Tuesday, September 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከቅርቡ የዕልቂትና የውድመት ታሪክ መማር ይገባል!

መሰንበቻውን የክልል ልዩ ኃይል አባላትን መልሶ በማደራጀት ወደ አገር መከላከያ ሠራዊት፣ ወደ ፌዴራል ፖሊስ፣ ወደ ክልል ፖሊስ ወይም ወደ ሲቪል ሕይወት እንደ ምርጫቸው ለማሰማራት የተደረሰው ውሳኔ በተለይ በአማራ ክልል ከባድ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር፣ በገዥው ብልፅግና ፓርቲና በሌሎች አካላት ስለውሳኔው አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ሰፋፊ ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል፡፡ ማብራሪያዎቹንም ሆነ ተቃውሞውን በአንክሮ የሚከታተሉ ወገኖችም ጠቃሚ ነው የሚሉትን ሐሳብ እያጋሩ ነው፡፡ የብዙዎቹ እምነትም ኢትዮጵያ በአንድ የአገር መከላከያ ሠራዊት መጠበቅ እንዳለባት ነው፡፡ ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ተግባር ግን ልዩ ጥንቃቄ ተደርጎ ግልጽነት የተላበሰ እንዲሆን ከአየቅጣጫው ጥያቄ እየቀረበ ነው፡፡ ሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ውሳኔውን እኩል ተግባራዊ የማድረጋቸው ጉዳይ ጥያቄ እያስነሳ ሲሆን፣ የአማራ ክልል ካለበት የፀጥታ ሥጋት አኳያ ቀዳሚ በመደረጉ በተቃውሞ የታጀቡ ከፍተኛ ግጭት የሚያስነሱ ምልክቶች እየታዩ በመሆናቸው ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ኢኮኖሚው ከባድ ችግር ውስጥ ሆኖና አስመራሪው የኑሮ ውድነት የብዙዎችን ሕይወት እያመሰቃቀለ፣ እንደገና የግጭት አዙሪት ውስጥ መገኘት ብዙዎችን እያስፈራ ነው፡፡

ሁሌም እንደምንለው ማንኛውም የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ ሆኖ ተጠያቂነት ሊኖርበት ይገባል፡፡ አሁን የተጀመረው የልዩ ኃይል አደረጃጀትን የመቀየር ሥራም ግልጽና አሳማኝ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ቀደም ክልሎች ለምን ልዩ ኃይል ይኖራቸዋል የሚለው ጥያቄ የብዙዎች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር የሚገዳደር ትጥቅ የያዙ ኃይሎች መኖር እንደሌለባቸውም የብዙዎች እምነት ነው፡፡ እንደተባለውም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት የማስከበር ተልዕኮ የእሱ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ሠራዊቱም በብቁ የሰው ኃይል፣ በዘመናዊ ትጥቆች፣ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት ጎልብቶ አገርን የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሁለንተናዊ ዕገዛ ማድረግም ተገቢ ነው፡፡ ይህንን ክቡር ዓላማ ለማስፈጸም ተብሎ ከዚህ ቀደም የተገባበትን ስህተት ለማረም ሲፈለግ ግን፣ የውሳኔው አፈጻጸም ሒደት የግብር ይውጣ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ሁሉንም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ የሚያሳትፍ መሆን ይኖርበታል፡፡ ተቃውሞ ከተነሳባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ጋር ግልጽ ውይይት በማድረግ፣ በችኩልነት ከሚወሰዱ ዕርምጃዎች መታቀብ አስፈላጊ ነው፡፡

በሕዝባችን ውስጥ የሚታዩት ጨዋነት፣ አርቆ ማሰብ፣ መከባበር፣ መመካከር፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በብልኃት መፍታት፣ አገርን በጋራ የመጠበቅና የመሳሰሉት ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ያገለገሉ ዋነኛ ሀብት ናቸው፡፡ ይህንን የመሰለ ሀብት በማባከን ችግር ውስጥ መግባት ተገቢ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያችን  ለዘመናት ስሟን  በክፉም  በደጉም  ያስጠሩ  በርካታ  ውጣ  ውረዶችን  ያለፈች አገር  ናት፡፡  በአራቱም  ማዕዘናት  በተለያዩ  መልክዓ  ምድራዊ  አሠፋፈር  ውስጥ  ሆነው  ከእነ ልዩነቶቻቸው  የራሳቸውን  የጋራ  ማንነት  የፈጠሩ  ልጆቿ፣  ልዩነቶቻቸውን  ውበትና  ጥንካሬ  አድርገው  ለዘመናት  በአንድነት  ኖረዋል፡፡  በዚህ ዘመንም ችግሮች ሲያጋጥሙ በመነጋገርና በመደማማጥ ለመፍታት የሚያስችሉ ሁኔታዎች እያሉ፣ አላስፈላጊ ውዝግቦች ውስጥ በመግባት ደም መቃባት ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡  የኢትዮጵያዊነት  ትልቁ  ምሥል  መገለጫ  የሆኑት  ጥልቅ  የአገር  ፍቅር፣  መከባበርና መዋደድ የሕዝባችን የጋራ ማኅበራዊ  እሴቶች  መሆናቸው  የታወቀ  ነው፡፡  በአንድ ጉዳይ ላይ ልዩነቶች ሲያጋጥሙ ዘሎ ጦር ከመስበቅና ይዋጣልን ከማለት በፊት፣ የልዩነቶችን መንስዔ በመመርመር የሚያግባባ ውሳኔ ላይ መድረስ ከጥፋት ያድናል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ አንገቷን እንድትደፋ ባደረጓት የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነትና በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ዘግናኝ ግጭቶች ከፈሰሰው የንፁኃን ደም በቅጡ ሳትነፃ፣ እንደገና ለሌላ ዙር ፍጅት የሚያዘጋጅ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ስትገኝ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል፡፡ ካለፉት አሳዛኝና አሳፋሪ የዕልቂትና የውድመት ክስተቶች መማር አቅቶ፣ በውይይት መፍትሔ ሊያገኙ የሚችሉ ጊዜያዊ ችግሮችን በመለጠጥ ቅራኔ ማባባስ አያስፈልግም፡፡ አሁንም ጊዜው አልረፈደምና በጉዳዩ ላይ በግልጽ ተነጋግሮ ለመፍትሔ መትጋት ለሁሉም ወገኖች ይጠቅማል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው የትግራይ፣ የአማራና የአፋር ክልሎች በተጨማሪ ሌሎች አካባቢዎችም በተፅዕኖው ምክንያት ኢኮኖሚያቸው ተጎድቷል፡፡ በመላ አገሪቱ ሕዝባችን ከዕለት ወደ ዕለት በኑሮ ውድነቱ ምክንያት ቁልቁል እየወረደ ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ከሚጠብቁ ተፈናቃይ ወገኖች በተጨማሪ፣ በድርቅ ምክንያት የሚቀምሱት አጥተው የምግብ ያለህ የሚሉ ወገኖች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ያለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሌላ ዙር ጦርነት ለማስተናገድ አቅም የለውም፡፡

