‹‹የግንባታ ፈቃድ ማውጣት እንዳለብን አሁን ነው ያወቅነው››
ፍቅሬ ደሳለኝ (ፕሮፌሰር)፣ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት
‹‹እኔ ከፕሮፌሰር እንደዚህ ያለ መልስ አልጠብቅም››
ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ፣ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ
የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ከሚመለከታቸው አካላት የተሰጠ የግንባታ ማረጋገጫና ፈቃድ ሳይኖረው ግንባታ እያከናወነ እንደሆነ፣ በፌዴራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝት ተረጋገጠ፡፡
የዩኒቨርሲቲውን የ2013/14 ዓ.ም. የሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ እንደተጠቆመው፣ ከበርካታ የኦዲት ግኝቶች መካከል የከተማና ልማት መመርያ የጣሱ ግንባታዎች መፈጸማቸው ተገልጿል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በግኝቶቹ ላይ ለመነጋገር መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በጠራው ስብሰባ፣ የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎችና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ተገናኝተው ነበር፡፡
የክዋኔ ኦዲት ሪፖቱን በሚመለከት ቋሚ ኮሚቴው ያዘጋጃቸውን ጥያቄዎች በዝርዝር በንባብ ያቀረቡት፣ የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ዝናዬ ነጋሽ ሲሆኑ፣ ከጥያቄዎቹ መካከልም ዩኒቨርሲቲው ለምን ያለ ፈቃድ ግንባታ እንደፈጸመ ምላሽ የሚጠይቅ ነው፡፡ ‹‹ግንባታ ከመጀመሩ በፊት መሟላት የነበረባቸውን ጉዳዮች ማሟላት ሲገባው፣ ከሚመለከተው አካል ተረጋግጦ የተሰጠ የፕላን ስምምነትና የግንባታ ፈቃድ ማስረጃዎች ሳይሟሉ ሕንፃዎች የተገነቡ መሆናቸው በኦዲቱ ታይቷል፤›› ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል አብራርተዋል፡፡
ለጥያቄዎቹ አብዛኛውን ማብራሪያ የሰጡት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፍቅሬ ደሳለኝ (ፕሮፌሰር) ሲሆኑ፣ ያለ ማረጋገጫና ፈቃድ ተገነቡ የተባሉትን ሕንፃዎች በሚመለከት ድርጊቱን እንደ ጉድለት እንደሚያዩት ገልጸዋል፡፡ ተቋማቸው ግኝቶቹን እንደ ጉድለት ቢያየውም፣ ፈቃድ ማውጣት ይኖርባቸው እንደሆነ ካለማወቅ እንደተከናወነም አስረድተዋል፡፡
‹‹ግለሰቦች ግንባታ ሲፈጽሙ ፈቃድ ያወጣሉ፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ተቋማት ባላቸው ይዞታ ግንባታ ሲፈጽሙ ፈቃድ ከከተማ አስተዳደሩ ማውጣት እንዳለባቸው አሁን ነው እየተማርን ያለነው፤›› በማለት ፍቅሬ (ፕሮፌሰር) ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡ ‹‹በተቋም ደረጃ ማወቅ ነበረብን፣ ይኼን ጉድለት ነው ብለን ነው የወሰድነው፤›› ብለዋል፡፡
ሌላው ከማረጋገጫና ከፈቃድ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲው ካልነበረው ዕቅድ ውጪ መገንባቱን በሚመለከት ለተነሳላቸው ጥያቄ ፕሬዚዳንቱ ሲያስረዱ፣ ዩኒቨርሲቲው ባለበት ሲኤምሲ አካባቢ ካሉት ሕንፃዎች አኳያ መሠረት በማድረግ እንደታቀደ፣ እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው ሦስትና አራት ፎቅ በማድረግ መጀመርያ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ዩኒቨርሲቲው አመራር ቦርድ ዕቅዱ ማነሱንና ማሻሻያ ተደርጎ ስምንትና አሥር ፎቅ ሆኖ እንዲገነባ መወሰኑን ጠቁመው፣ ‹‹በእርግጥ ትክክለኛ ከሆነው ከከተማና መሠረተ ልማት ማረጋገጫ መውሰድ ነበረብን፡፡ ይኼንን እንደ ጉድለት ነው የምናየው፤›› ሲሉ ፍቅሬ (ፕሮፌሰር) ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ምላሽ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ‹‹ፈቃድ እንደማያስፈልግ አናውቅም›› ተብሎ ለተመለሰው መልስ፣ ‹‹እውነትም አለማወቅ ይሁን አይሁን የሚለው መታየት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይኼን የመሰለ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ፈቃድ እንደሚያስፈልገውና እንደማያስፈልገው አያውቅም ነበር?›› ብለዋል፡፡
ምክትል ሰብሳቢዋ አክለውም፣ ‹‹መዳፈር አይሁንብኝና እኔ ከፕሮፌሰር ይኼን መልስ አልጠብቅም›› ብለው፣ ሌሎች ይኼንን ለሚከታተሉ የግል ባለሀብቶች፣ ‹‹እኛ የመንግሥት አካላት በመመርያ የተሰጠውን አናውቅም ስንል ምን ይሉናል?›› ብለዋል፡፡
ከመንግሥት አካል መልሶች ሲሰጥ ለሚማሩ አካላት ምሳሌ መሆን እንደሚገባቸው፣ ሌሎች በግንባታ ሥራ ላይ የተሳተፉት የመንግሥትም ሆነ የግል ባለሀብቶች ሕግና ደንብን ተከትለው እንዲሠሩ ሞዴል መሆን እንደሚያስፈልግ ወ/ሮ አራሬ አስታውቀዋል፡፡