Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የምንዛሪ ገበያ እንዳይኖር ሊመክሩ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን የሁለትዮሽ የውጭ ምንዛሪ ገበያ እንዳይቀጥል ለማድረግ የሚያስችል መፍትሔ ለማግኘት በዚህ ሳምንት ስብሰባ ሊቀመጡ መሆናቸውን ገለጹ፡፡

ስብሰባው በዚሁ ሳምንት መካሄድ በጀመረው የሁለቱ ተቋማት ዓመታዊ የስፕሪንግ ጉባዔ (Spring Meetings) ጎን ለጎን እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴን ጨምሮ የኢትዮጵያ ልዑክ ጉባዔውን ለመካፈል በዋሽንግተን ይገኛሉ፡፡

ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪ ማልያስና የአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት የጋራ ውይይት፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ካሉበት ውስብስብ ችግሮች እንዴት መውጣት እንደሚችሉ ከጉባዔው መፍትሔ ሊገኝ ይችላል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ያለው የሁለትዮሽ የምንዛሪ ገበያ ትልቅ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሕጋዊው የምንዛሪ ገበያ ጥቂቶችን ብቻ ነው የሚያገለግለው፡፡ ሕገወጥ የሆነው የትይዩ ገበያ ደግሞ በጣም ውድ ስለሆነ እሱም ጥቂቶችን ያገለግላል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ምንዛሪ ገበያ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በዚህ ሳምንት በጠረጴዛ ዙሪያ እንሰባሰባለን፤›› ሲሉ ዴቪድ ማልያስ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት በኢትዮጵያ ካለው 120 ሚሊዮን ሕዝብ አብዛኛው በሁለትዮሽ ገበያ ሥርዓት ምክንያት እየተጎዳ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ አራት ዓመታት ያለፋቸው ማልያስ እ.ኤ.አ. 2019 ኢትዮጵያ መጥተው የነበረ ሲሆን፣ በዚያው ዓመት የአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክርስቲና ጅዮርጅዮሽም ኢትዮጵያን ጎብኝተው ነበር፡፡

የዕዳ ሽግሽግንም በተመለከተ ተጨባጭ ውሳኔ ከዚህ ጉባዔ እንደሚጠበቅ ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ሁሉም አብዳሪዎች ከተበዳሪዎች ጋር ለመጀመርያ ጊዜ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚመክሩ ተነግሯል፡፡ ስብሰባው (ጉባዔው) ከሰኞ እስከ እሑድ ይደረጋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በአይኤምኤፍ አማካሪነት ሀብታም አገሮችና ሌሎች አበዳሪዎች ሊያደርጉ ከተስማሙት የታዳጊ አገሮች ዕዳ ሽግሽግ ተጠቃሚ ለመሆን የሁለትዮሽ ምንዛሪ ገበያውን አንድ ማድረግ (Currency Unification) እንዳለባት እንደ ቅድመ ሁኔታ ተጠይቋል፡፡  

ሕጋዊውን የምንዛሪ ገበያና የትይዩ ገበያን አንድ ለማድረግ የብርን የመግዛት አቅም አሁን ካለበት ቢያንስ በእጥፍ በማወረድ (Devaluation) የጥቁር ገበያው አሁን ካለበት እኩል ማድረግ ግዴታ መሆኑን፣ ሁለት ተቋማት ሲወተውት እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ሳምንታት አዲስ አበባ የከረሙት የአይኤምኤፍ የባለሙያ ቡድን፣ ይህንን አቋም አጠናክሮ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሲገለጽ መቆየቱን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

‹‹አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አላት ብለው አያስቡም፡፡ ችግሩ የምንዛሪ  አስተዳደሩ ነው ብለው ይደመድማሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክራቸው የብርን የመግዛት አቅም እንደገና በማውረድ የጥቁር ገበያው ምንዛሪ አሁን ካለበት እኩል ማድረግ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ጥቁር ገበያው አሁን ካለበት አማካይ 100.00 ብር አካባቢ) ከፍ እያለ ለመሄድ አይችልም ወይም ረዥም ጊዜ ይወስድበታል ብለው ያስባሉ፤›› ይላል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የምጣኔ ሀብት አማካሪ፡፡

ውሳኔው በተተገበረበት ብሔራዊ ባንክ ባለፉት ዓመታት በቁጥቁጥ ሳያወርድ የነበረውን የብር የመግዛት አቅም በቅርቡ ያንሸራትታል ይላሉ አማካሪ፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ውሳኔ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲመጣ ማድረግ ቢችልም፣ የጎንዮሽ ጉዳቱ ግን የገቢ ምርቶችን ማስወደድና በኢትዮጵያ ያለውን የዋጋ መናር ማባባስ ነው ይላሉ፡፡  

የሳምንታት ቆይታቸውን ባለፈው ቅዳሜ ያጠናቀቁት የኤይኤምኤፍ የባለሙያዎች ቡድን ባወጡት አጭር መግለጫ፣ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ቁጥር ሁለትን ለመደገፍ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ በረቂቅ ደረጃ ያለው ሁለተኛው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ዶክመንት የምንዛሪ ገበያው ቀስ በቀስ መከፈቱ (Liberalize) እንዳለበት ይጠቁማል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች