በአበበ ፍቅር
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ለውጭ አገርም ሆነ ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች የተሟላና ምቹ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ተባለ፡፡
የከተማዋና ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ‹‹ዲስከቨር አዲስ አበባ›› የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያና የከተማዋን የቱሪዝም ብራንድ ለማስተዋወቅ መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው መድረክ ተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡
አዲስ አበባ ዕድሜ ጠገብ ከተማ እንደመሆኗ በውስጧ አምቃ የያዘቻቸው ባህል ወግና ልዩ ልዩ ቅርሶች ለውጭ አገርም ሆነ የአገር ውስጥ ጎብኝዎችን በሚስብ መልኩ ተዘጋጅተውና ተሰባስበው ለዕይታ እየበቁ አይደለም ተብሏል፡፡
የከተማዋን ጥንታዊነትና የቀድሞ ማንነቷን የሚያሳዩ የቤት አሠራሮች ባህላዊ አልባሳትና ምግቦች ሲደበዝዙ፣ ሲጠፉና ሲፈርሱ የሚመለከተው አካል ቸል ሊል አይገባም ብለዋል፡፡
‹‹የወጣቱን መንፈስ የሚያረጋጉ የኪነ ጥበብ መድረኮችን ከማዘጋጀት ይልቅ፣ ትልልቅ መንግሥታዊ ድግሶችን በመደገስ ስህተቶችን ለመሸፈን የሚደረገው እንቅስቃሴ ሊቆም ይገባል፡፡ በአንፃሩ ሁሉንም ማኅበረሰብ በአንድ ቋንቋ ሊያግባባ የሚችል መድረክ ሊፈጠር ይገባል፤›› ያሉት የመድረኩ ተሳታፊ ናቸው፡፡
በየመንገድ ዳሩ የሚተከሉና የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች በተገቢ ቦታ በባለሙያ ተጠንተው ባለመተከላቸው የከተማዋን ገጽታ እያበላሹ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
በሌላ በኩል ቅርሶች ተገቢውን እንክብካቤ ሳይደረግላቸው ሲቀር አልያም በዕድሜ ብዛትና በተለያዩ ምክንያቶች ሲፈርሱና ይዘታቸውን ሲቀይሩ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ በአግባቡና በወቅቱ ጥገና አለማድረግ እንዲሁም፣ “ለልማት” በሚል ሰበብ ከመፍረሳቸው ባሻገር ካጠገባቸው በሚሠሩ ትልልቅ ሕንፃዎች ተከልለው ለዓይን ሲሰወሩ እየተመለከትን ነው፣ ሲሉ አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግረዋል፡፡
በተለይ የውጭ አገር ጎብኝዎች ሲመጡ ከሚቸገሩባቸው ሁኔታዎች መካከል የተሟላ ሽንት ቤት አለማግኘት አንዱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ቱሪስቶች ደኅንነት ተሰምቷቸው በአግባቡ ከተማዋን እንዲመለከቱና የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የራሱ የሆነና በዘርፉ የሠለጠኑ የደኅንነት ፖሊስ ቢቋቋም የተሻለ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
እነዚህንና ከዘርፉ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በተለይ ደግሞ ከሰሜኑ ጦርነትና ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ በከተማዋ በእጅጉ የቀነሰውንና የተቀዛቀዘውን የከተማዋን የጎብኝዎች ቁጥር ከፍ ለማድረግ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ የተናገሩት የዲስከቨር አዲስ አበባ ፕሮሞሽን ፕሮጀክት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ አዚዝ ይማም ናቸው፡፡
ፕሮጀክቱ የቱሪዝሙን ፍሰት ለማሳለጥ ብሎም የሚታዩትን ችግሮች በመቅረፍ የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝምን ለማሳደግ የተጠነሰሰ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
‹‹ዲስከቨር አዲስ አበባ›› በዋናነት ቱሪስቶች በአገራቸው ሆነው በእጅ ስልካቸው የአየር ትኬትን መቁረጥ እንዲችሉ ወደ ከተማም ከመጡ በኋላ የሚያርፉበትን ሆቴልና በአጠቃላይ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ‹‹በዲስከቨር አዲስ አበባ›› የሞባይል መተግበሪያ ታግዘው ማግኘት እንዲችሉ ተደርጎ እንደተዘጋጀ አቶ አዚዝ ተናግረዋል፡፡