Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቁም እንስሳት ግብይትን ጨምሮ ሦስት ፖሊሲዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ሊደረጉ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ያልነበሩ ብሔራዊ የንግድ፣ የጥራትና የቁም እንሰሳት ዓብይት ሦስት ፖሊሲዎች በዚህ ዓመት ፀድቀው ተግባራዊ ዝግጅት መጠናቀቁን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከሦስቱ ፖሊሲዎች በተጨማሪም ብሔራዊ የውጭ ንግድ ፕሮሞሽን ስትራቴጂ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁን፣ የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኢትየጵያ ለ60 ዓመታት አገልግሎት ላይ የዋለውን የንግድ ሕግ በማሻሻልና አዳዲስ ድንጋጌዎችን በማካተት ከሁለት ዓመት በፊት አፅድቃ ሥራ ላይ አውላ የነበረ ቢሆንም፣ ለረዥም ጊዜ በዝግጅት ላይ የነበረው በአገሪቱ የመጀመሪያ የሚሆነው የንግድ ፖሊሲ ግን እስካሁን አልፀደቀም ነበር፡፡

እንደ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ አቶ እንዳለው መኰንን ገለጻ፣ በንግዱ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ጉዳዮችን ለመቅረፍ የተዘጋጀው ይህ ፖሊሲ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ካዘጋጃቸው ሌሎች ሕጎች ጋር አብሮ በዚህ ዓመት እስከ ሰኔ ወር ድረስ ማፀደቁን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከሌሎች የአገሪቱ ፖሊሲዎች ጋር ድግግሞሽ እንዳይኖር የሚመሳከሩ ሥራዎችን፣ እንዲሁም ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ከአገራዊ ዕቅዶች ጋር የማመሳከር ሥራዎች ተሠርተው መጠናቀቃቸውን የገለጹት አቶ እንዳለው፣ በተጨማሪም ከክልል ቢሮዎች ጋርና ከተጠሪ ተቋማት ሥራ አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ከጥራት መሠረተ ልማት ስትራቴጂ በስተቀር፣ አገራዊ የጥራት ፖሊሲ እንደሌለና የመሠረተ ልማት ተቋማትን ከማቋቋም ባለፈ እንደማይሠራ ሚኒስትር ደኤታው ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን የተዘጋጀው ፖሊሲ ተቋማትን ወደፊት ብዙ የሚወስዳቸውና እንደ አገር ረዘም ላለ ጊዜ ሊኖረን የሚገባውን የጥራት ግንባታ ምን መሆን እንዳለበት የሚያሳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ምርቶች ወደ ውጭ ከመላካቸው በፊት ጥራታቸውን የጠበቁ ለመሆናቸው በአገር ውስጥ ለመለካት የጥራት ፖሊሲው እንደሚጠቅም፣ እንዲሁም በምርት ተቀባይ አገሮች መሥፈርት መሠረት ምርቶች ተሟልተው እንዲላኩም እንደሚያዝ አቶ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ሦስተኛው ፖሊሲ የቁም እንስሳት ግብይት እንደሆነና ግብይቱም  ‹‹በጣም ችግር ያለበት›› በመሆኑና የቁም እንስሳት በሕገወጥ መንገድ ከአገር እየወጡ ለውጭ ገበያ ስለሚቀርቡ፣ ፖሊሲውን ማውጣት ካስፈለገበት ምክንያቶች አንደኛው ነው ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ሀብት እንዳላት አገር ተጠቃሚነቷ በአቅሟ ልክ እንዳልሆነ፣ ፖሊሲውም ከዋነኛ ጉዳዮቹ ውስጥ አድርጎ ከያዛቸው ዓላማዎች ይህንን ችግር መፍታት አስፈላጊ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በወጪ ንግድ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሌላው በዚህ ዓመት ተጠናቆና ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚደረግ የሚጠበቀው ብሔራዊ የወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ስትራቴጂ ነው፡፡

ስትራቴጂውም በሦስት ጉዳዮች ላይ በማጠንጠን የወጪ ንግዱን ዘርፍ እንደሚያስተካክለው እንደሚጠበቅ ሚኒስትር ደኤታው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የምርቶችን ስብጥር በማሳደግ የገበያ መዳረሻን ማስፋት፣ ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል ተቋማዊ ግንባታ ላይ መሥራት የሚያተኩርባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በሦስቱ ፖሊሲዎችና በስትራቴጂው ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ሲያካሂድ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች