Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከውጭው ገበያ ባልተለየ የሚነገድበት የኤግዚቢሽን ገበያ

ከውጭው ገበያ ባልተለየ የሚነገድበት የኤግዚቢሽን ገበያ

ቀን:

በኢትዮጵያ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማርገብ መንግሥት ከሚያቀርባቸው አማራጮች መካከል የእሑድ ገበያና በዓል በመጣ ቁጥር የሚዘጋጁ የጎዳና ላይ ኤግዚቢሽኖች ይገኙበታል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎችም ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻውን በትላልቅ የኤግዚቢሽን አዳራሾች በተለያዩ ጊዜያት ያቀርባሉ፡፡

በተለይ ከፋብሪካና ከአርሶ አደሮች የሚገኙ ምርቶችን ሸማቾች በቀጥታ እንደ ልባቸው እንዲገበያዩ የሚያደረገው በበዓላት ወቅት በሚዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች ነው፡፡ ይሁን እንጂ በእንዲህ ዓይነት መልኩ በሚዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች ጭምር በምግብ ነክም ሆነ በሌሎች ግብዓቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ይታያል፡፡

‹‹ዩቶፕያ የፋሲጋ ኤክስፖ›› በሚል ስያሜ ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚሌኒየም አዳራሽ እንዲሁም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እየተካሄደ ያለውን የፋሲካ በዓል ኤግዚቢሽን ሪፖርተር ቃኝቷል፡፡

በሚሌኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ባለው ኤግዚቢሽን  የተሳተፉት የመርካቶ ሸማቾች ማኅበር ጤፍ፣ ዘይት፣ መኮሮኒ፣ ፓስታ፣ ቡና፣ ላርጎ፣ ዱቄትና ሌሎች የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶችን ይዘው ቀርበዋል፡፡

የማኅበሩ የሒሳብ ሠራተኛ ወጣት ቃልአብ ደረጄ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዝያ 7 ቀን በሚሌኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ባለው ኤግዚቢሽን ማኅበሩ ለሸማቾች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ነው፡፡

ማኅበሩ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት በሚካሄዱ ኤግዚቢሽኖች የተሳተፈ ሲሆን፣ በሚሌኒየም አዳራሽም ለመጀመርያ ጊዜ መሳተፋቸውን ወጣት ቃልአብ አስረድቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተሳተፉት ኤግዚቢሽን ላይ ነጭ ጤፍ በኪሎ 75.00 ብር፣ አምስት ሊትር ዘይት በ960 ብር፣ ዋንጋሪ የተሰኘ ዱቄት በኪሎ 70 ብር፣ አተር በኪሎ 98 ብር፣ ቡና በኪሎ 340 ብር፣ መኮሮኒ በኪሎ 85 ብር፣ ሩዝ በኪሎ 65 ብር፣ የባልትና በርበሬ በኪሎ 320 ብርና ሌሎች ምርቶችን እየሸጡ መሆኑን ለሪፖርተር አብራርቷል፡፡

የኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከተከፈተ ጊዜ ጀምሮ አብዛኛው ሸማቾች እየተገበያዩ አለመሆኑን፣ ከዚህ በፊትም በተሳተፉባቸው ኤግዚቢሽን ላይ እንዲህ ዓይነት ችግር አይተው እንደማያውቁ ወጣቱ ያስረዳል፡፡  

በሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሄደው ኤግቢዚሽን የተሳተፉት አብዛኛው ነጋዴዎች የተመቻቸ የቦታ ይዞታ ቢያገኙም፣ ሸማቾች ግን በብዛት ገብተው የተለያዩ ምርቶችን ባለመሸመታቸው የተነሳ እሱን ጨምሮ ሌሎች ነጋዴዎች እያማረሩ እንደሆነ ይናገራል፡፡

በተመሳሳይ ከደቡብ ክልል ከሃላባ መንቼኖ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ደረጃ አንድ የሆነ የሃላባ ዛላ በርበሬን ለመሸጥ በኤግዚቢሽኑ የተገኙት አቶ መሐመድ ሁሴን ናቸው፡፡

ከዚህ በፊ በኤግዚቢሽን ማዕከል ተሳትፈው የተለያዩ ምርቶችን መሸጣቸውን የሚያስታውሱት አቶ መሐመድ፣ በዘንድሮ ኤግዚቢሽን ላይ ደረጃውን የጠበቀ ዛላ በርበሬ ለሸማቾች ለመሸጥ አሥር ጆንያ ይዘው መቅረባቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አንድ ኪሎ በርበሬ በ280 ብር እየተሸጠ መሆኑን፣ ከውጭ ዋጋ ጋር ሲነፃፀርም የ30 ብር ልዩነት እንዳለው አክለው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት የያዙዋቸውን ምርቶች በፍጥነት ሸጠው በድጋሚ እንደሚያመጡ፣ ዘንድሮ ግን የኑሮ ውድነቱ እንዳለ ሆኖ፣ በመገናኛ ብዙኃን በኩል ማኅበረሰቡ ጆሮ ባለመድረሱ የተነሳ አብዛኛው ሸማቾች እየተገበያዩ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ በርካታ ዜጎችን ማማረሩን በመግለጽም፣ ማኅበረሰቡ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የወር አስቤዛውን መሸመት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በዓል ሲደርስ ሸማቾች የፈለጉትን ግብዓት የሚያገኙት እንዲህ ዓይነት ቦታዎች ላይ እንደሆነ፣ ከዚህ በፊትም ከተሳተፉት የኤግዚቢሽን ማዕከል አንፃር አሁን ያሉበት ምቹ መሆኑን አቶ መሐመድ ተናግረዋል፡፡

በኤግዚቢሽኑ ከከፋ ሁለገብ ዩኒየን የተሳተፉት አቶ ክፍሌ ኃይለ ጊዮርጊስ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት እንዲህ ዓይነት ኤግቢዚሽን ያስፈልጋል፡፡

በኤግዚቢሽኑም የጫካ ማር፣ ቡናና ኮረሪማ ይዘው መቅረባቸውን፣ ነገር ግን ኤግዚቢሽኑ ከተከፈተ ጊዜ ጀምሮ የሚሸምቱ ሰዎች የውኃ ሽታ እንደሆኑባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከውጭ የገበያ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑንና አንደኛ ደረጃ የከፋ ቡና በኪሎ በ350 ብር፣ ማር 400 ብርና ኮረሪማ በኪሎ 250 ብር እየተሸጠ ነው ብለዋል፡፡

በኤግዚቢሽኑ በርካታ ነጋዴዎች መሳተፋቸውን፣ ነገር ግን የወቅቱን ሁኔታ ጨምሮ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከዚህ በፊት ተሳትፈው ከነበሩበት አንጻር ይህ ቀዝቀዝ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት በኤግዚቢሽን ማዕከል ይሳተፉ እንደነበር ገልጸው፣ ዘንድሮ ግን በሚሌኒየም አዳራሽ ለመጀመርያ ጊዜ ከመሳተፋቸው የተነሳ የያዙትን ዕቃ ሳይጨርሱ እንዳይመለሱ ሥጋት እንደያዛቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሄደው ኤግዚቢሽን አንድ ኪሎ ነጭ ጤፍ ከ73  እስከ 75 ብር፣ ቡና በኪሎ ከ350 እስከ 360 ብር፣ ላርጎ አንድ ሊትር ከ90 እስከ 100 ብር፣ አምስት ሊትር ዘይት 860 እስከ 895 ብር፣ ዱቄት ከ70 እስከ 73 ብር፣ የተቆላ ቡና በኪሎ 355 ብር፣ ቅቤ በኪሎ 430 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ ሸማቾች እንደገለጹት፣ አብዛኛው የምግብ ነክ ግብይቶችም ሆኑ ሸቀጣ ሸቀጦች ውጪ ካለው ዋጋ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

