ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የስድስት ግድቦችን ውኃ ተጠቅመው ክፍያ ባልፈጸሙ በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽንና በሳዑዲ ስታር እርሻ ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል የማኅበር ላይ ክስ ሊመሠርት መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ዓመታት ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ የግድቦች ውኃ ሲያቀርብላቸው ቢቆይም ስኳር ኮርፖሬሽን 2.8 ቢሊዮን ብር፣ ሳዑዲ ስታር ደግሞ 65.8 ሚሊዮን ብር ዕዳ እንዳልከፈሉ የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ አያሌው (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ለሸንኮራ አገዳ ልማት የተንዳሆ፣ የከሰም፣ የኩራዝ፣ የጣና በለስ፣ የወለንጪቲና የአልዌሮ ግድቦችን ውኃ ሲጠቀምበት እንደነበር ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
ንብረትነቱ የሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲ እንደሆነ የሚነገርለት የሳዑዲ ስታር እርሻ ልማት ድርጅት ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በጋምቤላ ክልል የሚገኘውን አልዌሮ ግድብን፣ የተለያዩ የእርሻ ምርቶች ለማልማት ሲጠቀምበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተደጋጋሚ ለድርጅቶቹ ክፍያውን እንዲፈጽሙ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ‹‹ውል የለንም›› በማለት እስካሁን እንዳልከፈሉና ለመክፈልም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ዮናስ (ኢንጂነር) ጠቁመዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑ የሕግ ክፍል በሕግ ለመጠየቅ ፍትሕ ሚኒስቴርን ትብብር የጠየቀ መሆኑን፣ በዚህም መሠረት ተገቢውን ክፍያ ለመጠየቅ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ድርጅቶቹ ውል እንዳልነበራቸው፣ ይሁንና ውል እንዲፈርሙ በተደጋጋሚ የመፈራረሚያ ሰነድ ቢልክላቸውም ፈቃደኛ እንዳልነበሩ አክለዋል፡፡ እንደ ዮናስ (ኢንጂነር) ገለጻ፣ ድርጅቶቹ የተጠቀሙትን የውኃ መጠን በማሳወቅ የተጠቀሰውን ገንዘብ ለመክፈል እንደሚገባቸው በማስረጃ እንደቀረበላቸው ተናግረዋል፡፡
ሳዑዲ ስታርም ‹‹ውል ሳይፈጸም የውኃ ተመን የምታወጡት ማን ስለሆናችሁ ነው›› በማለት ምላሽ መስጠቱን ገልጸው፣ የውኃ ተመን ማውጣት ያለበት ኮርፖሬሽኑ እንዳልሆነ በማስታወቅ ለኮርፖሬሽኑ ክፍያ መፈጸም እንደማይችል ምላሽ ሰጥቷል ብለዋል፡፡
የውኃ የዋጋ ተመን ያወጣው ኮርፖሬሽኑ ያቋቋመው ቦርድ መሆኑን፣ የመተመን ኃላፊነት ካለበት የቀድሞ ውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዋጋ ታሪፍ እንዲያወጡ ቢጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ሳይከፈል የቆየውን ዕዳ ኮርፖሬሽኑ በደብዳቤ በተደጋጋሚ ጠይቆ የተሰጠው ምላሽ ተገቢ ባለመሆኑ፣ በሕግ ለመጠየቅ መገደዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
የፓርላማው የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ከአንድ ወር በፊት ስኳር ኮርፖሬሽንና ሳዑዲ ስታር ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የተጠቀመበትን የውኃ ቢል አለመክፈላቸውን በኦዲት ሪፖርት ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት ከውኃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ዕዳ ያለባቸው ሁለቱ ተቋማት ኮርፖሬሽኑ በሁለት ወራት ውስጥ ገንዘቡን እንዲያስከፍላቸው ማሳሰቢያ መስጠቱም አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጂ ኮርፖሬሽኑ ለሁለቱ ተቋማት ክፍያውን እንዲፈጽሙ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን፣ በዚህም ምክንያት በሕግ ለመጠየቅ በሒደት ላይ እንደሆነ ዮናስ (ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