Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሰሞነኛው የአማራ ክልል ውጥረት ብልፅግናንና አብንን ፍጥጫ ውስጥ ከቷል

ሰሞነኛው የአማራ ክልል ውጥረት ብልፅግናንና አብንን ፍጥጫ ውስጥ ከቷል

ቀን:

ገዥው ብልፅግና ፓርቲና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በወቅታዊው የአማራ ክልል ውጥረት ምክንያት ተፋጠዋል፡፡

የክልል ልዩ ኃይሎችን በአገር መከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስና በክልል ፖሊስ መዋቅሮች እንዲደራጁ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ፣ በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ ገዥው ብልፅግናና አብን የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡

ስድስተኛ ቀኑን የያዘውና በአማራ ክልል በርካታ ከተሞች በቀጠለው ተቃውሞ የክልሉ ነዋሪዎች ውሳኔው ጊዜውን ያልጠበቀ፣ የክልሉን የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ከመሆኑም በላይ፣ የክልል ልዩ ኃይል መፍረስ ውሳኔ በክልላቸው ቀድሞ መጀመሩ ቁጣ እንደቀሰቀሰባቸው በፖለቲከኞች ዘንድ በተደጋጋሚ ተወስቷል፡፡

አብን መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የክልል ልዩ ኃይሎችን በሚመለከት ያሳለፈው ውሳኔ፣ በሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ በእኩል ደረጃ ተፈጻሚ የማይሆንና የውሳኔው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት መሆኑን ስለመገምገሙ አስታውቆ ነበር፡፡

ፓርቲው ከበቂ የሽግግር ጊዜ በኋላ የክልል ልዩ ኃይሎችን አደረጃጀት ማስተካከል እንደሚገባ የሚያምን መሆኑን ገልጾ፣ ጉዳዩን ከሕጋዊነት፣ ከወቅታዊና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር በመመርመር ገዥው ፓርቲ ያሳለፈው ውሳኔ ወቅቱን ያልጠበቀ እንደሆነ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

አብን ክስተቱ ከተፈጠረ ወዲህ በተከታታይ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ ባደረጋቸው መግለጫዎች፣ ሕወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት መሠረት ትጥቅ ባልፈታበት ልዩ ኃይልን ያለ በቂ ዝግጅት፣ ውይይት፣ የጋራ መግባባትና መተማመን ሳይደረስ በድንገትና ያለ በቂ የፀጥታ ዋስትና ለማፍረስ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየሄደበት ያለው መንገድ ኃላፊነት የጎደለው ነው ብሏል፡፡

በተመሳሳይ ገዥው ፓርቲና የፌዴራሉ መንግሥት ስህተቱን ከማረምና መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ፣ በጥፋት ላይ ጥፋት እየጨመረ ችግሩን እያወሳሰበና ክልሉን ለከፍተኛ አለመረጋጋትና የፀጥታ መደፍረስ እየዳረገው እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ በዚህም ሳቢያ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች የተቃውሞ ሠልፎች ስለመካሄዳቸውና መደበኛ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውን ጠቅሶ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ ጭምር የታገዘ ተኩስ በመኖሩ ይህ በአሰቸኳይ ይቁም ሲል ጠይቋል፡፡

አብን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት ጉዳዩን በተመለከተ፣ “ከጊዚያዊ መፍትሔ ዘላቂ ጥቅም አይገኝም” በሚል ርዕስ ባወጡት መግለጫ፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ትጥቅ የማስፈታት ውሳኔ ‹‹ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን ተግባራዊ እንደሚደረግና የሕግ ማስከበር ዕርምጃ እንደሚወሰድ›› ማለታቸው፣ በአማራ ክልል አለመረጋጋት እንዳይኖርና ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ነው ሲል አስታውቋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የአገራችን የፖለቲካ ተዋናያን ከሕገወጥና መርህ አልባ እንቅስቃሴ ሊቆጠቡ ይገባል፤›› ብሏል፡፡

ብልፅግና በመግለጫው አንዳንድ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው፣ እንዲሁም ማኅበራዊ አንቂዎች ነን የሚሉ ግለሰቦች፣ ጉዳዩን አንድን ክልል ብቻ ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ አድርገው የሚያቀርቡበትና ጉዳዩን ለመግለጽ የሚጠቀሙባቸው፣ ‹‹ማክሰም፣ ማጠፍ፣ ማፍረስ፣ መበተን…›› የሚሉት አገላለጾች ምንጫቸው ከየትና ምርጫቸው እንዴት እንደሆነ፣ ግባቸውም ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስና ሕዝብን ለማሳሳት በመሞከር ጊዜያዊ ቅቡልነት ለማግኘት የመጣር ፍላጎት ነው ሲል አስታውሷል፡፡

