በደመቀ ከበደ
ዝምታ ሲበዛ ፣ የራስ አፍ ያገማል
ብዙ መናገርም ፣ ሐሳብ ያገለማል፤
ግና በኒህ ፅንፎች
በአለማውራትና ፣ በመናገር መሃል
አለ ጥልቅ ነገር ፣ ማስተዋል የሚባል፡፡
ይህንን እያሰብኩ ፤ እኔ እተክዛለሁ
ከሕመምና ሳቅ ፤ ስንኝ እመዛለሁ፡፡
‹‹ለአፍታ በአርምሞ ፤ ቆሞ ላስተዋለው
ዝምታም ሕመም ነው ፤ ጩኸትም ሕመም ነው››
እንዳለው ገጣሚ ፤ ያማል፣ ያማል፣ ያማል፤ አዎ ሁሉም ‹‹ያማል››
ያልታመመ የለም፤ በጥጋጥጉ ፤ የጣር ድምፅ ይሰማል
ይህን መስማት ደግሞ ፤ ይብስ እጥፍ ያማል
ያማል አዎ ያማል!!
በመስማት ታምሜ፤ በማየት ታምሜ፤
በማሰብ ታምሜ፤ በማለም ታምሜ፤
በማንበብ ታምሜ ፣ በመፃፍ ታምሜ፤
ታምሜ፣ ታምሜ፣ ………..
በአስታማሚ ማጣት ፤ እያየኝ ደክሜ
እዩት ያን ወንድሜን ፤ ዳር ቆሞ ይስቃል
በታማሚ ተውኔት ፤ ጥርሱ እስከሚሰበር
ሰርክ ይፈንድቃል፤ ሰርክ ይንፈቀፈቃል፡፡
ይህን ሳቅ መስማትም ፤ እጅጉን ያደማል
ያማል አዎ ያማል፤
ዝምም አፍ ያገማል
መናገር ‹‹ነውር ነው››፤ ሐሳብ ያገለማል፤
ከህልቆ ሕመሞች ፤ አንደኛውን ሕመም ፤ መምረጥ የቸገረኝ
ሕመም የወለደው ፤ ሕመም ያናወዘው፤ አንድ ሐሳብ ነበረኝ፡፡
‹‹በጤነኞች መሃል ፤ ታማሚ ከበዛ
ወይ አካሚ ቅጠር ፤ ወይ መድኃኒት ግዛ››
በሚል አመክንዮ ፤ ላይጠግግ ሕመሜ ፤ ላልሆን እንደቀድሞ
ላምጠው እንግዲህ፤ ከሕመሜ ልውለድ ፤ የሚያድን አክሞ!!