Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበየመን ሰላም እንደሚያሰፍን ተስፋ የተጣለበት የሁቲና የሳዑዲ ዓረቢያ ውይይት

በየመን ሰላም እንደሚያሰፍን ተስፋ የተጣለበት የሁቲና የሳዑዲ ዓረቢያ ውይይት

ቀን:

የመን የእርስ በርስና የውክልና ጦርነት ውስጥ ከተዘፈቀች ዘጠኝ ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ በየመን ውስጥ ያለው መከፋፈል፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራውና ለመንግስት ይወግናል የሚባለው ጥምር ጦር ጣልቃ መግባት፣ የየመን ዋና ከተማ ሰንዓን ጨምሮ ሰፋፊ ቦታዎችን የተቆጣጠረው የሁቲ ታጣቂዎች በኢራን መደገፋቸው በአገሪቱ ስር የሰደደ ፖለቲካዊና ሰብዓዊ ቀውሶችን አስከትሏል፡፡

ከየመን ሲሶ ያህሉ ሕዝቧ ድህነት ውስጥ የተዘፈቀ ሲሆን፣ ከዓረቡ ዓለም የመጨረሻ ደሃ አገርም ሆናለች፡፡ በአገሪቱ የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስም በዓለም አስከፊ የሚባለው ነው ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ይገልጸዋል፡፡

ተመድ በ2021 ያወጣው ሪፖርት፣ በጦርነቱ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከ370 ሺሕ በላይ ሰዎች መሞታቸውን ያሳያል፡፡ ጦርነቱ ቢዚሁ ከቀጠለ እ.ኤ.አ. በ2030 የሟቾች ቁጥር 1.3 ሚሊዮን ይደርሳል፡፡

ችግሩን ይቀርፋል ያለውን የሰላም ውይይትና ተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተመድ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን በኦማን አግባቢነት የተጀመረው ሳዑዲ አረቢያንና የየመን የሁቲ አባላትን የማወያየት ሥራ ተስፋ ሰጥቷል፡፡

የሳዑዲና የኦማን ልዑካን ቡድኖች በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ በመገኘት አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል ከተቆጣጠሩት የሁቲ ተወካዮች ጋር ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ተወያይተዋል፡፡

በየመን ሰላም ለማስፈን የተጀመረውን ጥረት ያጠናክራል የተባለው የሳዑዲና የኦማን በየመን መገኘት፣ በየመን የነበረውን አልበገር ባይነት የሚያለሳልስና፣ በሳዑዲ መሪነት የተዘጉ የየመን ወደቦች እንዲከፈቱ ዕድል የሚከፍት ነው ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

በየመን የሁቲ ጠቅላይ የፖለቲካ ምክር ቤት የበላይ ኃላፊ መሃዲ አል ማሻት በየመን ሁቲዎችና በሳዑዲ ዓረቢያ የተደረገውን ውይይት አስመልክተው እንዳሉት፣ የመን ማንኛውንም ዋጋ ከፍላ ሰላሟን፣ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን ማግኘት ትፈልጋለች፡፡

የሁቲ መሪ ሞሐመድ አል ቡካቲ በበኩላቸው፣ በሁቲና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል ሰላም ማስፈን ለየመንም ሆነ ለሳዑዲ ዓረቢያ ታላቅ ድል ይሆናል፣ የመንን ወደቀደመ ሰላሟ ለመመለስ ሁሉም ወገኖች ሊሠሩ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡

ጦርነቱ ከተጀመረ እ.ኤ.አ. ከ2014 ወዲህ ይህኛው የሰላም ውይይት ለየመን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ያስችላል ያሉት ደግሞ በየመን የተመድ መልዕክተኛ ሃንስ ግሩንድበርግ ናቸው፡፡

በቻይና አደራዳሪነት በሳዑዲ ዓረቢያና በኢራን መካከል የተደረሰው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሥምምነት በየመን ያለውን ጦርነት ለማክተም የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል ተስፋም ተጥሏል፡፡

ሆኖም በየመን ያለው ጦርነት በተለያዩ ያገባኛል ባዮች መካከል መሆኑ ሰላም ለማስፈን እንቅፋት ሊሆን እንደሚችልም ተገምቷል፡፡

ተመድ ከዚህ ቀደም ሁሉንም ተዋጊ ኃይሎች የፖለቲካ ውይይት እንዲያደርጉ ጥረት ማድረጉንም የአልጀዚራው ሃሺም አልቢራ ያስታውሳል፡፡ ሁሉንም ወገኖች መግባባትና ጽንፍ የረገጠ ልዩነታቸውን ማጥበብ ያስቸግራልም ይላል፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ ልዑክና በሁቲ በኩል የተደረገው ውይይት ምን አካቷል? ሮይተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደገለጸው፣ በሁቲና በሳዑዲ ዓረቢያ ልዑክ መካከል ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች በሁቲ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ወደቦችንና የሰንዓ አየር ማረፊያን መልሶ መክፈት፣ ለሠራተኞች ደመወዝ መክፈል፣ ሰላም ለማስፈን ያሉ ጥረቶችን መልሶ ማጠናከርና በየመን የሚገኙ የውጭ ኃይሎች ከአገሪቱ የሚወጡበትን የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የመን በተለያዩ ታጣቂ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር የምትገኝ ቢሆንም፣ ሳዑዲ ዓረቢያ ከሁቲ ጋር ብቻ ውይይት መጀመሯ፣ በሁለቱ መካከል የተነሱ ጉዳዮች በአግባቡ እንዳይፈጸሙ ሥጋት ሊሆን እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...