Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያ አዲስ የዓይነት ግብይት አገልግሎት ሊጀምር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከመደበኛው የምርት ግብይት (Spot Trade) በተጨማሪ፣ ወደፊት የሚፈጸም ግብይት (Forward Trade) የሚባል አዲስ ዓይነት ግብይት ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡

አዲሱ የግብይት ሥርዓት ገዥና ሻጮች ቀድመው ውል ፈጽመው፣ በውሉ መሠረት ተፈላጊው ምርት ሲደርስ ግብይታቸውን መፈጸም የሚችሉበት አሠራር ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቺፍ ማርኬቲንግ ኦፊሰር አቶ በረከት መሠረት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ እስካሁን ድረስ በምርት ገበያ በኩል ወዲያውኑ ግብይት በመፈጸም ሻጭን ከገዥ በማገናኘት ግብይቶች ያከናውኑ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ምርቶች በስፋት እየተመረቱ በመሆናቸው ወደፊት የሚፈጸም ግብይት (Forward Trade) ለመጀመር ምርት ገበያው በዝግጅት ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከምርት ገበያ ውጪ የሚፈጸሙ ግብይቶች ላይ ገዥዎች ቀድመው ገንዘብ ከሰጡ በኋላ ምርቱን ያለማግኘት፣ እንዲሁም ሻጮች ምርቱን ለመሸጥ ከተስማሙ በኋላ በወቅቱ ክፍያ ያለማግኘት ችግሮች በምርት ሰንሰለት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮች መሆናቸው፣ ከዚህ ቀደም በተደረገ ጥናት እንደተለየ አቶ በረከት አስረድተዋል፡፡

ይህንን ክፍያ ያለመፈጸም (ዲፎልት) ችግር ለማስቀረት፣ ምርት ገበያው ከመደበኛው የምርት ግብይት (Spot Trade) በተጨማሪ፣ ራሱን የቻለ የፀና ውል በመዋዋል የሕግ ተፈጻሚነትና አስገዳጅነት ያለው ወደፊት የሚፈጸም ግብይት እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡

 አሠራሩ ውል ያለመፈጸም ችግር (Default Risk) ከማስወገድ በተጨማሪ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ መዋዥቆችን ቀድሞ ለመገመትና የሚመጡ ችግሮችን ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን አቶ በረከት አክለዋል፡፡

በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ምርት በመኖሩ አዲሱ የውል ግብይት፣ ለመነሻ እስከ ሦስት ወራት የሚደርሱ የውል ግብይቶችን በማዋዋል ለመጀመር ታስቧል ተብሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለው በአብዛኛው የመኸር ወቅት ምርት ከመሆኑ፣ ከስድስት ወራትና ከዚያ በላይ ጊዜ ስለሚያስፈልግ በቀጣይ እስከ አንድ ዓመት ሊቆዩ የሚችሉ ውሎችን ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

ወደፊት የሚፈጸም ግብይት በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ እንደሚውል የተገለጸ ሲሆን፣ ከሚተገበሩት አማራጮች ውስጥ አንደኛ ገዥና ሻጭ ምርትና ገንዘባቸውን ወደ ምርት ገበያ መጋዘንና የክፍያ መፈጸሚያ ቋት ውስጥ ካስገቡ በኋላ ግብይት የሚፈጽሙበት አሠራር ነው ተብሏል፡፡

ሁለተኛው ምርት ወደ ምርት ገበያ ሳይመጣ ግብይት የሚፈጸምበት ሁኔታ ካለ ክፍያ ያለመፈጸም ችግር እንዳይኖር ማስያዣ (Margin) የሚባል አሠራር ስላለ፣ ገዥው በገንዘብ ሻጭ በምርት ወይም ለዚያ ምርት አቻ በሚሆን በወቅቱ በሚኖር የገበያ ዋጋ የተቀየረ ገንዘብ አስይዘው ግብይት የሚፈጸሙበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

 በዚህ ሒደት ሁለቱ አካላት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ክፍያ የሚፈጸሙ ከሆነ፣ በማስያዣ የሚያስይዙት ገንዘብ ላይ ዕርምጃ ስለሚወሰድ የግብይት አሠራር ትልቅ ጥቅም ይሰጣል ተብሏል፡፡ 

በሙከራ ደረጃ በሚጀመረው አዲስ የግብይት ዓይነት ከ20 በላይ በሆኑ ምርቶች ለማስጀመር ሲታቀድ ከቡና ጀምሮ ጥራጥሬዎች፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች ከዚህ ውስጥ ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

ለአብነት አኩሪ አተር በተያዘው ዓመት በብዛት ቢመረትም ነገር ግን በቂ የሆነ የግዥ ፍላጎት ባለመኖሩ ክፍተቶች እንዳጋጠሙ በመጥቀስ፣ እነዚህን ክፍተቶች ቀድሞ የግብይት ውሳኔ ቢደረግ (Customize Forward Trade) በገዥና በሻጭ መካከል ከፍተኛ ትስስር በመፍጠር ችግሩን ማቃለል ይቻል እንደነበር አቶ በረከት ገልጸዋል፡፡

ወደፊት የሚፈጸም ግብይት ሥርዓት የሚመለከተው መመርያ አስፈላጊውን ሒደት አልፎና ፀድቆ ወደ ምርት ገበያ ስለተላከ፣ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ የሚገኘውን ዝግጅት በማጠናቀቅ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች