Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሆድና የሆድ ነገር

ሆድና የሆድ ነገር

ቀን:

(ክፍል ሰባት)

በጀማል ሙሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር)

የእነ እንትናዬ ቤት – አለ ወይ ፈረሰ

እበላበት ነበር – እግሬ እንዳደረሰ፡፡

የሚያበላና የሚያጠጣን ሰው፣ ሁሉም ይወደዋል፡፡ “የሚጠላው ሰው የለም” ማለትም ይቻላል በሀብቱና በቸርነቱ የተመቀኘ ሰው ካልሆነ በስተቀር፡፡ የዚህ አይነቱ ሰው ከሞተ ደግሞ ሙገሳውና ውደሳው እስከ ሙሾ ሊደርስ ይችላል፡፡ ከላይ የቀረበው ግጥም ለዚህ ጥሩ አብነት ነው፡፡

ግጥሙ የያዘው መልእክት ጠንካራ ነው ሙሾ አውራጅ ወደ ሟች ቤት ጎራ ባለ ወይም ባለች ቁጥር የምግብ መስተንግዶ ያለማሰለስ እንደሚደረግለት ወይም እንደሚደረግላት ብቻ ሳይሆን፣ ሟችም ሆነ ቤተሰቡ በደስታ የሚያስተናግዱ መሆናቸውን ቢያንስ በተዛዋሪ ይጠቁማል፡፡ ከቤተሰቡ መሀል አንዱ ፊቱን ቢያጠቁር ማን እዚያ ድርሽ ይል ነበር? “ከፍትፍቱ ፊቱ” የሚለውን አነጋገር አትርሱት እንጂ!

ሁለተኛው ነጥብ ግጥሙ የተገጠመበት ወይም የቀረበበት ዓውድ ነው ሲያበላና ሲያጠጣ የሚያልቅብኝ የማይመስለው ሰው በሞተ ሰዓት ወይም ጊዜ፡፡ አወዳሽ የሰውን ውለታ ወይም በቀጥተኛ አነጋገር ለሆዱ የተደረገለትን ውለታ የማይረሳ መሆኑ ያስመሠግነዋል፡፡ ሆኖም አሳዛኙ ነገር፣ የውደሳውን ቧንቧ የከፈተው፣ የአድናቆቱን ውኃ ያንቧቧው የሰውዬውን ዕለተ ሞት ጠብቆ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡

እሱም ሆነ ሌሎች ሙሾ አውራጆች የሚያወርዱት ሙሾ፣ በሙሾው ውስጥ ያለው ውዳሴ፣ ሙገሳ፣ እነሱም ሆኑ ሌሎች ለቀስተኞች የሚያፈሱት እንባ፣ ደረት መደቃት… ለሟች “አምስት ሳንቲም” በማይጠቅምበት ሰዓት ነው፡፡ ሟች የሚያየውም ሆነ የሚሰማው ነገር የለም፡፡ ይህ ሁሉ ይቅርና በስሙ ከመጠራት፣ “አስክሬን” ወይም “ሬሳ” ወደ ሚል የሙታን የወል መጠሪያ ስም ከተሸጋገረ ቆየ ነፍሱ ከወጣችበት ቅፅበት አንስቶ፡፡

ግን ምን ዓይነት የንፉግነት ባህል ነው ያለን? ንፉግ የሆንነው ደግሞ ገንዘብ፣ ዕቃ ወይም ምግብ ለመስጠት አይደለም? እሱማ በስንት ጣዕሙ፡፡ ንፉግ የሆንነው ያበላንንና ያጠጣንን ሰው ስንኝ ቋጥረን ለማመሥገን ነው፡፡ ስንራብና ስንጠማ ብቻ ሳይሆን፣ ባለፍን-ባገደምን ቁጥር ጭምር ሲያበላንና ሲያጠጣን የነበረን ሰው በግጥም ለማሞገስ ሞተ ዕለቱን የምንጠብቅ ምን ዓይነት ንፉጎች ብንሆን ነው? አስክሬን አወዳሽነትን ማን ይሆን ያስተማረን? ከዚህ ባህል ጋር በማስቲሽ ተጣብቀብ የቀረነውስ ለምን ይሆን?

አንድ ታዋቂ ሰው የሞተ ጊዜ፣ የሠራቸውን መልካም ነገሮችና ስኬቶቹን አግበስብሶ ፕሮግራም በመሥራት የሚያጥለቀልቁን የአገራችን ሚዲያዎችስ፣ የዚህ ሙት አወዳሽ ባህል ሰለባዎች መሆናቸው ያጠያይቅ ይሆን? እነሱ የሚነግሩንም ሆነ የሚያስተምሩን፣ የሚያደነቁሩንም ሆነ የሚቦተልኩልን (የወሎ ገበሬን አነጋገር “ተውሼ” ነው) የተፅዕኖው ምንጭ፣ ማርስ ላይ ሳይሆን መሬት ላይ ያለው እውነታ አይደለምን? መሬት ላይ ያለነው ደግሞ እኛ ኢትዮጵያዊያን አይደለንምን?

ሌላው ቢያንስ በተዛዋሪ በዚህ ግጥም ውስጥ የሚንፀባረቀው አሉታዊ ሐሳብ ወይም በቀጥታ አነጋገር ያወዳሽ ደካማ ጎን፣ ያለስስት የሚያበላ ሰው ሞትን ከቤት መፍረስ ጋር የማመሳሰሉ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ለጋስ የሆነ ሰው ከሞተ፣ የእሱ ሞት ለተለጋሹ ከሰውዬው ቤት መፍረስ ጋር እኩል መስሎ ሊታየው ለምን ቻለ? የአንድ ሰው ቤት የመኖሩ ዋናው መገለጫ፣ ሌሎች ሰዎችን ማብላትና ማጠጣቱ ሆኖ ለምን ቀረበ? ማብላት፣ ማጠጣቱ ከቀረ፣ ያ ቤት እንደፈረሰ ለምን ይቆጠራል? ይኼ “ሆድ” የተባለ ነገር፣ የዕይታችንን “ሌንስ” በቅርብ ሊገኝ የሚችልን ነገር (ምግብን) እንጂ፣ ራቅ ያለውን (ያለብንን ውለታ) እና ለሰውዬው ሊኖረን የሚገባንን መልካም ምኞት እንዳናይ የማድረግ ኃይል ጭምር የለውም ማለት ይቻል ይሆን?

በሌላ በኩል መልካም ለሠራ ሰው ሙገሳውንና ውደሳውን፣ ውዴታንና ፍቅርን የማዝነቡ ነገር ግማሽ ያህሉ እንኳን በሕይወት እያለ ቢሆንስ ኖሮ ብለን እስቲ እናስብ? በሥራው የበለጠ እርካታ ይሰማው፣ ለበለጠ መልካም ተግባርም ይበረታታ፣ ሌሎችም የእሱን አርዓያነት ለመከተል ይነሳሱ ነበር፡፡ ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬውና ማኅበራዊ ግንኙነቱ ይበልጥ የበረታ ከመሆንም አልፎ፣ በሕይወት ዘመኑ ይበልጥ ስኬታማ ለመሆን ትልቅ ስንቅ ሊሆነው ይችል ነበር፡፡ ማን ያውቃል ከራስ አልፎ ለሌሎች፣ ከሌሎች አልፎ ለአገር የሚተርፍ ቁም ነገር ትቶልን እስከ መሄድም ሊደረስ የሚችልበት ዕድልም ሊፈጠር ይችላል፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው ኗሪን ወቃሽ፣ ሟችን አወዳሽ ሆነን አርፈነዋል? ከሁሉ የከፋው ነገር ደግሞ ሆድ ዋናው ሚዛን ሆኖ ሲመጣ ነው፡፡

እርግጥ ነው፣ የሰው ልጅም ሆነ ማንኛውም ሕይወት ያለው እንስሳ ያለ ምግብ ውሎ ማደር አይችልም፣ ውሎ ቢያድር አይሰነብትም፡፡ ከአየርና ከውኃ (ውኃም ከምግብነት መመደቡ እንደ ተጠበቀ ሆኖ) ቀጥሎ ምግብ የህልውናችን መሠረት ነው፡፡ በእኛ ባህልና ባህሉ በገነባው አስተሳሰብና አመላካከት ውስጥ፣ ከምግብና ከምግብ ጋር የተያያዙ የሆድ ትርክቶች ሜዳውን ተቆጣጥረውታል፡፡ ይኼ አንድ ነገር ነው፡፡

ሁለተኛ፣ ሰውን ማብላት የቸርነት ብቻ ሳይሆን የደግነት፣ የቁም ነገረኛነት፣ የታላቅነት፣ ወዘተ. መገለጫ ተደርጎ እስከ መቆጠር ደርሷል ከዚህ ውጪ ያለው መልካም ተግባር ሁሉ በዜሮ ሊባዛ ትንሽ እስከሚቀረው፡፡

ከፍ ሲል በቀረበው ግጥም ውስጥ፣ ያለስስት የሚያበላ ሰው ይሞገሳል፣ ይሞካሻል፡፡ ሞቱም ከቤቱ መፍረስ ይቆጠርለታል፡፡ በዚህ ተቃራኒ የሆነ ሰው ከሞተስ ማለትም ንፉግ የሆነ፣ ሰው ማብላትን ድህነትን ከመጥራት የሚቆጥር? ችግር የለም ይገጠምለታል ወይም ተገጥሞለታል፡፡ በሆድ ጨክኖ ማን ይምረዋል? ወትሮስ ቢሆን “የሆድ ነገር፣ ሆድ ይቆርጣል” አይደል የሚባል?

ከዚህ አንፃር እስቲ አንድ ግጥም ለአብነት እንጥቀስ፡-

ቶሎ ቅበሩልኝ – ቶሎ ልሂድ ቤቴን

ጋግሬ ልብላበት – እህል መድኃኒቴን፡፡

ገጣሚዋ ሴት እንደሆነች መገመት ይቻላል፡፡ እንጀራ የሚጋግር ወንድ ድሮ ይቅርና አሁን “አለ” ለማለት ያስቸግራል፡፡ በዘመናችን “ጎበዝ” የተባለ ወንድ ወጥ ቢሠራ ነው፡፡ አብዛኛው ወጥ የሚሠራው ደግሞ ሚስቱን በሥራ ለማገዝ ፈልጎ ሳይሆን፣ እንጀራ ገዝቶ ስለሚበላ ነው – ላጤ ስለሆነ፣ የኑሮ ውድነቱ ማንቁርቱን አንቆ ስለሚይዘው ጭምር፡፡

ወደ ዋና ጉዳያችን እንመለስ፡- ሴትየዋ ምን አለች? ለምንስ እንደዚህ አለች? ከመቃብር ቦታ ወደ ቤቷ ለመመለስ በጣም ቸኩላለች፡፡ ምክንያቷ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ ርቧታልና እንጀራ፣ ቂጣ ወይም ዳቦ ጋግራ መብላት ፈልጋለች፡፡ ትናንት ቆሞ ይኼድ የነበረ ሰው፣ ዛሬ የማይንቀሳቀስ በድን ሆኖ ከቃሬዛ ላይ ተኝቶ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ በሐዘን ጥርስ አንጀታቸው እየተበላ፣ ሴትየዋ ርሃቧን ለመታገስ አለመቻሏ ግን አስገራሚ ነው፡፡ እርግጥ ነው የሆድ ነገር ነውና ከቀብር በኋላ መብላት አይቀርም፡፡ ወይም ይህን ሐሳብ በዚሁ በፈረደበት የሆድ ትርክት ቋንቋ እናስቀምጠው – “‘ዋ!’ ብሎ ጉርስ” አይቀርም፡፡ እሷ ግን እስከዚያ ጊዜ መታገስ አልቻለችም፡፡

