በሕብስት አበበ
የበዓል መቃረቢያ ሰሞን ዘንቢል አንጠልጥለው የሚሮጡ እናቶች ቁጥር በርከት ይላል፡፡ ሁሉም በአቅሙ ለበዓል ቤቱን ለማሞቅ የበዓል ሸመታ የሚዘለቅ ቢሆንም፣ የሸቀጦች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመር ግን ወገብ የሚሰብር ሆኖባቸዋል፡፡
የበዓል ገበያ ይጨምራል በማለት አብዛኛው ሸማች ተበድሮ አልያም ለወር ካሰበው ላይ ቀንሶ ይገበያያል፡፡ መንግሥትም የበዓል ወቅት በመምጣቱ ብቻ የሚስተዋለውን ምክንያታዊ ያልሆነ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ለመከላከል ኮሚቴ ከማዋቀር በዘለለ እዚህ ግባ የሚባል መፍትሔ አምጥቶ አያውቅም፡፡
በኢትዮጵያ በክርስቲያንና በሙስሊም ምዕመን በዋናነት የሚከበሩ በዓላት ከስምንት በላይ ቢሆኑም፣ እነዚህ በዓላት በመጡ ቁጥር ማኅበረሰቡ በኑሮ ይፈተናል፡፡ በዋናነት በበዓል ወቅት የሚዘወተሩ ቅቤ፣ ሽንኩርት፣ ዶሮ፣ በግ፣ ዕንቁላል መሰል ግብዓቶችና በዋዜማው ዋጋቸው ጣሪያ ይነካል፡፡
እነዚህ ነጋዴዎች በበዓል ዋዜማ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚዳክሩ ቢሆንም፣ በመንግሥት ደረጃ ቁጥጥር ያደርጋሉ ተብለው የሚዋቀሩ ቡድኖችም ለዚህ ተጠያቂ ናቸው፡፡
ለበዓል ሸመታ ተብሎ በተለየ ሁኔታ ገንዘብ የሚያጠራቅሙም አሉ፡፡ ይህም በከፍተኛ ሁኔታ ከነጋዴውና በደላላው በደንብ ስለሚታወቅ ገበያውን በፈለጉት ልክ ሲያንቀሳቅሱት ይታያል፡፡
ይህም እንደ ከዚህ ቀደሙ ነገ ልግዛው አልግዛው ለመወሰን አስቸጋሪ እንደሆነ የሚያውቁት ነጋዴዎች በፈለጉት ልክ ዋጋውን ይተምናሉ፡፡ ለምሳሌ ብናነሳ በማንኛውም ጊዜ ዶሮ ለመግዛት አማራጭ ባይኖርም፣ በሌላ ቀን መግዛት በመቻሉ የዋጋ ጉዳይ በገዥው እጅ ነው፡፡ የዚህ የገበያ ሁኔታ ለበዓል ወቅት የተገላቢጦሽ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ሸማቹ ለበዓል የሚሆነውን ሸቀጦች የግድ መግዛት እንዳለበት ስለሚታወቅ የዋጋው ጉዳይ በነጋዴው እጅ ይወድቃል፡፡
ሸማቹ የዋጋ ተመኑ ልክ ገንዘብ ባይዝ እንኳን መጠኑን ወይም ኪሎውን ቀንሶ ለመግዛት ሲገደድ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ የቅቤን ዋጋ ስንመለከት በሾላ ገበያ የበዓል ገበያ ከመቃረቡ በፊት እስከ 900 ብር ድረስ በኪሎ ይሸጣል፡፡
ይሁን እንጂ አንድ ሸማች ከአንዳንድ የበዓል ሸቀጦች ውጪ በአብዛኛው ላይ ዋጋ ስለሚጨምር፣ ሸማቹ ሳይወድ በግዱ አንድ ኪሎ ለመግዛት ሄዶ ግማሽ ኪሎ እንዲገዛ ይገደዳል፡፡
የበዓል መቃረቢያ ወቅት ተጠቃሚ የሚሆኑት ነጋዴውና ደላላው ሲሆን፣ የሁለቱ ጥምረት የገበያውን ዋጋ በፈለጉት ልክ እንዲዘውሩት ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡ ለዚህ እንደ ማሳያ የሚነሳው ምንም እንኳን ገበያውን ለማረጋጋት መንግሥት የሚኖሩ ቡድኖች ቁጥጥር አደርጋለሁ ቢልም፣ ሲባባስ እንጂ ሲሻሻል እንዳልታየ የዓመታት የበዓል ወቅት ገበያን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡
የበዓል ወቅት ገበያ መጨመር ከነጋዴዎችና ከደላሎች በተጨማሪ የትራንስፖርት ዋጋ መናርም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከወላይታ የሚመጣ ዶሮ አዲስ አበባ ሲደርስ ከ700 እስከ አንድ ሺሕ ይሸጣል፡፡ ነገር ግን ዶሮው የሚመጣበት ቦታ ላይ ግን አዲስ አበባ ከሚሸጠው በግማሽ እንደሚቀንስ ይታወቃል፡፡
ለዚህም እንደ ምክንያት የሚነሳው የትራንስፖርትና ሌሎች መሰል ወጪዎች ተደምረው ዋጋውን ከፍ እንደሚያደርግ ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በበዓል ወቅት ሁሉም ገዥ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ ይህም ለገበያው የሚቀርበውና የሚፈለገው ወይም ደግሞ አቅርቦትና ፍላጎት ለመጣጣም በራሱ የዋጋው ጭማሪ እንዲታይ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡
የሸማቹ ፍላጎትና ለበዓል ገበያ የቀረቡ ምርቶች በፍላጎት ልክ ሳይሆን ሲቀር፣ ዘርፉን የሚዘውሩት ደግሞ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ይጠቀሙበታል ይወስዱታል፡፡ በሌላ በኩል ትልልቅ ግብይቶች ዓመቱን ሙሉ ቁጭ ብለው በዓል ሲቃረብ የሚነቃቁበት ምርቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም ምርቶች ውስጥ አንዱ የሆነው በገና በዓል ወቅት የሚዘወተረው የስጦታ ዕቃዎችን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡
በዚህ ለበዓል ገበያ ተፈላጊ የሆኑት እነዚህ ምርቶች ዓመቱን ሙሉ በተፈለገው ልክ ስለማይሸጡ፣ በነጋዴዎች ይህችን ወቅት ጠብቀው ዋጋውን ጣሪያ ላይ ያደርሳሉ፡፡ በሌላ በኩል በበዓል ወቅት የዋጋ መጨመር ሌላኛው ምክንያት የሸማቹ (ገዥዎች) እንደ ወትሮ ሳይሆን፣ በተለየ ሁኔታ ብር የማውጣት አቅማቸው ከፍ ሲል ይስተዋላል፡፡
ገንዘቡ በብድር አልያም በሌላ ሁኔታ የሚመጣ እንኳ ቢሆን ለበ
ዓል ጊዜ ሳይሰስቱ የሚያወጡት ልምድ መኖሩ ሌላኛው ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡ ለኢትዮጵያ በክርስትናና በእስልምና ዕምነት በዓመት የሚከበሩ በዓላት ጥቂት ቢሆኑም፣ ማኅበረሰቡ ለበዓል ባለው ጉጉት ምክንያት የሚመጣው ውጪ የትየለሌ ነው፡፡
በበዓል ወቅት የመንግሥት ዕርምጃ ደግሞ ዘለቄታዊ ሳይሆን ነገሮችን የሚያባብስ መሆኑ ይነገራል፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ የሚነሳው፣ ለማሳያነት በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚቀርበው ምርት ዘላቂ አይደለም፡፡
የበዓል ገበያ ያረጋጋል የሚባለው ዘዴ ይብሱኑ የሚያባብስና ከመደበኛ ገበያው ዋጋ ጋር ለምሳሌ በመደበኛ ገበያ በበዓል ወቅት የሐበሻ እንቁላል ከ13 እስከ 12 ብር ድረስ ሲሸጥ፣ መንግሥት በሚያቋቁማቸው ገበያዎች ደግሞ እስከ 11.50 ሳንቲም ድረስ ነው፡፡ ይህም ኅብረተሰቡ አቅራቢያው ከሚገኘው መደበኛ ገበያን አንድ እንቁላል በአሥር ብር መግዛትን ሲመርጥ ይስተዋላል፡፡ ምክንያቱም ትራንስፖርት፣ ልፋትና ሌሎች ውጣ ውረዶች ከመጋለጥ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ይላሉ፡፡
ለዚህ ሁሉ ችግር መንግሥት በጊዜያዊነት መፍትሔ ያለውን የገበያ መረጋጊያ ዘዴ ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ፣ ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባዋል፡፡ የገበያ ዋጋ አለመረጋጋት በበዓል ገበያ ብቻ የሚታይ ባለመሆኑ፣ መንግሥት በገበያው የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት በመውጣት ኅብረተሰቡን ካላስፈላጊ ቀውስ መታደግ አለበት፡፡
በተለይም በበዓል ገበያ መንግሥት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት መጠቀም እንደማይችል ባለሙያዎችም ይናገራሉ፡፡
ምርት የሚመጣባቸው አካባቢዎች ሰላም መደፍረስ ሌላኛው ችግር ሲሆን፣ መንግሥት በሌላ የገበያ (ማርኬቱ) ከቁጥጥር ውጪ እንደሆነ ምክንያት ሆኗል፡፡
|
|
|