Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናልዩ ኃይሎችን መልሶ በማደራጀት እንቅስቃሴ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መበት ጥሰቶችን መንግሥት እንዲያስቆም ኢሰመጉ...

ልዩ ኃይሎችን መልሶ በማደራጀት እንቅስቃሴ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መበት ጥሰቶችን መንግሥት እንዲያስቆም ኢሰመጉ ጠየቀ

ቀን:

የክልል ልዩ ኃይሎችን ለማደራጀት እየተከናወነ ባለው እንቅስቃሴ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መንግሥት እንዲያስቆም፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጠየቀ፡፡

መንግሥት መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለመጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት አቅጣጫ በማስቀመጥ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አባላት እንደ ምርጫቸው በመከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስና በክልል ፖሊስ አባልነት መካተት እንደሚችል መግለጹን ያስታወሰው ኢሰመጉ፣ ‹‹ከዚህ ጋር ተያይዞ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ከመንግሥት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በአፈጻጸም ተገቢነት ላይ የተለያዩ ግንዛቤ በመኖሩ ምክንያት፣ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ድርጊቱን በመቃወም ሠልፍ የተደረገ ሲሆን፣ እነዚህንም ሠልፎች ተከትሎ መንገዶች መዘጋታቸውንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች መረዳት ችያለሁ፤›› ብሏል፡፡

ኢሰመጉ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመንግሥት ባደረገው ጥሪ፣ ‹‹ይህ በመንግሥት እየተወሰደ ያለው የልዩ ኃይል አባላትን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ በሌሎች ክልሎች እኩል ተፈጻሚነት ያለው በመሆኑ፣ ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንዳይገጥሙ አካሄዱንና ምክንያቱን አስመልክቶ ኅብረተሰቡን ያማከለና ግልጽ ሊሆን ይገባል፤›› በማለት አሳስቧል፡፡

‹‹ይህንን ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለውን አደረጃጀት በሕግ ማዕቀፍ በተደገፈና አገራዊ መልክ ያለው አደረጃጀት መዘርጋት የሚደገፍ ተግባር ቢሆንም፣ ከአፈጻጸም ጋር ተያይዞ ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላትና በአጠቃላይ ለማኅበረሰቡ እንቅስቃሴውን ግልጽ ማድረጉ ለሚፈጽመው ተግባር ቅቡልነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤›› ሲል ኢሰመጉ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡

በመንግሥት እየተወሰደ ያለው የልዩ ኃይል አባላትን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ የክልሎችን ነባራዊ ሁኔታ፣ እንዲሁም ሥጋት ከግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን እንደሚገባ፣ መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴው የዜጎችን ደኅንነት ሥጋት ላይ የማይጥልና ከመልሶ ማደራጀት እንቅስቃሴው ጋር ተያይዞ ሥጋት ውስጥ የሚወድቅ ወይም ደኅንነቱ አደጋ ውስጥ የሚወድቅበት አካል ሊኖር እንደማይገባ የገለጸው ኢሰመጉ፣ ‹‹ስለሆነም መንግሥት ይህንን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ በሚከውንበት ወቅት ከላይ ለተጠቀሱት ነጥቦች ተገቢውን በቂ ትኩረት በመስጠት ከሥጋት የፀዳ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ፀጥታና ሰላም ዜጎችን ደኅንነት የሚጠብቅና ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበት አገራዊ ግንባታ ላይ ያተኮረ መሆን አለበት፤›› ሲል አሳስቧል፡፡

ኢሰመጉ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት እያካሄደ ያለውን የልዩ ኃይል አባላትን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ ለባለድርሻ አካላትና ለአጠቃላይ ማኅረሰቡ ግልጽና በምክር ላይ የተመሠረተ በማድረግ፣ ይህንን እንቅስቃሴ በሰላማዊ መንገድ በትዕግሥትና ዘላቂ ሕጋዊ መፍትሔ ከማምጣት አንፃር እንዲፈጸም፣  የልዩ ኃይል አባላትን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴው ጋር ተያይዞ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያስቆምና መሰል ጥፋቶች እንዳይፈጸሙ ተገቢውን ትኩረትና ጥንቃቄ ሰጥቶ እንዲሠራ ጠይቋል፡፡

የፌዴራል እንዲሁም የሚመለከታቸው የክልል መንግሥታት ለጉዳዩ ሰላማዊ፣ ዘላቂና የማኅበረሰቡን ደኅንነትና ጥበቃ የሚያረጋግጡ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጡ ያሳሰበው ኢሰመጉ፣ ‹‹ማንኛውም ሰው ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብቱን፣ ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቱን የሌላውን መብት ባልጣሰና በሕግ አግባብ እንዲለማመድ፣ እንዲሁም መንግሥት ሰዎች እዚህን መብቶች እንዲጠቀሙ ያላግባብ ገደቦችን እንዳይጥል፤›› ሲልም አሳስቧል፡፡

ኢሰመጉ አክሎም፣ ‹‹መንግሥት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ የተዘጉ መንገዶችን በማስከፈት የዜጎችን የመዘዋወር መብት እንዲያስከብር፣ ኅብረተሰቡ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት፣ የሲቪል ማኅበራትና የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በውጭ የሚኖሩ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ጋዜጠኞችና ልዩ ልዩ የሚዲያ አውታሮች፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ነገሮች እየተባባሱ ሄደው ለከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይዳረጉ ነገሮችን በትዕግሥትና በማስተዋል አገራዊ አንድነትና ሰላምን ለመገንባት በሚያስችል መንገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በክልሎች የአካባቢያዊ ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር በሚል የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀት በመዘርጋት እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ እንደቆዩ በመግለጫው የጠቀሰው ኢሰመጉ፣ ‹‹ሆኖም በእነዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በሰሜኑ ክፍል ከፍተኛ ቀውስ ያስከተለባቸው ጊዜዎች የቅርብ ትውስታዎቻችን ናቸው፡፡ ይህ አደረጃጀት ጅማሬው ሰላምና ፀጥታ የማስከበር እንቅስቃሴ ቢሆንም በተደጋጋሚ በማኅበረሰብ አንቂዎች፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በጋዜጠኞች፣ በውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሕገ መንግሥታዊ መሠረት እንደሌለውና አስፈላጊ አለመሆኑ ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ክልሎች ልዩ ኃይሎቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ በማደራጀት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት መሆናቸው የሚታወስ ነው፤›› ሲል በመግለጫው አክሏል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...