ዕውቀትን የሚጋፋና ከዕውቀት ጋር ተቻችሎ መኖር ያቃተው ኅብረተሰብ አባሎች መሆናችንን መቀበል ይኖርብናል፡፡ እንደ ምዕራብ አገሮች ገዳማት ሁሉ የኢትዮጵያ ገዳሞች የምርምርና የፈጠራ ማዕከል መሆን ጀምረው ነበር፡፡ ብራና መሥራት፣ መጻፊያ ቀለም መበጥበጥ፣ በብራና መጻፍ፣ ሥዕላዊ ሐረጐች መሥራት፣ የመስቀል ሥራ፣ የሥዕል ሥራና የመሳሰሉት ጥበቦች ሁሉ በገዳማት አካባቢ ማበብ ጀምረው ነበር፡፡
ከገዳማት ውጭ ደግሞ የሸክላ፣ የሸማ፣ የእንጨት፣ የብረት፣ የሕንፃ ሥራዎች፣ ወዘተ በተጨባጭ ሥር ሰደው ነበር፡፡ በኋላ ግን ይህ ሁሉ ጥበብ እንደ አስማት ሥራ እንዲታይና እንዲወገዝ በመደረጉ ምክንያት የጥበብ ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀዘቀዘ መጣ፡፡ በግብፅ የሃይማኖት መሰሪ መሪዎች አማካይነት ይህ እንደተደረገ የሚገምቱ ወገኖች አሉ፡፡ አለቃ ታዬ ለአፄ ምኒልክ በጻፉት ደብዳቤ ይህንኑ አመልክተው ነበር፡፡ አፄ ምኒልክም የዕደ ጥበብ ባለሙያ ቢሰደብ ሰዳቢው በሕግ እንደሚቀጣ አዋጅ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡
ሸክላ ሠሪዎች፣ ብረት ቀጥቃጮች፣ ቆዳ ፋቂዎች፣ አናጢዎች፣ ደብተራዎች፣ ወዘተ በኅብረተሰብ ዘንድ የተዋረዱና የተገለሉ ወገኖች እንደነበሩ እናውቃለን፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ካህናትን፣ አፄ ዮሐንስ እነማኅደረቃልን፣ አፄ ምኒልክ አጽመ ጊዮርጊስን በጥርጣሬ ዓይን ይመለከቱ ነበር፡፡
ዛሬም ቢሆን መንግሥታችን የተማሩ ሰዎችን በጥርጣሬ ዓይን እንደሚመለከት ሚዲያ ሳይቀር እያወጀ ነው፡፡ በተለይ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተማሩ ኢትዮጵያውያን አገሪቱን እንዲመሩ ትልቅ ጉጉት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ አገራችንን በውጭ አገር ኤክስፐርቶች ለመምራት ጥረት ሲደረግ ይታያል፡፡ ያውም ሁሉም ዓይነት ሙያ ከቤት ሆኖ ለማፈስ በሚቻልበት ዘመን፡፡ ዞሮ ዞሮ ድምዳሜው ያው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ በተለይ የመንግሥትና የሃይማኖት መሪዎች ከዕውቀት ጋር ያላቸው አለመቻቻል ጉልህ መሆኑን መቀበል አለብን፡፡ ይህ ክፍል ሲደመደም ቤተመንግሥት፣ ቤተክህነትና ቤተመስጊድ ባመዛኙ የመቻቻል ዓይነተኛ ተምሳሌቶች እንዳልነበሩ እንገነዘባለን፡፡ እናዝናለንም፡፡
- ኃይሌ ወልደሚካኤል ‹‹አብሮነት በኢትዮጵያ›› (1994)