ታላቁ ህዳሴ ግድብ የተጀመረበት ቀን ዓመት ቆጥሮ ሲመጣ የግብፅ ፖለቲከኞች እንደተለመደው ጩኸታቸው ጎላ ብሎ ይሰማል፡፡ ዘንድሮ መጋቢት 24 ቀን የግድቡ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት 12ኛ ዓመት ሲታሰብም፣ እንደተጠበቀው የግብፅ ፖለቲከኞች ጩኸት ጎልቶ ሲሰማ ነው የከረመው፡፡ ታላቁ ህዳሴ ግድብን ግብፆች ቢቻል ለማስቆም ካልተቻለም ለማስተጓጎል ብዙ ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ያደረጓቸው ጥረቶች ሳይሳኩ እንደቀሩት ሁሉ፣ አሁን የግድቡ ግንባታ 90 በመቶ በደረሰበት ወቅት ጥረታቸው ይሳካል ብሎ መገመት ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ ይሁን እንጂ ግብፅ ግድቡ ወደ መገባደድ ምዕራፍ እየገፉም ቢሆን ጩኸታቸውን መቀጠላቸውና በሴራ ፖለቲካ መግፋታቸው፣ ከበስተጀርባው ምን ፍላጎት ቢኖር ነው የሚል ጥያቄ አሁንም መፍጠሩ አልቀረም፡፡
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋር ከሰሞኑ ከተደረገ ውይይት በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ በግድቡ ውኃ አሞላልና አገልግሎት አሰጣጥ (ኦፕሬሽን) ላይ አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈረም እንፈልጋለን ሲል መግለጹ ተዘግቧል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሹክሪ የአውሮፓ አገሮች ዲፕሎማቶችንና የኅብረቱ ባለሥልጣናትን ሰብስበው፣ ኢትዮጵያ ከታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ጋር ውል እንድታስር እንደጠየቁ በግብፅ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የግብፅ ፕሬዚዳንትና ሌሎች ባለሥልጣናትም የዓባይን ችግር በጉልበት ለመፍታት፣ አገራቸው አቅምና ፍላጎቱ እንዳላት ሲናገሩ ከርመዋል፡፡ ሁሉም ዓይነት አማራጭ ጠረጴዛ ላይ ነው የሚለው የግብፅ ባለሥልጣናት ሰሞነኛ ፉከራ አቋማቸው ምን እንደሆነ ጠቋሚ ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር፣ እንዲሁም የብሉ ናይል ውኃ ምርምር ተቋም ተመራማሪ የሆኑት አቶ አበበ ይርጋ፣ ‹‹ሁሉም አማራጭ በጠረጴዛ ላይ ነው የሚለው የግብፅ አባባል››፣ አገሪቱ በጉልበት እንጂ በዲፕሎማሲም ሆነ በድርድር እንደማታምን ማሳያ ነው ይሉታል፡፡
‹‹የኢትዮጵያን በውስጥ ችግር አቅሟ መዳከሙንና አለመረጋጋቷን በመጠቀም ነው ይህን ደጋግመው የሚናገሩት፡፡ የግድቡ ግንባታ እንደማይቆም እያወቁ፣ ከድርድር ውጪ አንዳችም አማራጭ እንደማያዋጣቸው እያወቁ ነው ጫና ለመፍጠር የሚጥሩት፡፡ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ የአሁኑን ብቻ ሳይሆን የመጪውን ትውልድ ጥቅም የሚነካ ስምምነት እንድንፈርም ይፈልጋሉ፡፡ የዓረብ አገሮችና የዓረብ ሊግ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ እንዲሁም አሜሪካ እንዲደግፏቸው ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ አንቶኒ ብሊንከን አሳሪ ስምምነት ብለው በቅርቡ መናገራቸው የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል፡፡ አሳሪ ስምምነት መፈረም እንደማንችል ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ መንግሥት አይፈቅዱም፡፡ አሁን እኮ ከጦርነት ወጥተናል፣ ያን ጊዜ ራሱ አልተቀበልነውም፡፡ ከተሳካ ልሞክር በሚል ነው የሚገፉት፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡
በታላቁ ህዳሴ ግድብ አንዱ የኢትዮጵያ ተደራዳሪና በውኃ ሀብት ዘርፍ በተለይ በዓባይ ጉዳይ ሰፊ ምርምር ያደረጉት ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የግብፆቹ ጩኸት የተለመደ ነው ይሉታል፡፡
‹‹አሁን የተለየው ግድቡ በሚሞላበት ሐምሌና ነሐሴ ሳይሆን የካቲትና መጋቢት ላይ መምጣቱ ነው፡፡ ከማርች 22 እስከ 24 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የውኃ ፎረም ይካሄድ ስለነበር ከዚያ ጋር ለማገናኘት የታሰበበት ይመስላል፡፡ ከግብፅ ጎን የቆሙ ወገኖችም የግብፅን አቋም እያንፀባረቁ ነው፤›› በማለት ነው የዓባይ ጉዳይ ምሁሩ የሚናገሩት፡፡
ግብፅ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ ስምምነት ካልተፈረመ እያለች መሆኑ ይነገራል፡፡ አገሪቱ ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ ልትከት ትፈልጋለች የሚለው ጉዳይም በበርካታ ምሁራን ዘንድ ሚዛን ይደፋል፡፡ ግብፅ ኢትዮጵያን ወደ አሳሪ ስምምነት በመክተት ወደፊት ግድቦችን በወንዞቿ ላይ እንዳትገነባ ጫና ለመፍጠር ማለሟንም ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት አስገዳጅ ስምምነቶችን ለመፈረም የምትገደድባቸው ምክንያቶች እንደሌሉ ነው ምሁራኑ የሚጠቁሙት፡፡
የግብፅ ባለሥልጣናት የግድቡን ውኃ ሙሌት ለማስቆም እንደማይቻል ባያጡትም፣ ነገር ግን ግድቡ ወደ ሥራ ከገባ በኋላም በሚኖረው የኃይል ማመንጨትና የውኃ አጠቃቀም ሥራዎች ላይ አገራቸው በቀጥታ እንድትሳተፍ ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ተገማች ነው፡፡ የካይሮ ሰዎች ግድቡን ማስቆሙ ባይሳካም ወደ ሥራ ሲገባ በአሳሪ ስምምነት ተከልለው የግድቡን የየዕለት ሥራ ለመከታተል መፈለጋቸውን፣ ከሰሞኑ እንቅስቃሴያቸው በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡
አቶ አበበ ስለዚሁ ጉዳይ ሲጠየቁ፣ በግድቡ አስተዳደርና አሠራር ግብፆቹ ካልተሳተፍን ቢሉም ነገር ግን ዕድሉ እንደሌላቸው ነው የሚናገሩት፡፡
‹‹ዲፕሎማሲያዊ ብልኃት በጎደለው መንገድ እያስፈራሩና ጠላትነታቸውን እያሳዩ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት አመኔታ ሊያገኙ አይችሉም፡፡ ንግግርና መተማመን ሲኖር ነው አብሮ መሥራት የሚቻለው፡፡ ንግግርም ሆነ አብሮ መሥራት እንዳይቻል እያደረጉ ኢትዮጵያ መጥተው ጉባ ላይ ተቀምጠው የግድቡን የውኃ ፍሰትና አገልግሎት ለመከታተል የሚችሉበት ዕድል የለም፡፡ ይህን በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከደኅንነት አኳያ ተገቢ ምላሽ ሰጥቶበታል፡፡ የእነሱን የውኃ አጠቃቀም መረጃና ዕቅድ ሳይሰጡ የእኛን የውኃ አጠቃቀም መረጃ ለመውሰድ መሞከር ስህተት ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የውኃ አጠቃቀም ሕጎች አሉ፡፡ እ.ኤ.አ. የ1997 ‹‹UN Water Course Convention›› (የተመድ ውኃ ስምምነትን) የሚጥስ ነው ፍላጎታቸው፡፡ የውኃ አጠቃቀም መረጃ የላይኛው ተፋሰስ አገር ብቻ ሳይሆን የታችኛውም የተፋሰስ አገር ይሰጣል፡፡ ግብፅ በተቃራኒው የምትፈልገው እሷ መረጃ ሳትሰጥ ለመውሰድ ነው፤›› በማለትም ተመራማሪው ያስረዳሉ፡፡