በመሆኑም ከዚህ አገርን ዋጋ ከሚያስከፍል ሕገወጥና መርህ አልባ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ በማሳሰብ፣ ‹‹ይህንን ውሳኔ በአማራ ክልል ላይ ብቻ የተወሰነ ውሳኔ አድርገው ለማቅረብ የሚጋጋጡ አገር ነቅናቂ ግጭት ናፋቂ ኃይሎች የሚነዙት መርዛማ መረጃ ፍጹም ሐሰት እንደሆነ ፓርቲያችን በአጽንኦት ማሳወቅ ይፈልጋል፤›› የሚለው የብልፅግና መግለጫ፣ ውሳኔው ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ተነጋግረው የተወሰነ ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ የጊዜ መስመር በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚተገበር ስለመሆኑ አስታውቋል፡፡

‹‹የክልል ልዩ ኃይሎች ሕገ መንግሥታዊ በሆኑት የፀጥታ መዋቅሮች ገብተው እንዲያገለግሉ መደረግ እንዳለበት ከብልፅግና እኩል (አንዳንዴም በላይ) ሐሳብ ሲያነሱና ሲሞግቱ የነበሩ ፓርቲዎችና አመራሮችም ጭምር ዛሬ ላይ ከሥጋው ፆማለሁ ከመረቁ ስጡኝ ዓይነት መግለጫ ለማውጣት መጋጋጣቸው ፓርቲያችንን በእጅጉ አሳዝኖታል፤›› ብሏል፡፡

ብልፅግና በመግጫው ሻማ እንዲሸጥላቸው ጨለማ የሚናፍቁና የሚጠብቁ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው፣ ነገሮችን ከማባባስና ሞትን ለመጥመቅ ግጭት ከመጠንሰስ እንዲቆጠቡ በአፅንኦት አሳስባለሁ ሲል አስታውቋል፡፡

አብን ማክሰኞ ሚያዝያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የልዩ ኃይልን ለማፍረስና ውሳኔውን ለማስፈጸም የወሰዳቸው ዕርምጃዎች፣ በአማራ ክልል ላስከተሉት ከፍተኛ አለመረጋጋት፣ የመደበኛ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎልና ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት መሆኑን ገልጿል፡፡

ገዥው ፓርቲ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ያወጣውን መግለጫ፣ ‹‹እውነታን የካደና አሁንም ገዥው ፓርቲ ለመፍትሔው ዝግጁ አለመሆኑን የሚያሳይ መሆኑን፣ ገዥው ፓርቲ ውሳኔው በአማራ ክልል ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተመሳሳይ የጊዜ መስመር የሚተገበር ነው ቢልም፣ ከአማራ ክልል በቀር በየትኛውም ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላትን ትጥቅ የማስፈታት ወይም በገዥው ፓርቲ አነጋገር “መልሶ የማደራጀት” እንቅስቃሴ አልተደረገም፤›› ብሏል፡፡

በዚህም ገዥው ፓርቲ ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተስማሙበት ውሳኔ መሆኑን ሲናገር የቆየ ቢሆንም፣ የአማራ ክልልን ጨምሮ የየትኛውም ክልል ካቢኔ ወይም ምክር ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ ያደረገው ውይይትም ሆነ ያሳለፈው ሕጋዊ ውሳኔ የሌለ መሆኑን አብን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

በስድስተኛው ምርጫ ተወዳድረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑ አምስት የአብን ተወካዮች ማክሰኞ ሚያዝያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲፈርሱ ያሳለፈውን ውሳኔ፣ በፌዴራል መንግሥት ስምና በመከላከያ ሠራዊት የኃይል ዕርምጃ ለማስፈጸም የሚያደርገውን ፋሽስታዊ ዕርምጃ ሊያቆም ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

የአብን የፓርላማ አባላት በመግለጫቸው የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መጋቢት 2015 ዓ.ም. የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀትን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ አገሪቱ ከነበረችበት አንፃራዊ መረጋጋት፣ ሰላምና ተስፋ መፈንጠቅ ወደ ትርምስ፣ ሥጋትና የመበተን አደጋ ገብታለች ሲሉ በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ፓርቲው ሕገ መንግሥታዊ የመንግሥትና ሕዝብ ተቋማትን ‹‹እንደ ፓርቲው አደረጃጀት የቆጠረ፣ ለብቻው በፓርቲ ደረጃ በሕዝብና በመንግሥት ተቋማት ላይ አዛዥ ናዛዥ እንደሆነ አድርጎ ያቀረበ በመሆኑ ከሕግ፣ ከሞራልና ከአሠራር አንፃር ተቀባይነት የሌለው ነው፤›› ሲሉ አባላቱ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የታጠቀ ኃይል ማንቀሳቀስ የማይችሉ መሆናቸውን የሚደነግገውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር የተመለከተውን አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የተላለፈ መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የብልፅግና ፓርቲን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሕግ የጣሰ ውሳኔ በመመርመር በፓርቲው ላይ ተገቢውን የሕግ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

በአማራ ክልል እየተደረጉ ባሉ የተቃውሞ ሠልፎች የማኅበራዊ አገልግሎቶች የተቋረጡ ሲሆን፣ ከክልሉ ውጪ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ተቋርጠዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት በከተሞች ሥምሪት ማድረጉ የታወቀ ሲሆን፣ በአንዳንድ ከተሞች የመከላከያ ሠራዊት ከታጠቁ አካላት ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጉና ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ዜጎች መገደላቸውና መቁሰላቸው እየተገለጸ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...