አስተሳሰብህ የማንነትህ ወፍጮ ነው፤ ወደ ሐሳብህ የምታስገባው ነገር ሁሉ በውስጥህ በሒደት አልፎና ተፈጭቶ ተግባር ሆኖ ይወጣል፤ ተግባሩም ሲደጋገም ልማድ ይባላል፡፡ አንድ ሰው ደጋግሞ ሲያደርግ ከሚታየው ነገር ውጪ ሌላ ምን ማንነት አለው? በአጭሩ አንድ የአስተሳሰብህ ውጤት ነህ፡፡ በሸተኝነትን እያሰብክ ጤናማ መሆን አትችልም፡፡ ብቸኝነትን እያስላሰልክ ባለወዳጅ ልትሆን አትችልም፡፡ የድህነት አመለካከት ተቆጣጥሮህ ባለጠጋነት የማይታሰብ ነው፡፡ አወንታዊዎቹን ሐሳቦች ስላስተናገድክ ብቻ የጠበቅከውን ነገር ታገኛለህ ማለት ሳይሆን፣ አሉታዊው ወይም ጨለምተኛው አመለካከት መልካም ነገር ፊትህ ቢመጣ እንኳ እንዳታየው ስለሚጋርድህ ነው፡፡
በብዙ መልኩ ተሞክሮ እምቢ ያለ ማንነትህ አንተው አስበህበትና ወስነህ እንዲለመድ ስታደርገው ብቻ ነው ወደ እሺታ የሚመጣውና በአስተሳሰብህ ላይ አቋም ውሰድ፡፡ ለማይረበ ነገር እምቢ ማለትንና ለመልካም ነገር እሺታን የምትለምደው ያንን ለመልመድ አቋም ስትይዝና ያንን ማሰላስል ስትጀምር ብቻ ነው፡፡ በሌላ አባባል አንተነትህ ብቻ ነው እሺ የሚለውና እዘዘው!!!
የአንድ ወር የቤት ሥራ ለአንባቢዬ እንድሰጥ ይፈቀድልኝ፡፡ ራስን ለማስለመድ የማትፈልገውንና ምናልባት ከዚህ በፊት ይሳካል ብለህ ያሰብከውን ነገር ለአንድ ወር እንድትለማመደው ላደፋፍርህ፡፡ ለመንደርደሪያ ያህል የሚከተሉትን ልምምዶች ልሰንዝር፡፡
- አንድ ወር- ከመኝታህ መነሳት በማትችልበት የማለዳ ሰዓት ተነሳና አንድን ነገር ተግባር፣ አንብብ፣ አስፈላጊ ከመሰለህ ስፖርት ሥራ፡፡
- ለአንድ ወር- ሳትበላ ወይም ሳትጠጣ ማለፍ የማትችለውን እንደሱስ የሆነ የምግብ ወይም የመጠጥ ዓይነት ሳትቀምስ እለፍ፡፡
- ለአንድ ወር- ለጤንነት አስጊ ይሆናል ብለህ የምታስበውን ወይም በሐኪም የተነገረህን የምግብ ዓይነትና መጠን ቀንስ፡፡
- ለአንድ ወር- ያህል በሕይወትህ ያለውን ጤና ቢስ ነው ብለህ የምታስበውን ልማድ ላለማድረግ ተጋደል፡፡
- ለአንድ ወር- በቀን የአንድ መጽሐፍ ቢያንስ 10 ገጽ አንብብ፡፡
- ለአንድ ወር- በየቀኑ ማታ ወደ ቤትህ ስትገባ በኪስህ የተረፈህን ሳንቲም አጠራቅምና መጨረሻ ስንት እንደሚሆን ተመልከት፡፡
- ለአንድ ወር- ከቀጠሮህ 10 ደቂቃ ቀደም እያልክ ተገኝ፡፡
- ለአንድ ወር- ለሥራህ፣ ለዓላማህ፣ ለቤተሰብህ ወይም ለጤናህ ጠንቅ ከሆነ ዓይነት ሰው ተለይ፡፡
- ኢዮብ ማሞ (ዶር.) ‹‹አመራር A to Z›› (2003)