በዚህ ንፉግ ሟች ላይ ያላት ጥላቻ ልክ ከማለፉ የተነሳ፣ የቀብሩን ሥነ ሥርዓት እንደ አላስፈላጊና የማይረባ ነገር ቆጠረችው፡፡ በተቃራኒው ለርሃቧ የምትሰጠውን ምላሽ ማለትም ከጋገረች በኋላ የምትበላውን ምግብ የመድኃኒትነትን ደረጃ እስከሚያገኝ ሰቀለችው፡፡ ምግብ ለእሷ እንደ መድኃኒት ሳይሆን፣ ራሱ መድኃኒት ሆነ ሰዓቱ ሊዛነፍበት የማይገባ ጭምር፡፡

የምድር ላይ ጉዞውን ጨርሶ፣ መሬት ልትሰለቅጠው አፏን ከፍታ ለምትጠብቀው ሰው ቅንጣት አለማዘን ምን ይባላል? የሆድ ነገር የጨካኝም ጨካኝ የሚያደርገው እስከዚህ ድረስ ነው ማለት ነው? አዎ ሀቁ ይኼው ነው፡፡

ምን አለፋችሁ? የሆድ ጥሪን መመለስ የሕይወት ግብን የማሳካት ትልቁ ወይም የመጨረሻው ደረጃ በመሰለ መንገድ ነው የሆድ ነገር ትርክቱን የተቆጣጠረው፡፡ በምግብ ራሥን መቻል ሳይሆን፣ ሆድን መሙላት በራሱ የሐበሻ ራዕይ እስከሚመስል ነው የተተረተው፣ የተተረከው፣ የተሞሸው (ሙሾ የተወረደው)፣ የተዘፈነው፣ የተንጎረጎረው፣ የተቀነቀነው…

እስቲ ቀጥሎ ያለውን ግጥም ልብ ብላችሁ አንብቡት፡-

አሥር ሳንቲም ያለው፣ አይባልም ደሃ

አምስቷን ለቆሎ፣ አምስቷን ለውኃ፡፡

እርግጥ ነው፣ ግጥሙ ከዘመነ ግሽበት እጅግ ወደ ኋላ በሄደ ዘመን ውስጥ የተቀኘ ነው፡፡ በዚያን ወቅት በአምስት ሳንቲም የሚገዛ ቆሎ ለምሳ ወይም ለእራት ወይም ደግሞ ለምሳና ለእራት በቂ የሚሆን ቆሎ ለመግዛት የሚያስችል ነበር፡፡ ግማሽ ኪሎ ቆሎ እየተሸጠ ያለበትን የአሁኑን ዘመነ ግሽበት ከጭንቅላታችሁ አውጡት፡፡ በእኔ ዕድሜ ያሉ አንዳንድ ሰዎች፣ አባታቸው በአምስት ወይም ስድስት ብር በግ ገዝቶ የነበረ መሆኑን ሊነግሯችሁ ይችላሉ፡፡ ወይም ደግሞ በጉን በስድስት ብር ገዝቶ፣ ቆዳውን በአምስት ብር በመሸጥ፣ የአንድ በግ ሥጋ በአንድ ብር መገዛቱን “ሊያበስሯችሁ” ይችላሉ፡፡

ወደ ዋናው ነጥባችን ስንመለስ፡- ምናልባት በዚያን ዘመን ‹‹አሥር ሳንቲም ለማግኘት፣ አሥር ዓይነት ላብ ማውጣት ግድ ነበረ፤›› ካልተባለ በስተቀር፣ ድህነትም፣ ሀብታምነትም ቅልል ተደርገው ነው የታዩት፡፡ እንደ ግጥሙ ሐሳብ ከሆነ፣ በሁለቱ መሀል ያለው ድንበር እጅግ የሳሳ ነው፡፡ አንድ ሰው አሥር ሳንቲም ካለው ሀብታም ነው፡፡ ቆሎና ውኃ ገዝቶ በመመገብ ሆዱን መሙላት ይችላል፡፡ ሆዱ ከሞላ ከሀብታም ይመደባል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የመኖር ራዕዩን አሳካ ማለት ነው፡፡

