በአበበ ፍቅር
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን አልጋ ወራሽ ይባሉ ከነበሩበት ከ1915 ዓመት ጀምሮ፣ የሕክምና አገልግሎትን ቤተ ሳይዳ በሚል ስያሜ የጀመረው የአሁኑ የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ነው፡፡ የዘውድ ሥርዓቱ በ1967 ዓ.ም. ሲያከትም የሆስፒታሉ ስም ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ የካቲት 12 ተቀይሯል፡፡
የሆስፒታሉ መሥራች ዓይነር የተባለ ስዊድናዊ ዜግነት ያለው ሐኪም ሲሆን ከተቋቋመበት ከ100 ዓመት በፊት ጀምሮ እስከ 1928 ዓ.ም. በሜዲካል ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡
የያኔው ቤተ ሳይዳ የአሁኑ የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የመጀመርያ ስያሜውን ያገኘው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡ ወደ ሥራ ሲገባም ከ25 የማይበልጡ አልጋዎች እንደነበሩት ይነገራል፡፡
በ1928 ዓ.ም. የጣሊያን ወረራ ጊዜ ተቋሙ ከደረሰበት ጥቃት አንዱ የቀድሞ ስሙንና ይዘቱን መቀየሩ ነበር፡፡ በወቅቱ አዲስ ሕንፃን በማስገንባት ባቶሪያ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በጀግኖች አርበኞች ወራሪ ኃይል ከአገር ሲባረር የእንግሊዝ ቀይ መስቀል ማኅበር ሆስፒታሉን በመረከብ 140 አልጋዎችን በማስገባት እስረኞችን ለማከም ይጠቀምበት ነበር፡፡
ሆስፒታሉ ከእንግሊዝ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመሆን ዘመናዊ የነርሲንግ ትምህርት ቤት በመክፈትና በርካታ ባለሙያዎችን ያፈራ ለዘመናዊ ትምህርት አሰጣጥ መሠረት የጣለ ተቋም ነው፡፡
እስከ 1947 በእንግሊዝ ቀይ መስቀል ሥር ሆኖ ሲተዳደር ከቆየ በኋላ እንደገና በቻርተር እንዲቋቋም ተደርጎ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሥር እንዲተዳደር ተደርጎ፣ አገልግሎቱ የንጉሥ አስተዳደር እስከተለወጠበት ድረስ ቆይቷል፡፡
በየዘመኑ ስያሜው እየተለዋወጠ የመጣው ተቋሙ በ1967 ዓ.ም. የካቲት 12 ሆስፒታል በመባል እስከ 2003 ዓ.ም. ሲጠራበት ቆይቶ፣ በአገሪቱ የታየውን የሐኪሞች እጥረት ለመቀነስ የከተማ አስተዳደሩ በአዋጅ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ እንዳደገና በመዲናዋ ሥር ከሚገኙ ስድስት የመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ ትምህርት የሚሰጥ ብቸኛ ተቋም ለመባል እንዳስቻለው የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ኤልያስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የሕክምና ሥልጠና ማዕከል ተብሎ በአዋጅ ከተቋቋመ በኋላ በአገሪቱ የሚከሰተውን ከፍተኛ የሆነ የጤና ባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ ተሳታፊ በመሆን አዲስ በተዘረጋው የሕክምና ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ላለፉት 13 ዓመታት በሕክምና ዶክተርነት ከ400 በላይ ጠቅላላ ሐኪሞችን በስድስት ዙር ማስመረቁን ባለፈው ሳምንት ተቋሙ መቶኛ ዓመቱን ባከበረበት ወቅት ተነግሯል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከ200 በላይ የሚሆኑ የኅብረተሰብ የጤና ባለሙያዎችን በሁለት ዙር ማስመረቁን ተቋሙ አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ 130 ስፔሻሊስትና 70 ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪሞች፣ 180 ጠቅላላ ሐኪሞች፣ 61 የኅብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች፣ ከ250 በላይ ነርሶችና 59 የፋርማሲ ባለሙያዎች ያሉት ሲሆን፣ ተቋሙ በ350 የአስተዳደር ሠራተኞች እንደሚመራ ኤልያስ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡
ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለኅብረተሰቡ በአስተኝቶ ሕክምና፣ በተመላላሽ እንዲሁም በድንገተኛ ሕክምናና በበርካታ ዘርፎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የተናገሩት ኤልያስ (ዶ/ር)፣ የውስጥ ደዌ የቀዶ ሕክምና፣ የአጥንት ቀዶ ሕክምና፣ የጉበትና ሐሞት ቀዶ ሕክምና፣ የአንጎልና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ሕክምና እንዲሁም የነርቭ ሕክምናና ለሌሎችም በርካታ ሕመሞች የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው ብለዋል፡፡
በመድኃኒትና ተያያዥ ግብዓቶችንም ልዩ ትኩረት በመስጠት የአቅርቦት መጠኑ 86 በመቶ እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡ ላለፉት ስድስት ወራት ለ137 ሺሕ ሰዎች የተመላላሽ የሕክምና አገልግሎት የሰጠ ሲሆን፣ ለ19 ሺሕ ሕሙማን በድንገተኛ ሕክምና እንዲሁም 13,762 አስተኝቶ ሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን የተናገሩት መረርቱ ተመስገን (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ለስድስት ሺሕ ታማሚዎች የቀዶ ሕክምና መስጠቱንና አምስት ሺሕ እናቶች በተቋሙ በሰላም መውለዳቸውን መረርቱ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚታወቅበት የቃጠሎ ሕክምና 2,919 ሕሙማንን ያገለገለ ሲሆን፣ በከንፈርና ላንቃ ክፍተት ላለባቸው ሕሙማን የቀዶ ሕክምና አገልግሎት፣ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የንግግር ችግር ላለባቸው 1,076 ሕሙማን የንግግር ሕክምና አግኝተው የተግባቦት ክህሎታቸው እንዲያድግ ማድረጉን መረርቱ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት የሕሙማን ቁጥር እየጨመረ ለመጣው የካንሰር በሽታን ለመቀነስ ተቋሙ የሕክምና አገልግሎት የጀመረ ሲሆን፣ የተቋሙ ስፔሻሊስት ሐኪሞች በተመረጡ ጤና ጣቢያዎች በቋሚነት አገልግሎት እየሰጠ ነው ተብሏል፡፡
የመቶኛ ዓመት ክብረ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሰጡ ኃይል እጥረት ያለባቸውን የጤና ሙያዎች በመለየት አዳዲስ የጤና ትምህርት ፕሮግራሞችን በመክፈት ወደ ጤና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለማሸጋገር አስፈላጊውን ዝግጅት እያገባደዱ እንደሆነ የሜዲካል ኮሌጁ አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሮቮስት የሆኑት አቶ ዓለሙ ክብረት ተናግረዋል፡፡
በሆስፒታሉ መቶ ዓመት ያስቆጠሩ የመመገቢያ ዕቃዎች ሌሎች ታሪካዊ የሆኑ መገልገያዎች በቅርስነት ተጠብቀው እንደሚገኙ አቶ ዓለሙ ተናግረዋል፡፡