Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኦቲዝም ተጠቂዎች በአካቶ ትምህርት

የኦቲዝም ተጠቂዎች በአካቶ ትምህርት

ቀን:

በዓለም ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ይታመናል፡፡ አብዛኛው የኦቲዝም ተጠቂዎችም በራሳቸው ዓለም የሚኖሩና ቃላት አሰካክተው መናገር የሚቸገሩ ናቸው፡፡

የኦቲዝምን መንስዔ ለማወቅ ብዙ ጥረት ቢደረግም፣ መንስዔውንና መፍትሔውን በእርግጠኝነት ለመናገር አልተቻለም፡፡ ሆኖም በኦቲዝም የተጠቁ ልጆችን በተለያዩ ዘርፎች ማስተማርና ክህሎት እንዲያዳብሩ ማድረግ እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የኦቲዝም ተጠቂ ልጆችን ማስተማር ግን እንደ መደበኛ ተማሪዎች ቀላል አይደለም፡፡ በልዩ ፍላጎት ትምህርት የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ይፈልጋል፡፡

ይህንንም አሠራር በመከተል ሻምፒየንስ አካዳሚ የትምህርት ተቋም የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ በአካዳሚው የትምህርት አገልግሎቱን እያገኙ ከሚገኙት ውስጥ የአቶ መንግሥቱ ገብረመስቀል የመጀመርያ ልጅ ሕፃን አሜን ትገኛለች፡፡

ገና በጨቅላ ዕድሜዋ የኦቲዝም ተጠቂ የሆነችው አሜን፣ ችግሩ እንዳለባት የታወቀው በሒደት መሆኑን አባቷ አቶ ገብረ መስቀል ይገልጻሉ፡፡

የኦቲዝም ተጠቂ ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ባህሪዋ መቀየሩንና በእሷ ዕድሜ ክልል ላይ ከሚገኙ ሕፃናት ጋር ስትገናኝ ለብቻዋ እንደምትሆን አባቷ ይናገራሉ፡፡

የኦቲዝም ተጠቂ መሆኗ ከታወቀ በኋላ የተለያዩ የሕክምና ተቋሞች ጋር መሄዳቸውን በመጠቆም፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ የልጁን ባህሪ ቀድሞ በማጤንና ምልክቶችን በማየት የልጁን ጤና መታደግ ይኖርበታል ይላሉ፡፡

በተለይ እናቶች የልጆቻቸው ባህሪ ሲቀየር ወይም የተለየ ነገር ሲያዩ በአቅራቢያቸው በሚገኝ የሕክምና ተቋም ሄደው የልጆቻቸውን ጤንነት ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው አቶ ገብረመስቀል ተናግረዋል፡፡

ልጃቸው የኦቲዝም ተጠቂ ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ችግሮችን ማየታቸውን የሚናገሩት እኚህ አባት፣ ልጃቸውን ለመንከባከብ ለሁለት ዓመት ያህል ሥራ ማቋረጣቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሕፃናት ልጆች ሦስት ዓመት እስኪሞላቸው የኦቲዝም ተጠቂ መሆናቸው እንደማይታወቅና ምልክቱ ግን እንደሚታይ ይናገራሉ፡፡ ልጃቸውም ሁለት ዓመት ከአራት ወር አካባቢ ሲሆናት በሰው አማካይነት ሻምፒየንስ አካዳሚ መግባቷንና አሁን ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቷን ያስረዳሉ፡፡

 በአካዳሚው ከገባች በኋላ በጊዜ ሒደት ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተቀላቅላ እንደምትማር በአሁኑ ወቅትም የአፐር ኬጂ ተማሪ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

የአካቶ ትምህርት ውስጥ ከመቀላቀሏ በፊት መጀመሪያ ለብቻዋ በአንድ አስተማሪ ትማር እንደነበርና ለውጥ ስታመጣ ከመደበኛ ተማሪዎች መቀላቀሏን ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ልጃቸው ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቷን፣ ይህም ለእሳቸውም ሆነ ለባለቤታቸው ዕፎይታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡

የሻምፒየንስ አካዳሚ መሥራችና የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያ ወ/ሮ መዓዛ መንክር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ በኦቲዝም ተጠቂ የሆኑ ሕፃናትን ለመታደግና በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍና ማኅበረሰቡ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

የኦቲዝም ተጠቂ ልጆች ከሌሎች ልጆች እኩል ታይተው የትምህርት አገልግሎት ማግኘት እንዳለባቸው በመጠቆምም፣ ተቋሙ እዚህ ላ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡

አብዛኛው ማኅበረሰብ ጋር የግንዛቤ ችግር መኖሩን፣ የኦቲዝም ተጠቂ ልጆች የተሻለ ነገር እንዲያገኙና እንዲኖራቸው በዘርፉ የሠለጠነ ባለሙያ አለመኖሩን ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ ቁጥር ያላቸው የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናት በአካዳሚው እንደሚገኙና የአካቶ ትምህርት አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ወ/ሮ መዓዛ ተናግረዋል፡፡

የኦቲዝም ተጠቂ ለሆኑ ሕፃናት የሚሰጠው ቦታ አነስተኛ እንደሆነና ችግሩ በርካታ ወላጆች ላይ እንደሚታይ የተናገሩት መሥራቿ፣ ችግሩንም ለመቅረፍ የግንዛቤ መሠራት ይኖርበታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የየካቲት ሃያ ሦስት ልዩ ፍላጎት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርና የልዩ ፍላጎት ባለሙያ አቶ እስራኤል እሸቴ እንደገለጹት፣ የኦቲዝም ተጠቂ የሆኑ ልጆች አስፈላጊው እንክብካቤና ትምህርት እንዲያገኙ መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ አይደለም፡፡

በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ላይ የሚታየው ችግር ከፍተኛ መሆኑን በተለይም ያለው የባለሙያ ቁጥርና የኦቲዝም ተጠቂዎች ቁጥር አለመመጣጠኑ ችግሩን ከፍተኛ እንዳደረገው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በትምህርት ቤቱ ለመማር የሚመጡ የኦቲዝም ተጠቂዎች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም፣ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ባለመስጠቱ የተነሳ አብዛኛው ሕፃናት ከችግሩ ሲያገግሙ አይታይም በማለት አብራርተዋል፡፡

የየካቲት ሃያ ሦስት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት በጣም ጠባብና ለኦቲዝም ተጠቂዎች ምቹ ባለመሆኑ የተነሳ አብዛኛው ልጆች ላይ ለውጥ እንደማይታይና ወላጆች በአሁን ወቅት ልጆቻቸውን ከትምህርት ገበታቸው እያስቀሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ መስማት የተሳናቸውንና ሌሎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ልጆች ተቀብሎ እንደሚያስተምር ገልጸው፣ አገልግሎት የሚሰጡ መምህራን ቁጥር ግን ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የልዩ ፍላጎት ትምህርት ወስዶ የተመረቀ መምህር በትምህርት ቤቱ ውስጥ አለመኖሩ ችግሩን እንዳባባሰው፣ ይህም ለኦቲዝም ተጠቂ ተማሪዎች የሚሰጠው ቦታ ዝቅተኛ መሆኑን እንሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

የኦቲዝም ተጠቂዎች አግባብነት ባለው መልኩ ትምህርት እንዲያገኙና ስለኦቲዝም ማኅበረሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ሻምፒየንስ አካዳሚ አርቲስት ዕድለወርቅ ጣሰውን የተቋሙ አንባሳደር አድርጎ ሾሟታል፡፡

የሒሳብ ሊቅና ሳይንቲስቱ አልበርት አንስታይን፣ ተዋናይትና የአካባቢ ተሟጋች ዳሪል ሃናህ፣ ተዋናይ አንቶኒ ሆፕኪንስ፣ የፊልም ዳይሬክተሩ ቲም ቡርቶንና በርካታ ሰዎች የኦቲዝም እክል ኖሮባቸው በሙያቸው አንቱታን ካተረፉት ውስጥ ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...