አሥር ሳንቲም ከሌለው ደግሞ እሱ ደሃ ነው፡፡ (የደሃ ደሃ፣ ከድህነት ወለል፣ ከድህነት ጣሪያ በላይ፣ በታች ቅብጥርሴ የሚል የምሁራን የቃላት ፈለጣና ትንታኔ እዚህ ቦታ የለውም፡፡) ቆሎም ሆነ ውኃ መግዛት አይችልም፡፡ እናም ይራባል፣ ከተራበ በቃ ደሃ ነው ራዕዩን ማሳካት የተሳነው ደሃ ነው፣ አለቀ! ግጥሙ የሚነግረን ይኼንኑ ነው፡፡

ግለሰቡ አምስት ሳንቲም ብቻ ካለውስ? “ደሃ” እንዳይባል፣ አምስት ሳንቲም አለው፡፡ ሀብታም እንዳይባል፣ አምስት ሳንቲም ጎድሎታል፡፡ ቆሎ ወይም ውኃ መግዛት ይችላል፡፡ ሁለቱንም መግዛት ግን አይችልም፡፡ በረሃብና በጥም ላለመሞት፣ ከሁለት አንዱን የግድ መምረጥ አለበት፡፡ የባሰበትን ብቻ ነው መግዛት የሚችለው ወይ ውኃ ወይ ቆሎ፡፡

ዋናው ነገር “የት ይመደብ ነው?” የሚለው ነው፡፡ ‘መካከለኛ ገቢ ያለው’ ተብሎ ይመደብ እንዳትሉ፡፡ ይህን ካላችሁ፣ ችግሩ የራሳችሁ ነው፡፡ በድህነት ቋንቋ፣ ሀብታምነትንና ድህነትን ደረጃ ሰጥታችሁ መክፈል ያለመቻላችሁ ውጤት ነው፡፡ ሆኖም ምንም እኳን፣ በዘመናችን መካከለኛ ገቢ ያለው ማን እንደ ሆነ ይቅርና የመካከለኛ ገቢን ወርድና ቁመት መንገር ሊያስቸግራችሁ እንደሚችል ብገምት፣ እናንተ ከግጥሙ ባለቤቶች የተሻለ ራዕይ እንዳላችሁ እወስዳለሁ (“እወስዳለሁ” የምትለዋን ቃል የተጠቀምኩት፣ የካድሬ ቋንቋ ጣል ላድርግበት ብዬ ነው)፡፡

ለዚህ መጣጥፍ አንድ ሦስት ግጥሞችን በቴሌግራም በኩል የላከልኝ፣ የሥራ ባልደረባዬ አቶ ሐሰን ዑስማን፣ በአካል እንደተገናኘን፣ እየጻፍኩ ስላሉሀት ስለሆድና ሆድ ነገር ትንሽ አጫወትኩትና ስለላከልኝ ግጥሞች ሐሳብ አብራራልኝ፡፡ በአገራችን የአማርኛ ሥነ ቃል ውስጥ ከምግብ ጋር የተያያዙ እጅግ በርካታ አገላለጾች እንዳሉ አወራን፡፡ አንዳንዶቹ ምግብ ማግኘትን ቀጥታ ግባቸው ያደረጉ ናቸው፣ ምኞታቸውም፣ ራዕያቸውም እሱ ነው ምግብ ማግኘትና ሆድን መሙላት፡፡ ሌሎቹና ብዙዎቹ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ አጀንዳቸው የሚሽከረከረው በእሱ ዙሪያ ነው በምግብና ሆድን በመሙላት ዙሪያ፡፡

ከሐሰን ጋር በነበረን ጨዋታ፣ አንዳንዶቹ ሥነ ቃሎች የሰውን ራዕይ የመገደብ ኃይል እንዳላቸውና ጥቂቶቹ ደግሞ ሆድ አደርነትን ጭምር የሚያበረታቱ እንደ ሆኑ አወራን፡፡ ወዲያውም በ1991 ዓ.ም. አካባቢ በነበሩ ዘፈኞች ውስጥ የሚከተለውን ግጥም መስማቱን ነገረኝ፡-

“እኔስ ማደሬ ነው – እኔስ ማደሬ ነው

ከበላሁ ከጠጣሁ – ሁሉም አገሬ ነው፡፡”

የሐበሻን ባህል ከሆድ ጋር ያስተሳሰረው ገመድ፣ የዘመን ጉዳይ አለመሆኑን ይኼ ግጥም ጥሩ ምስክር ነው፡፡ መልዕክቱም ግልጽ ነው የሆድ ጥያቄ ማለትም መብላትና መጠጣት ከተሟላ ሌላ የሚያሳስብ ነገር የለም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ለሆድ ጥያቄ ተፈላጊውን መልስ መስጠት የቻለ ቦታ ሁሉ ከአገር ይቆጠራል፡፡ የህሊና፣ የእምነት፣ የመንቀሳቀስ፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ነፃነቶች ጥንቅር ብለው ቢቀሩ የራሳቸው ጉዳይ ነው፡፡ ወይም ቢያንስ-ቢያንስ በሌላ ጊዜ ይታሰብባቸው ይሆናል፡፡ ወይም ላይታሰብባቸውም ይችላል…

ይህን ሐሳብ እየጻፍኩ እንዳለሁ አንድ ጉዳይ ወደ አዕምሮዬ ሲሮጥ መጥቶ ትንሽ ረበሸኝ፡፡ ምን መሰላችሁ… ፌስታል አንጠልጥለው የቀይ ባህርን ወይም የሜዲትራንያን ባህርን ለመሻገር የሚኳትኑት የአገሬ ልጆች በዓይኔ ላይ መጡ… “ቁሞ ከመሞት፣ እየሄዱ መሞት” የሚሏት አገላለጻቸው አቃጨለችብኝ፡፡ “ሠርቼ እለወጣለሁ” የሚል ራዕይ ሰንቀው ከአገራቸው ከወጡ በኋላ፣ የሻርክ (የዓሳ)፣ የአዞ፣ የዱር አራዊት፣ የበረሃማው አሸዋ… እራት ሆነው የቀሩት ለጋ ወጣቶች በዓይኔ ላይ ሄዱ… በሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች የተገረፉት፣ ገላቸው በዘይት የተቃጠለው፣ የተደፈሩት… በዓይኔ ላይ ዞሩ…

ከእነዚህ ወጣቶች መካከል ተሳክቶላቸው ባህሮቹን ያቋረጡና ሚጢጢዬም ብትሆን ሥራ ያገኙ ወጣቶች፣

“እኔስ ማደሬ ነው – እኔስ ማደሬ ነው

ከበላሁ ከጠጣሁ – ሁሉም አገሬ ነው፡፡”

የምትለዋን ግጥም በእስክሪብቶ ወረቀት ላይ ጽፈው ከሚኖሩባት ክፍል ግድግዳ ላይ ቢለጥፉ ላይፈረድባቸው ይችላል፡፡ እርግጥ ነው፣ “ከሀብታም ቤት ጥብስ፣ ከደሃ ቤት ጥቅስ አይጠፋም” በማለት፣ በደሃዎች የሚሳለቁ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ደሃዎች፣ ትከሻን የሚያጎብጠውን፣ ወገብ የሚሰብረውን የድህነት ሸክማቸውን በመፅናናት ቀለል ለማድረግ፣ በራሳቸው መንገድ በቀየሱት የሥነ ልቦና የህክምና ሥልት መሳለቅ ጥሩ አይመስለኝም፡፡

የሚያስገርመው ነገር፣ በደሃዎች ጥቅስ የሚሳለቁት ሰዎች ራሳቸው ከሆድ ትርክት ያልወጡ መሆናቸው ነው ጥብስን ነው የሀብት መገለጫ አድርገው ያቀረቡት፡፡ ይኼ በምግብ ራሳችንን ያልቻልን ብቻ ሳይሆን፣ ለዘመናት ከረሃብ ያልተላቀቅን ሕዝቦች ከመሆናችን የተነሳ፣ ሆድና የሆድ ነገር ሁለመናችንን የተቆጣጠረን የመሆኑ ጉዳይ መገለጫው ብዛቱ! (በክፍል ስምንት እንገናኝ – ኢንሻ አሏህ!)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው jemalmohammed99@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...