የዩኤስ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ከባለቤታቸው የአሜሪካ ሁለተኛ አባወራ ዳግላስ ኤምሆፍ ጋር ባለፈው ሳምንት በጋና ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ከጎበኟቸው አንዱ በዩኔስኮ የተመዘገበ ታሪካዊ የቤተ መንግሥት ሕንፃ ያለበት የኬፕ ኮስት ከተማ ነው፡፡ አገረ ገዥው ዳግማዊ ኦሳባሪማ ክዌሲ አታ፣ በኬፕ ኮስት በሚገኘው ኤሚንትሲማድዘ ቤተ መንግሥት የክብር አቀባበል አድርገውላቸው በጋና የከፍተኛ ክብር ምልክት የሆነውን ባህላዊውን የኬንቴ አልባሳት ለጥንዶቹ አበርክተዋል፡፡
ጋና ኒውስ እንደዘገበው፣ በሕብረ ቀለማት ያሸበረቁት አልባሳቱ እያንዳንዳቸው ተምሳሌታዊ ፍቺ አላቸው፡፡ ወርቃማው ኩነትን /መረጋጋትን፣ ቢጫው ፍሬያማነትን/ መውለድን፤ አረንጓዴው መታደስን፣ ሰማያዊው ንፁህ መንፈስን/ መስማማትን፣ እንዲሁም ቀይና ጥቁር በቅደም ተከተል ፍቅርና አክብሮትን፣ ከቀደምት ትውልዶች አበው ጋር በመንፈሳዊ ግንዛቤ መተሳሰርን የሚያመለክት ነው።