ውስጥ ታስገባለች ያሉት የኢንዱስትሪ ሚንስትሩ፣ በመሆኑም እነዚህን ሁኔታዎች ማስታረቅ እንደሚያስፈልግ ይነገራል፡፡
አቶ መላኩ እንደሚሉት በማቀነባበር ሥራ ላይ የሚገኙ ባለሀብቶች የማቀነባበር ሥራውን ብቻ ሳይሆን፣ ቢያንስ እስከ “ብሬክኢቨን” ድረስ ያለው ግብይት በራሳቸው እንዴት ሊያመርቱ እንደሚችሉ ማሰብና መነጋገር ያስፈልጋል፡፡
አርሶ አደሩ በስፋት ሲያመርት ለገበያ ብሎ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ መላኩ፣ ይህንን የሚቀበሉ በቂ ኢንዱስትሪዎች ሊኖሩ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ከተቋቋሙ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጪ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ትልልቅ የሚባሉ ፓልምን የሚጨምቁ (ድፍድፍ ዘይት የሚጨምቁ) በሌላ በኩል አኩሪ አተርና ሌሎች የቅባት እህሎችን የሚጠቀሙ የዘይት ፋብሪካዎች በስፋት በሁሉም አካባቢዎች እየተስፋፉ መምጣታቸው፣ ይህም ለአምራቹ የሚኖረው ፋይዳ በጣም ከፍተኛ ነው የሚሉት ሚኒስትሩ፣ ይህም የገበያ ዕድል በመፍጠር ረገድ ነው፡፡
የግብይት ሥርዓቱን ለማሻሻል በምርት ገበያ በኩል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በማንሳት የመጋዘን ተደራሽነትን በማስፋት ገበያው ለማስፋፋት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ጥሩነቱ ቢነሳም፣ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት ካልተጠናከረ በመሀል የሚገባው ደላላ የዘርፉ ተዋንያን ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም የሚያሳጣ ነው፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ (ዶ/ር) በማጠቃለያ ሐሳባቸው፣ በባለፉት ሦስት ዓመታት የተሞከረው የአኩሪ አተር ምርት በዚህ ወቅት ያለበት ዓብይ ችግር የገበያ ችግር መሆኑን አስምረውበታል፡፡
አኩሪ አተርን ጨምሮ በሌሎች የግብርና ምርቶች ውጤቶች ላይ ያለው የግብይት ጉዳይ የተረጋጋ ግብይትና ተገማች የሆነ ሊሆን ይገባል፡፡ ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ዩኒየኖች የተመረተ ምርትን ለመሰብሰብ፣ ለማቀናጀት በገበያው ላይ የሚሰማሩ ተዋንያን እንደመሆናቸው እነሱን በተለያየ መንገድ ማለትም በፖሊሲና በሌሎች ድጋፎች ሊያገኙ እንደሚገባ መለስ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡
አቶ መላኩ በስተመጨረሻ ላይ እንዳስታወቁት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከዓመት በላይ የቆየ ምርት አለ፡፡ ለአብነት ያህል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 40 ሺሕ ኩንታል የተከማቸ የቅባት እህል አለ፡፡ በሌላ በኩል ይህንን ጥሬ ዕቃ ለመጠቀም የሚችሉ የተለያዩ ኢንዱስትዎች አሉ፡፡ ይህንን የማስታረቅ ሥራ ይቀራል፡፡
የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት በመንግሥት የተመደበለትን ገንዘብ በመጠቀም የተከማቹት ምርቶች ግዥ መጀመር አለባቸው፡፡ ሆኖም ይህ ሲሆን ግዥውን ከሚያደርጉ ፋብሪካዎች ጋር ውል በማሰር ሊሆን ይገባል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) የተገኘውን ገንዘብ ለጥጥና ለቅባት እህል አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲዳረስ የግብርና ሚኒስቴርና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል፡፡
የንግድ ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤክስፖርት ሳያደርጉ ሲቀሩ ለፋብሪካዎች የሚያቀርቡበት አሠራር ሊያበጅ ይገባዋል፡፡
የምርት ዕድገት እየጨመረ በሄደ ቁጥር ዘመናዊ የሆኑ የመጋዘንና የምርት ማከማቻ ጎተራ ግንባታ ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ በተለይም ብዙ ምርት በሚመረትባቸው አካባቢዎች በልዩ ሁኔታ ላይ የጎተራ ግንባታ ጉዳዩን ግብርና ሚኒስቴርና ተጠሪ አካላት ሊያስቡ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ከሎጂስቲክስ ጋር ተያይዞ የምርት ክምችቱን ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር እስከ ኮንቮይ በሚደርስ ተሽከርካሪ ለማውጣት በዘመቻ ጥረት ይደረጋል ተብሏል፡፡