Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበደብረብርሃን ከተማ ሁሉም ነገር ዝግ ከመሆኑም በተጨማሪ መግባትም ሆነ መውጣት እንዳልተቻለ ነዋሪዎች...

በደብረብርሃን ከተማ ሁሉም ነገር ዝግ ከመሆኑም በተጨማሪ መግባትም ሆነ መውጣት እንዳልተቻለ ነዋሪዎች ተናገሩ

ቀን:

  • በከተማው ውስጥና ዙሪያው የተኩስ ልውውጥ መኖሩም ተጠቁሟል
  • ወደ ደሴ መውጫ እስከ ጣርማ በር ተሽከርካሪዎች ከነጭነታቸው መቆማቸው ታውቋል

የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና ማደራጀት ወይም ወደ መከላከያ፣ ፖሊስ፣ ፌዴራል ፖሊስ ለማካተት ወይም ወደ ሲቪል ለመመለስ ከተጀመረው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ፣ በተለይ በአማራ ክልል ተቃውሞ መነሳቱ ይታወቃል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ከእሑድ ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ሰላማዊ ሠልፍ የተደረገ ሲሆን፣ የሪጂዮ ሜትሮ ፖሊቲያን ከተማ መሆኗ በምትታወቀው ደብረብርሃን ከተማ ግን ጉዳዩ ከረር ብሎ ቀጥሏል፡፡

በከተማው እሑድ ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ውዥንብር እንደነበረ የከተማው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን፣ በተለይ ከትናንት በስቲያ ሚያዚያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሁሉም እንቅስቃሴ መቆሙን ተናግረዋል፡፡ አቶ ሰላሙ ተገኝ የተባሉ የደብረብርሃን ነዋሪ ለሪፖርተር እንደለጹት፣ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ከከተማው መግቢያ ማለትም ከአዲስ አበባ ወደ ደብረብርሃን መግቢያ አካባቢ ወይም ዳሸን ቢራ ፋብሪካ አካባቢ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ሲሰማ ነበር፡፡ የተኩስ ድምፅ የሚሰማው ከሁለት አቅጣጫ የሚመስል ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ሌሊቱን አድሮ ማክሰኞ ትናንት ሚያዚያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ተኩሱ ያለማቋረጥ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

እሳቸው እንደተናገሩት፣ ምክንያቱ የመከላከያ ሠራዊት ልዩ ኃይሎችን ትጥቅ ለማስፈታት ወደ ደብረብርሃን በመምጣቱ እንደሆነ መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሰሞኑን በተለያዩ የመረጃ መንገዶች የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ፋኖ ትጥቅ ሊፈቱ እንደሆነ ሲነገር በመክረሙ፣ በአካባቢው የሚገኙት የልዩ ኃይል አባላት ‹‹ለምን?›› በማለት ሳይቃወሙ እንዳልቀሩና መከላከያ መግባት የለበትም የሚል አቋም ይዘው እየተታኮሱ ሊሆን እንደሚችል ነዋሪው አስረድተዋል፡፡

የደብረብርሃን ከተማ ሰኞ ከሰዓት ጀምሮ ተቋማት፣ የንግድ ተቋማትና ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ሥፍራዎች ዝግ መሆናቸውን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

ከእሑድ ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከደሴና አካባቢ ከተሞች ወደ ደብረብርሃን የሚገቡ የሰው ማመላለሻ አውቶቡሶች (ሽንኩርት፣ ሙዝ፣ ቅቤ፣ ጥራጥሬና ሌሎችም) የጫኑ አይሱዙዎችና ሌሎችም ተሽከርካሪዎች በተለምዶ ደብረብርሃን መውጫ (አስመራ በር) እና ወደ አንኮበር መገንጠያ መንገድ አንስቶ እስከ ቀይት፣ ባቄሎና ጣርማበር ድረስ መቆማቸውን ተናግረዋል፡፡ የጫኗቸው ሸቀጣ ሸቀጦች የሚበላሹም ስላሉባቸው ሊበላሹ እንደሚችሉም አክለዋል፡፡ ለተለያዩ ጉዳዮች ከአዲስ አበባ ወይም ከደሴና ሌሎች ከተሞች ተነስተው በመንገድ ላይ የቀሩት ተሳፋሪዎችም፣ ገንዘብ ያለው በእግር ወደ ደብረብርሃን መግባቱንና የሌለው በተሳፈረበት መኪና ውስጥ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ችግሩ ጠንከር ያለ መሆኑን መንግሥት ተገንዝቦ ነገሮችን በኃይልና በእልህ ሳይሆን በመነጋገርና በመወያየት መፍታት እንዳለበት ጠቁመው፣ ያ የማይሆን ከሆነ ግን ለአገርም ሆነ ለወገን የሚፀፅት ነገር ሊከሰት እንደሚችል ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተያያዘ ዜናም በአጣዬ ከተማና ዙሪያው ከፍተኛ ተኩስ መኖሩና በተለይ ሴቶችና ሕፃናት አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡ በአጣዬ ከተማ የመከላከያ ሠራዊት መኖሩን ጠቁመው ሁኔታው ግን እንደሚያስፈራና ተጨማሪ ኃይል ሳያስፈልግ እንደማይቀር ግን ሥጋታቸውን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...