ግብፆቹ አሳሪ ሕግን የሚወተውቱት የግድቡን አገልግሎት ለመከታተል በመመኘት ብቻ አለመሆኑ ይነገራል፡፡ ከአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋር የተገናኙት ሳሚ ሹክሪ፣ ‹‹ኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት አንቃወምም፤›› ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡ ‹‹ነገር ግን ኢትዮጵያ ለመልማት ጥረት ስታደርግ የግብፅና የሱዳንን የውኃ ጥቅሞች እንድታከብር እንፈልጋለን፤›› ነበር ያሉት፡፡ ይህ የተለመደ የሚመስል የግብፅ ባለሥልጣናት የተደጋገመ አገላለጽ፣ አገሪቱ ከኢትዮጵያ ምን እንደምትፈልግ ገላጭ ሆኖ መቅረብ ይችላል ነው የሚባለው፡፡
የመጀመሪያው የግብፅና የሱዳን የውኃ ጥቅም የሚሉት ከሀብቱ ወሳኝ ባለቤት ኢትዮጵያ ጋር ፍፁም የሚያጋጭ መጠን መሆኑ ይነገራል፡፡ ግድቡ መያዝ አለበት የሚሉት የውኃ መጠንም ቢሆን ከኢትዮጵያ ጋር አያቀራርባቸውም፡፡ በየዓመቱ ይለቀቅልን ወይም ይፍሰስልን የሚሉት የውኃ ምጣኔም ቢሆን ኢትዮጵያን አያስማማም፡፡ ይህን በተመለከተ የግብፅና የሱዳንን ፍላጎት ከኢትዮጵያ ኪስ ውኃ የመፈለግ ብልጣ ብልጥነት ሲሉ ነው ታዛቢዎች የሚተቹት፡፡
ግብፅ በራሷ እጅ ከዓባይ በስፋት የመጠቀም ተስፋና ዕድሏን እያኮላሸች መሆኑን የሚናገሩት አቶ አበበ፣ አገሪቱ ኢትዮጵያን ደግፋ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጎን ብትቆም እንዲሁም አብሮ መሥራትን ብትመርጥ ይሻላት እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹እነሱ ውኃውን በደንብ ሲጠቀሙት ኖረዋል፣ እኛ ደግሞ አልተጠቀምንም፡፡ በፍጥነት እያደግን በመሆኑ ከድህነት ለመውጣት ውኃውን መጠቀማችን ይጨምራል፡፡ እነሱ በአስገዳጅ ስምምነት ስም የውኃ ባርነት ነው መፍጠር የሚፈልጉት፡፡ የኢትዮጵያን ውኃ መቆጣጠርና ኢትዮጵያ መብት እንዳይኖራት ማድረግ ነው ፍላጎታቸው፡፡ የሱዳኖችና የግብፆች ጥያቄ አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ የግድቡ የደኅንነት ጉዳይ ነው ሱዳኖችን የሚያሳስባቸው፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ ልምድና ጥራት ካላቸው ተቋራጮች ጋር ኢትየጵያ የምትሠራ በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ ገፍተው ችግር መፍጠር አልቻሉም፤›› በማለትም የግብፆችን ከውኃ ጉዳይ ጀርባ ያለ እኩይ ፍላጎት ያከብራሉ፡፡
ታላቁ የዓባይ ወንዝ ወይም ናይል የ11 አገሮችን የውኃ ጥም የሚቆርጥ ሰፊ የአፍሪካ ክፍልን የሚያካልል ዓለም አቀፍ ሀብት መሆኑ ይነገራል፡፡ የዚህ ታላቅ ሀብት ወሳኝ ምንጭ (ከ86 በመቶ በላይ የምታመነጨው) ደግሞ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ግብፆቹ የውኃ ጥቅማችንን ይጎዳል የሚሉት ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚገነባበት ቦታ ጉባ ከ50 በመቶ ያላነሰ የዓባይ ውኃ ወደ ጎረቤት ሱዳን የሚፈስበት ቦታ ነው፡፡ ይህን ውድ ሀብት ግን በፍትሐዊነትና በእኩልነት ለመጠቀም ግብፆቹ ሁሌም ዳተኝነት እንደሚታይባቸው ይታወቃል፡፡ ግብፆቹ የውኃ ጥቅማችን ይከበር እያሉ የሚወተውቱት ኢትዮጵያ በውኃው በመጠቀሟ ያጡት ነገር ኖሮ ሳይሆን፣ ፍፁም መስገብገብ በሞላበት የፖለቲካ ስሌት መነሻ እንደሆነ ብዙዎች ይተቻሉ፡፡ የግብፆች ፍላጎት ወደፊትም ቢሆን በዓባይ ተፋሰስ ላይ ተመሳሳይ የልማት ሥራዎችን ኢትዮጵያ እንዳትሠራ ለማሸማቀቅ ያለመ እኩይ ዓላማ ያለው እንደሆነ ይነገራል፡፡
ግብፆች የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይን በሰፊው የሚያጮሁትና የሚያራግቡት፣ ሁልጊዜ የውኃ ጥቅማችን ተነካ በሚል መነሻነት ብቻ አለመሆኑ ይነገራል፡፡ ግብፆች ከውኃ ጉዳይ ባለፈ የውስጥ ፖለቲካቸውን ለማስተንፈስና የሕዝብ ድጋፍም ለማግኘት፣ የዓባይ ጂኦፖለቲካ እንደሚጠቀሙበት ነው የዓባይ ተመራማሪው አቶ አበበ የሚናገሩት፡፡
‹‹የአልሲሲ መንግሥት በሰብዓዊ መብትና በዴሞክራሲ አያያዝ ይታማል፡፡ የውጭ ጠላት በመፍጠር ሕዝቡን ከጎኑ ለማሰለፍ ታላቁ ህዳሴ ግብን መቀስቀሻ አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ የሕዝቡን ሐሳብ ለማስለወጥ ወይም የተቃዋሚና የሕዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር ይጠቀምበታል፤›› ይላሉ፡፡
ግብፅ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የምታቀርበው ስሞታ መቼ እንደሚቆም አይታወቅም፡፡ ግድቡ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ የግብፅ ፖለቲከኞች ጉዳዩን ሲኮንኑት ኖረዋል፡፡ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም በተደጋጋሚ ወስደውታል፡፡ ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር የሶስትዮሽ የስምምነት ማዕቀፍ በመፈራረም፣ ጉዳዩን በዲፕሎማሲያዊ አማራጮች ለመፍታት ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡
የሦስትዮሽ የባለሙያዎች የጋራ ኮሚቴ በማቋቋምም በግድቡ የጎንዮሽ ተፅዕኖ ላይ ምክክርና ተደጋጋሚ ንግግሮች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በገለልተኛ ባለሙያዎች የግድቡ ተፅዕኖ ይጠና ሲባልም የውጭ ገለልተኛ አጥኚ ቡድን ተቀጥሮ ምክረ ሐሳብ እንዲቀርብ ኢትዮጵያ ፈቅዳለች፡፡ ኢትዮጵያ ግብፆችም ሆኑ ሱዳኖቹ የሚያነሱትን የተጋነነ ስሞታ ለማስቆም በሚል በግድቡ አሞላል ሒደት ላይ ሁሉንም ያማከለ አቀራራቢ አካሄድ ለመከተል የወሰነቸበት አጋጣሚም የሚታወስ ነው፡፡
ይሁን እንጂ የግብፅና የሱዳን ፖለቲከኞች የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ቢቻልም ለማስቀረት ስለነበር ዓላማቸው፣ አሳሪ ውል ካልተፈራረምን በሚል በኃያላን አገሮች ታግዘው ጭምር ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል፡፡ በዋናነት የግድቡን ጉዳይ በዓለም ባንክ ታዛቢነት በአሜሪካ አደራዳሪነት እናድርግ ከሚለው ሙግታቸው ጀምሮ፣ በተለያዩ መንገዶች ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ ሲሞክሩም ቆይተዋል፡፡
አቶ አበበ ይህን ሁኔታ በተመለከተ ሲጠየቁ፣ ግብፆቹ በየጊዜው አመላቸውን እየለዋወጡ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ሲያደርጉ መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡
‹‹መጀመሪያ መገንባት አይችሉም ሲሉን ነበር፡፡ ቀጥሎ ውኃ መያዝ አትችሉም አሉን፡፡ አሁን ደግሞ አሳሪ ሕግ ካልፈረማችሁ እያሉን ነው፡፡ ግብፆች እነዚህን ተለዋዋጭ የዲፕሎማሲ ጫናዎች የሚጠቀሙት ሆን ብለው ነው፡፡ እነዚህን መሰናክሎች ለማለፍ ኢትዮጵያ ቀላል ሥራ አይደለም የሠራችው፡፡ የእነሱ ጥቅም ብቻ እንዲጠበቅ እንደማንተባበር በደንብ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ከዚያ አካሄድ መላቀቅ አልቻሉም፤›› በማለት ነው ተመራማሪው የሚናገሩት፡፡
