Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናዩኒቨርሲቲዎች በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ መፈቀዱ ለትምህርት ተደራሽነትና ጥራት እንቅፋት እንዳይሆን ተሰግቷል

ዩኒቨርሲቲዎች በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ መፈቀዱ ለትምህርት ተደራሽነትና ጥራት እንቅፋት እንዳይሆን ተሰግቷል

ቀን:

  • በሦስት ዓመታት ውስጥ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ይሆናሉ ተብሏል

የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን ለማደራጀት እንዲረዳ ተዘጋጅቶ ለውይይት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ፣ ዩኒቨርሲቲዎቹ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ መደንገጉ፣ ተቋማቱ ከትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ይልቅ ወደ ገንዘብ ማካበት እንዳይሄዱ ሥጋት እንዳላቸው የፓርላማ አባላት አስታወቁ፡፡

ፓርላማው ከአንድ ሳምንት በፊት በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ረቂቁን ለዝርዝር ዕይታ ለሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል፡፡ ኮሚቴው በቢሾፍቱ ከተማ ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት፣ እንዲሁም ሰኞ ሚያዚያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በምክር ቤቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ከተወከሉ አስረጂዎች ጋር ምክክር አድርጓል፡፡

በምክር ቤቱ ከአስረጂዎች ጋር በነበረው ውይይት ዩኒቨርሲቲዎች በንግድና ኢንቨስትመንት ከመሰማራታቸው ባለፈ አንዱ የገቢ ምንጫቸው የተማሪዎቹ ክፍያ በመሆኑ፣ ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን ሲሉ ዋጋ ከፍ በማድረግ የዜጎችን የመማር መብት ሊጋፉ እንደሚችሉ በቋሚ ኮሚቴ አባላት በሥጋትነት ተመልክቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ውይይት አድርገው ለትምህርት ሚኒስቴር ባቀረቡት ጥያቄ፣ ዜጎች ከፍሎ ለመማር ባላቸው አቅም ውስንነት የተነሳ ትምህርት ውድ ሆኖ የማይታሰብ እንዳይሆን እንደሚፈራ፣ በዚህም የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ ሊያገኘው የሚችል ዕድል እንዳይሆን ሥጋት አለን ብለዋል፡፡

በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎች ወጪያቸውን ለመሸፈንና ገቢ ለማግኘት ከሚያደርጉት ጥረት ለትምህርት ሥራ የሚያደርጉት ጥረት እያነሰ እንዳይሄድ፣ በንግድና በኢንቨስትመንት የሚሠማሩበት ዘርፍ መለየት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በንግድ ዘርፍ የመሰማራት መብታቸው ተቋማቱን ከማኅበራዊ ተቋምነት ወደ ንግድ ኢንተርፕራይዝነት የማዘንበል ዓይነት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳያስገባቸው ጥንቃቄ ይደረግ ሲሉም አሳስበዋል፡፡

በረቂቅ አንቀጹ 36 የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች የገንዘብ ማግኛ ምንጮች ተዘርዝረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ረቂቁ ተቋማቱ የትምህርት ጥራትን ትተው ገንዘብ ወይም ገቢ ማሰባሰብ ላይ እንዲያተኩሩ ተደርጎ የተሠራ ስለመሆኑ ነው በአባላቱ የተገለጸው፡፡

በተመሳሳይ ከምክር ቤቱ የሕግ ክፍል የተጠናቀሩ ጥያቄዎችን ያቀረቡት አቶ አሰፋ ሻረው፣ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያቋቁሙት የንግድ ድርጅት እንዴት ወደ ሥራ እንደሚገባ ግልጽ አለመሆኑን አውስተዋል፡፡ በትምህርት ክፍያ ላይ ዩኒቨርሲቲው ዋጋ ሲወስን በመማር መብት ላይ ሊፈጥረው የሚችለው የፍትሐዊነት ጥያቄ እንዴት ይመለሳል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ማስተዋል መኮንን (ዶ/ር) የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል ባቀረቡት ጥያቄ፣ አዋጁ የትምህርት ተደራሽነትን ለማምጣት ክፍተት ያለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በርካታ ቁጥር ያለው የማኅበረሰቡ ከፍል ገንዘብ ከፍሎ ለመማር አቅም የሌለው መሆኑን አስረድተው፣ በዚህም የተነሳ ፍትሐዊነቱ እንዴት ሊረጋገጥ ይችላል ብለዋል፡፡

አቶ ታደሰ አባቡ የተባሉ የቋሚ ኮሚታ አባል ተማሪዎቹ ተወዳድረውና ገንዘብ ከፍለው ሲባል አገራዊ አቅምና ሁኔታው ይፈቅዳል ወይ በማለት ጠይቀዋል፡፡ አብዛኛው ማኅበረሰብ ከፍሎ የመማር አቅም ስለሌለው በዚህ የተነሳ ይህ ዩኒቨርሲቲ የሀብታም ዩኒቨርሲቲ አይሆንም ወይ በማለት ጠይቀዋል፡፡

በቢሾፍቱ በነበረው የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች በተሳተፉበት ውይይት ዩኒቨርሲቲዎች በንግድ ሕጉ መሠረት የራሳቸውን የንግድ ድርጅት የሚያቋቁሙ ቢሆንም፣ ዩኒቨርሲቲዎች ግን ከግብር ነፃ መሆን ካልቻልን ተመልሰን ወደ ኢኮኖሚያዊ ውድቀት ውስጥ እንገባለን የሚል ሥጋት ማቅረባቸውን አቶ ታደሰ አክለው ጠይቀዋል፡፡

ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትር ደኤታው ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፣ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ የመንግሥት ሀብት እንዴት እንደሚመደብላቸው የሚያብራራ በገንዘብ ሚኒስቴር አቅራቢነት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚፀድቅ ደንብ እንደሚኖር አስረድተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ ዋና ትኩረታቸው የገቢ ምንጭ ማሳደግና ነጋዴ መሆን ላይ እንዳያተኩሩ ሥርዓት ይበጅላቸዋል ብለዋል፡፡ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና በተልዕኮዋቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ሀብት የሚያስፍልጋቸው ቢሆንም፣ በሕግ አግባብና በተፈቀደው መንገድ ሥራ ላይ የሚያውሉት መሆን ስላለበት ሥርዓት ይበጅላቸዋል ብለዋል፡፡ ይህ የመንሥት ኃላፊነት በመሆኑ ተማሪዎችን ፈትነው ይቀበላሉ ሲባል ግን ከፍተኛ የመማር አቅም ያላቸው እንደሚሆን፣ ነገር ግን ከኅብረተሰቡ በበቂ ያልተወከሉትን በክፍያ ምክንያት እንዳይሆን መንግሥት በሚመደበው ሀብትና በሚዘረጋው ሥርዓት እንደሚቆጣጠር ሚኒስትር ደኤታው አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን ተማሪዎቹን ፈትኖ መቀበሉ የአካዳሚክ ነፃነት አንዱ አካል ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች የንግድ ድርጅት ሲያቋቁሙ ሌላ ነጋዴ መሥራት የሚችለውን ሳይሆን ከተልዕኮዋቸው ጋር የሚመጡና ተልዕኮዋቸውን የሚያጠናክሩና ከተልዕኮ ጋር የሚመጋገብ፣ ከተማሪም ከተመራማሪም የተገኘና ወደ ገበያ ሊወጣ የሚችል ሐሳብና ቴክኖሎጂ እንጂ ምግብ ለመሸጥ ወይም ቡቲክ ለመክፈት የሚፈቅድ አይደለም ብለዋል፡፡ በመሆኑም ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች የሚኖራቸው የገቢ ማመንጫ ድርጅቶች ቦርዱ በሚዘረጋው ሥርዓት እንደሚወሰን አስታውቀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ከፍለው መማር የሚችሉትን ተማሪዎቻቸውን ፈትነው ሲወስዱ፣ ከፍለው መማር የማይችሉትን ደግሞ መንግሥት በትምህርት ሚኒስቴር በኩል በሚመድበው በጀት ፍትሐዊነትን የሚያስተናግድ አሠራር እንደሚዘረጋና እየተዘጋጀ ባለው ደንብ ውስጥ ተቋማቱ ፍትሐዊነትን እንዲያስተናግዱ አስገዳጅና ማትጊያ ሁኔታዎች ስለመቀመጣቸው ገልጸዋል፡፡

ሳሙኤል (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲዎች ከታክስ ነፃ እንሁን ያሉትን ጥያቄ አስመልክተው ሲያብራሩ፣ ከግብር ነፃ እንሁን ማለት የንግድ ሕጉን ማፍረስ ስለሚሆን ብዙም ትርጉም አይሰጥም ብለዋል፡፡ በመሆኑም ተቋማቱ የሚመሠርቷቸው የንግድ ተቋማት በንግድ ሕጉ ይተዳደራሉ ማለት ተወዳዳሪ የሆነ የንግድ ድርጅት ይኖራቸዋል ማለት ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን ከግብር ነፃ ከሆነ ዓላማውን በመሳት ገበያውንም እንደሚያዛባ ገልጸው፣ ምክንያቱ ደግሞ አንዱ ከታክስ ነፃ ሌላው ታክስ እየከፈለ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ከሆነ ተወዳዳሪ መሆንም ፍትሐዊ የንግድ ተወዳዳሪነትም ሊያመጣ አይችልም ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ደኤታው በመጀመሪያው ምዕራፍ አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲን፣ በሁለተኛው ምዕራፍ ማለትም በቀጣዮቹ ሁለትና ሦስት ዓመታት ድግሞ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...