በተደጋጋሚ መልካም ዕድሎች ያመለጧት ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ያገኘችውን አጋጣሚ መጠቀም ሲያቅታት፣ ካለፉ ስህተቶች ለመማር አለመፈለግን ፍንትው አድርጎ ነው የሚያሳየው፡፡ በደም የጨየቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አንፃራዊ ሰላም ሊገኝ ነው በማለት በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተሰንቆ የነበረ ቢሆንም፣ በሰሞኑ ክስተት አማራ ክልል ውስጥ አደገኛ ውጥረት ሲፈጠር ለመፍትሔው ከመነጋገር ውጪ ሌላ አማራጭ ሊኖር አይገባም፡፡ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልሉ ብሔራዊ መንግሥት አለመግባባቱን በተመለከተ ጥያቄ ከሚያቀርቡ አካላት ጋር ግልጽ ውይይት ቢያደርጉ፣ አላስፈላጊ ዋጋ ከሚያስከፍል ጥፋት ለመታቀብ ይረዳል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነትም ሆነ የጦርነት ወሬ ሰልችቶታል፡፡ ከታሪኳ አብዛኛው ክፍል ጦርነት የሆነባት ኢትዮጵያ በዚህ በሠለጠነ ዘመን የገባችበት ፍጅት በወጉ ሳይጠናቀቅ፣ ለሌላ ዙር ዕልቂትና ውድመት የሚዳርግ የጥፋት መደላድል መፍጠር ለማንም አይጠቅምም፡፡ ይልቁንም ከረሃብ ጋር የተፋጠጡ ምስኪን ወገኖችን ለመታደግ የሚያስችሉ ኢኮኖሚያዊ ግንባታዎች ላይ ማተኮር ይመረጣል፡፡ የረባ ምግብ ብርቅ በሆነባት ኢትዮጵያ ውስጥ ለፍጅት ማኮብኮብ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡

የአገር  ጉዳይ  ያገባናል  የሚሉ  ዜጎች  አገርን  ሊያፈርስ የሚችል አደጋ ሲያንዣብብ  የማክሸፍ  ታሪካዊ  ኃላፊነት  አለባቸው፡፡  ኢትዮጵያን  ኢትዮጵያ  የሚያሰኟት  ኦሮሞው፣  አማራው፣  ትግሬው፣  ጉራጌው፣  ጋምቤላው፣  ወላይታው፣  አፋሩ፣  ሶማሌው፣  ሲዳማው፣  ወዘተ.  አገራቸውን ከጥፋት ለመታደግ በአንድነት ይቁሙ፡፡ ከ80  በላይ  እንደሆኑ  የሚነገርላቸው  ማንነቶች  ለዘመናት  የገነቧትና  መስዋዕትነት  የከፈሉላት  ኢትዮጵያ፣  በንግግርና በድርድር ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮቿ እንዲያጠፏት  መፍቀድ የለባቸውም፡፡  ይልቁንም  በታላቁ  የኢትዮጵያዊነት  ጥላ  ሥር  እኩልነት  እንዲሰፍን፣  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣  ፍትሐዊ የሀብት  ክፍፍል እንዲኖር፣  አምባገነንነት  እንዲወገድ፣  የሕግ  የበላይነት  እንዲረጋገጥና  ለመሳሰሉ መልካም አገራዊ ጉዳዮች  በአንድነት ይታገሉ፡፡  ከዚህ ታላቅ ዓላማ የሚያፈነግጡ ችግሮች አደጋ አይፍጠሩ፡፡  ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት የሚረጋገጡት ታላቁ የኢትዮጵያዊነት  ምሥል ከምንም ነገር በላይ ትኩረት ሲቸረው ነው፡፡ ከቅርቡ የዕልቂትና የውድመት ታሪክ መማር የግድ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...