ግብፆቹና ከጎናቸው ያሠለፏቸው ሱዳኖች የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የወሰዱበት አጋጣሚም በርካታ ነበር፡፡ በዓለም አቀፍ ዳኝነቱ አልሳካ ሲላቸው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ በመግባትና በኢትዮጵያ ዙሪያ ቀጣናዊ አለመረጋጋት በመፍጠር ጫናቸውን እንደገፉበት ይነገራል፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ዛሬም ቢሆን አለመታረሙ ይስተዋላል፡፡ ሳሚ ሹክሪ አሳሪ ሕግ ካልተፈራረምን ቀጣናው ችግር ውስጥ ይወድቃል ከሰሞኑ ማለታቸው በራሱ ለዚህ ማረጋገጫ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡
የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪው ያዕቆብ (ዶ/ር) ግን ለሁሉም የሚበጀው ሰላማዊ መንገድ መሆኑን ያሳስባሉ፡፡ ‹‹እኛ እነሱ የሚያሰሙትን ቅሬታ በጋራ መድረኮቻችን እንዲያንፀባርቁ ወይም በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በሚደረገው ንግግር እንዲያመጡ ነው የምንፈልገው፡፡ እነሱ ግን ከዚህ ያፈነገጠ ነገር እያደረጉ ነው ያሉት፡፡ ግብፆቹ ከዚያ ያፈነገጠ ነገር ማድረጋቸው መልካም ወዳጅነትም ሆነ ጉርብትናና የትብብር መንፈስን አያሳይም፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡
የብሉ ናይል ተቋሙ ተመራማሪ አቶ አበበ በበኩላቸው፣ ‹‹የግብፅ ጥቅምና ፍላጎት የሚከበረው በንግግርና በድርድር ብቻ ነው፡፡ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ፍላጎትን ማስፈጸም አይቻልም፡፡ ከዚህ ያልተማሩት ግብፆች ባልበላም ጭሬ ልበትነው የሚል አካሄድ ነው የሚከተሉት፤›› ሲሉ ነው ሐሳባቸውን የሚያጋሩት፡፡
የዓባይ ህልውና ዘላቂ በሆነ መንገድ የሚረጋገጠው የኢትዮጵያ ህልውና ሲረጋገጥ ነው የሚለው መሠረታዊ መርህ ከጥቂት የግብፅ ልሂቃን በስተቀር ሲስተጋባ አለመታየቱ ብዙ ጊዜ በትዝብት ይነሳል፡፡ ኢትዮጵያ በጦርነት፣ በግጭትና በቀውስ አዙሪት የምትዳክር ከሆነ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቦታ እንደማይኖረው፣ በዚህ የተነሳም የዓባይ ተፋሰስ ዘላቂነት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ በዘርፉ ባለሙያዎች ማሳሰቢያ ቢቀርብም፣ የግብፅና የሱዳን ባለሥልጣናት ግን ኢትዮጵያን ጎድቶ ወንዙን ስለመጠቀም ነው ሁሌም የሚያልሙት እየተባለ ይተቻል፡፡
ከሰሞኑ የጋራ መግለጫ ያወጡት በውጭ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አካላትን የወከሉ ድርጅቶች ይህንኑ ጉዳይ ያነሱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በራሷ የውኃ ሀብት የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት እንዳላት ነው የገለጹት፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ካላት የውኃ ኃይል የማመንጨት አቅም አንድ በመቶውን ብቻ ነው ጥቅም ላይ ያዋለችው፤›› ይላል የጋራ መግለጫው፡፡ ከ122 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 65 በመቶው ዛሬም ድረስ ብርሃን አይቶ እንደማያውቅ መግለጫው ያሰምርበታል፡፡ ‹‹ለግብፃዊያን ወንድሞቻችን ማረጋገጥ የምንወደው ኢትዮጵያውያን ፍትሐዊና ተመጣጣኝ የውኃ ሀብት ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ከመፈለግ በዘለለ፣ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን አደጋ ላይ ለመጣል እንደማንፈልግ ለማረጋገጥ እንወዳለን፤›› የሚለው መግለጫው፣ ግብፅ ከጠብ አጫሪና ቀጣናውን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ድርጊቶች ተቆጥበው በሕጋዊ መንገድ በንግግር ፍላጎታቸውን እንዲያቀርቡ ይጠይቃል፡፡