በተለይ እንዲህ ዓይነት ኤግዚቢሽኖች ሲዘጋጁ ታሳቢነቱ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እንደሆነ የሚናገሩት እኚህ ሸማቾች፣ መንግሥት በዚህ መልኩ የሚዘጋጁ ነገሮችን በመፈተሽ የኑሮ ውድነትን ማስቀረት ይኖርበታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ለመግቢያ ተከፍሎ ከውጪ ጋር የዋጋ ልዩነት ከሌለው ትርፉ ወጪ መሆኑን፣ ከዚህ በፊትም በነበሩ ኤግዚቢሽኖች እንዲሁ ዓይነት ተመሳሳይ ነገሮችን ማየታቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ የበዓል ወቅቶች በሚዘጋጁ ኤግዚቢሽኖች ምርቶች በአንድ ቦታ እንደሚገኙና ማኅበረሰቡ የፈለገውን መርጦ በመግዛት ተጠቃሚ እንደሚሆን ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል በኤግዚቢሽን ማዕከል ሪፖርተር ባደረገው ቅኝት፣ አገር ውስጥ የተመረተ አምስት ሊትር የአኩሪ አተር ዘይት 800 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

በኤግዚቢሽን ማዕከሉም በርካታ ቁጥር ያላቸው ነጋዴዎች መሳተፋቸውን፣ ነገር ግን ኤግዚቢሽኑ ከተከፈተ ጀምሮ እንደሌላው ጊዜ ብዙም ሸማቾች ከእየገቡ አለመሆኑን አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ነጋዴ ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

የቤት ዕቃዎች፣ ሶፋ፣ አልባሳት፣ ሸቀጣ ሸቀጦች፣ ለምግብነት የሚውሉ ግብዓቶች፣ ሌሎች ቁሳቁሶች ይዘው የቀረቡ ነጋዴዎች ቁጥር በሚሌኒየም አዳራሽ ከተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ጋር ሰፊ ልዩነት እንዳለው ሪፖርተር በቦታው ሆኖ ለመመልከት ችሏል፡፡

ከአሥር ቀናት በላይ ክፍት የሆነው የኤግዚቢሽን ማዕከል ውስጥ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ዘይትና ሌሎች ምርቶች ብዙም እንዳልገቡ፣ ነገር ግን የቤት ዕቃዎችና አልባሳት በብዛት መኖራቸውን መመልከት ችለናል፡፡

በሚሌኒየም አዳራሽ ለተከታታይ 15 ቀናት በሚቆየው ዩቶፕያ የፋሲካ ባዛር ከገበያ በተጨማሪ፣ ብራይዳል ሾው፣ የሥራ ፈጣሪዎች ኮርነር፣ የመጀመርያው የዳይኖሰር ጁራሲክ ትዕይንት፣ የልጆች ማቆያና የጨዋታ ቦታ እንዲሁም የንግዱ ማኅበረሰብ የሚሳተፍበት ዓውደ ጥናት የሚቀርብ መሆኑ ተገልጿል፡፡    

በሌላ በኩል ሪፖርተር በተለያዩ ሱቆች ላይ ተዘዋውሮ እንደተመለከተው፣ አምስት ሊትር ዘይት 900 እስከ 950  ብር፣ ዱቄት በኪሎ ከ75  እስከ 80  ብር፣ ነጭ ጤፍ በኪሎ ከ79  እስከ 80  ብር፣ መኮሮኒ በኪሎ ከ80  እስከ 85  ብር፣ ፓስታ ከ65  እስከ 70  ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

ከዚህ በፊት ከየካቲት 2 እስከ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ‹‹የኅብረት ሥራ ግብይት ለሰላምና ለተረጋጋ ገበያ›› በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የነበረው ኤግዚቢሽን ባዛርና ሲምፖዚየም በተከፈተ ማግሥት በዘይትና በተለያዩ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ዓምና ተከፍቶ በነበረው ኤግዚቢሽንና ባዛር ጤፍ፣ ዘይት፣ ማር፣ ቡና፣ በርበሬ፣ ቡላ፣ ቅቤ፣ ቅመማ ቅመም፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ሌሎች ምርቶች ለሸማቹ ማኅበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ የቀረቡ ቢሆንም፣ በዓምናው ሸመታ በአምስት ሊትር ዘይት ላይ የ60 ብር ጭማሪ ከመታየቱም በላይ በሌሎች ምርቶች ላይ ጭማሪ እንዳጋጠማቸው ሸማቾች ለሪፖርተር መናገራቸው ይታወሳል፡፡  

ዘንድሮ ደግሞ ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና አርሶ አደሮች የሚሳተፉበት ኤግዚቢሽን እንደ ከዚህ ቀደሙ በወርኃ የካቲት አልተካሄደም፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...